ለሕንድ ባለኃብቶች መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 11ሐ 2005 (ዋኢማ) - የሕንድ ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚያካሂዱት የኢንቨስትመንት ሥራ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፋፍ እንደሚያደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ 250 ሺህ የሕንድ ኩባንያዎች የወከሉ 15 አባላትን ማምሻውን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል፡፡ አሁን ያለው የሕንዳውያን የ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት መጠን በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ወደ 10 ቢሊዮን ለማሳደግ ዕቅድ እንዳለ አመልክተዋል። ሕንዳውያን ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ያለውን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ተጠቅመው ሙዓለ ነዋያቸውን ቢያፈሱ ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ በመንግሥት በኩል እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም አረጋግጠዋል፡፡

የሕንድ የንግድና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አር.ቪ. ካኖሪያ በበኩላቸው የሕንድ ባለኃብቶች በኢትዮጵያ ሙዓለ ነዋያቸውን ለማፍሰስ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

በተለይ በኢንዱስትሪ መስክ የሕንድ ባለኃብቶች በስፋት መሰማራት እንደሚፈልጉ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የሕንዳውያን የኢንቨስትመንት መጠንን በቀጣይነት ለማሳደግ ያቀደችውን ዕቅድ በጋራ ለማሳካትም በቅርበት ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ ሕንዳውያን ባለኃብቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በግብርና፣ በማንፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን ዕቃዎች፣ በሆቴልና በመሰረተ ልማት ዘርፎች በስፋት ለመሰማራት መጠያቀቸውን ውይይቱን የተከታተሉ አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡