የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ማዳን እንደሚቻል ተገለፀ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 9/2005 (ዋኢማ) - የዓለም የስነ ህዝብ ፈንድ የ2012 ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት እንዳለው ታዳጊ ሀገራት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ አላስፈላጊ ወጪን ማዳን ይችላሉ፡፡

የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት ሲባል የእናቶችና ህጻናትን ሞት መቀነስ የጤና አገልግሎትን ማዳረስ የትምህርት እድል እንዲኖር ማድረግ ነው ያለው ሪፖርቱ ታዳጊ ሀገራት ለእነዚህ የሚያወጡትን 11.3 ቢሊዮን ዶላር ማዳን ይችላሉ፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በተወካያቸው አማካኝነት ባስተላለፉት መልዕክት ኢትዮጵያ የምዕተ ዓመቱን የልማት ግብ ለማሳካት በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ የእናቶችና ህጻናት ሞትን መቀነስ ችላለች ብለዋል፡፡

የዓለም ስነ ህዝብ ፈንድ በኢትዮጵያ ባካሄደው ጥናት ባለፉት 10 ዓመታት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት እድገት እያስመዘገበ መሆኑን ገልጿል፡፡ በዚህም በጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም፣ በከተሞች መስፋፋት፣ በትምህርት እድል ማግኘት፣ የህጻናት ሞት መቀነስና በቤተሰብ ምጣኔ የወንዶች ተሳታፊነት ምክንያት የተጠቃሚዎቹ ቁጥር ጨምሯል፡፡ ሆኖም የጐንዮሽ ጉዳትን መፍራት ያልተፈታ ችግር መሆኑ ተመልክቷል፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አብርሃም ተከስተ የቤተሰብ ምጣኔ ለታዳጊ ሀገራት ያለውን ጠቀሜታ አስታሰው ኢትዮጵያም በቂ በጀት በመመደብ ዜጎች በቂ የትምህርት እና የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እያደረገች ነው ብለዋል፡፡