ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን አዲስ አበባ ውስጥ በድምቀት ተከበረ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 7/2005 (ዋኢማ) - ሕገ መንግሥቱ ያረጋገጠውን የእኩልነት መብት በአግባቡ በመጠቀም የመቻቻል ባህልን ከወትሮው በበለጠ ማዳበር እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
"የመቻቻል ባህላችንን በማጉላት ለዓለም ተምሳሌት እንሆናለን" በሚል መሪ ቃል ትናንት ዓለም አቀፍ የመቻቻል ቀን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እስከ ብሔራዊ ትያትር ድረስ በእግር ጉዞና በጥናታዊ ጽሁፎች ላይ ውይይት በማድረግ ተከብሯል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት /ዩኒስኮ/ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እንዲከበሩ ካፀደቃቸው በዓላት መካከል ኅዳር 16 ቀን የሚከበረው ዓለም ዓቀፍ የመቻቻል ቀን ነው፡፡

ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ዳውድ መሐመድ ቀኑን አስመልክተው እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች በቋንቋቸው የመናገርና የመፃፍ፣ የማሳደግና ባህላቸውን የመግለፅ፣ የማዳበር፣ የማስፋፋት እንዲሁም ታሪካቸውን የማሳደግ ሕገ መንግስታዊ እውቅና አግኝተዋል፡፡

ይህ በዓል የአገሪቷ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሕገ መንግስታዊ እውቅና ባገኙበት የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዋዜማ መከበሩ በዓሉን ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

በዓሉን ስናከበር የመቻቻል እሴቶቻችንን እንደ ባህል በመጠበቅ ሃገራችን በመተግበር ላይ ያለችውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድን ከግብ ለማድረስና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ራዕይ ለማስቀጠል የመቻቻል ባህል መጎልበት ወሳኝነት አለው፡፡

የኢንተርፌስ ፒስ ቢዩልዲንግ ኢንሼቲቭ የቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ሙሴ ኃይሉ በበኩላቸው በህዝቦች እኩልነት ላይ የተመሰረተችና በኢኮኖሚ የበለፀገች ሀገር ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት የሚሳካው በሕዝቦች መቻቻልና በመከባበር ነው፡፡

እንደ ኢዜአ ዘገባ  ኢንተርፌስ ፒስ ቢዩልዲንግ ኢንሼቲቭ ለዚህ የጋራ እሴት ዘላቂነት ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር በመስራት ላይ እንደሚገኝም ገልፀዋል፡፡ በውይይቱ ላይ መቻቻልና ተግዳሮቶቹ፣ ልማት፣ ዴሞክራሲና የኃይማኖት አክራሪነት፣ መቻቻልና ኃይማኖት፣ መቻቻልና ወጣቶች በሚል ርዕስ ጥናታዊ ፅሁፎች ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡