ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ድል ቀንቷቸዋል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2005 (ዋኢማ) - ባለፈው እሁድ በሊባኖስ ቤይሩትና በስፔን አንታርዮሪካ ቦርጎስ ከተሞች በተካሄዱ የማራቶንና የዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮች ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሁለቱም ፆታ የበላይነትን ይዘው አሸንፈዋል።

ለአስረኛ ጊዜ በተካሄደው የቤይሩት ማራቶን ውድድር ፍቃዱ ከድር በወንዶች፣ ሰኢዳ ከድር ደግሞ በሴቶች ቀዳሚ ሆነው ውድድራቸውን ፈፅመዋል። ከሰላሳ ሦስት ሺ በላይ አትሌቶች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር በቦታው ከነበረው የአየር ፀባይ ዝናባማነት ጋር ተያይዞ ምንም አይነት ክብረወሰን ሳይሻሻል ቀርቷል።

የኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች የበላይነት በተንፀባረቀበት በዚህ ውድድር በወንዶች አትሌት ፍቃዱ ከኬንያውያን አትሌቶች እልህ አስጨራሽ ፉክክር ቢገጥመውም 2፡12፡57 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆኖ ውድድሩን ፈጽሟል።

በዚህ ውድድር ብዙም ግምት ያልተሰጠው ፍቃዱ ኬንያውያኑን ስቴፈን ቺፕኮፖልና ዊሊያም ኪፕሳንግን በአስደናቂ የራስ መተማመን እያፈራረቀ በማዳከም ለድጋፍ የወጡትን በርካታ የሀገሩ ልጆችን አስደስቷል።

ፍቃዱን ተከትሎ ሁለተኛ በመሆን ውድድሩን ያጠናቀቀው ቺፕኮፖል 2፡13፡14 ሰዓት ተመዝግ ቦለታል። ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን የፈፀ መው ኪፕሳንግም 2፡14፡53 የሆነ ሰዓት ማስመዝገብ ችሏል።

በሴቶች በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ሰኢዳ ከድር ከኬንያና አሜሪካ አትሌቶች ጋር ተፎካክራ 2፡35፡08 በሆነ ሰዓት ቀዳሚ ሆና ውድድሯን አጠናቅቃለች።ኬንያዊቷ ሞኒካ ጂፕኮኢች 2፡36፡20 በሆነ ሰዓት ሁለተኛ ሆና ውድድሯን አጠናቅቃለች። አሜሪካዊቷ ማሪይ ኤኮር 2፡37፡32 የሆነ ሰዓት አስመዝግባ ሦስተኛ ሆናለች።

ከዘጠና ስድስት ሀገሮች የተውጣጡ አትሌቶች የተሳተፉበት ይህ ውድድር በከባድ ዝናብና ንፋስ መታጀቡ ለአትሌቶቹ ብቻ ሳይሆን ለአዘጋጆቹም ፈተና ሆኖ እንደነበር የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ድረ-ገፅ ዘገባ ያመለክታል።

በአረብ ሀገራት የተከሰተውን አለመረጋጋት አስመልክቶ የስፖርትን ጥሩነት ለሀገሪቱ ህዝቦች በስፋት ለማስተዋወቅ የተዘጋጀው ይህ ውድድር ከሳምንታት በፊት በቤይሩት ተከስቶ በነበረው ፍንዳታ ለተሰውት ሰባት የሊባኖስ ማራቶን ሯጮች መታሰቢያና በፍንዳታው ለተጎዱ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ እንደሆነም ተገልጿል።

በዚህ ውድድር በርካታ የሀገሪቱና የውጭ ጋዜጠኞች የተሳተፉ ሲሆን፣ ለአሸናፊዎቹም የቤይሩት ማራቶን ማህበር ፕሬዚዳንት ሜይ ኤል ከሊል ሽልማት አበርክተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በስፔን ዓለም አቀፍ ሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ኢማና መርጋ በአስገራሚ የአጨራረስ ብቃት የቀድሞ ድሉን ደግሟል።በዚህ ውድድር ኢማና እስከ መጨረሻዎቹ ሦስት መቶ ሜትሮች ከኬንያውያኑ ኢማኑኤል ቤትና ቪንሰንት ቺፕኮክ ጋር ጎን ለጎን ሲሮጥ ነበር።በዚህም ኢማና በኬንያ አትሌቶች የመሸነፍ እድሉ ከፍተኛ ነበር።

ኢማና ምንም እንኳን በውድድሩ እስክ መጨረሻው ድረስ ፈተና ቢበዛበትም ያለውን ልምድና የአጨራረስ ብቃት ተጠቅሞ የቀድሞ ስሙን አስጠብቋል።ኢማና ውድድሩን ለመፈፀም 28፡05 የሆነ ሰዓት ፈጅቶበታል።

በውድድሩ ከኢማና ጋር ጠንካራ ፉክክር ያደረገው ኬንያዊው ቺፕኮክ ለማሸነፍ ያደረገው ከፍተኛ ጥረት እንዳልተሳካለት ሲያውቀው ፉክክሩን ከአገሩ ልጅ ጋር በማድረግ የሁለተኛነቱን ደረጃ አስጠብቋል።ቺፕኮክ ውድድሩን የፈፀመው ከኢማና ሁለት ሰከንድ ዘግይቶ በ28፡07 ነው።በሦስተኛነት ያጠናቀቀው ቤትም ውድድሩን ለመፈፀም28፡09 ሰዓት ፈጅቶበታል፡፡

ጠንካራ ፉክክር በተስተዋለበት በዚህ ውድድር አርባ ያህል አትሌቶች ሦስት ሺ ሜትሩን በ9፡02 ሰዓት ሲሮጡ የአውሮፓ የአስር ሺ ሜትር የነሃስ ሜዳሊያ ባለቤት ጣሊያናዊው ዳንኤል ሙሲ የውድድሩን አሸናፊነት ከአፍሪካውያን ለመንጠቅ ተቃርቦ የነበረ ቢሆንም ሳይሳካለት ቀርቷል።

ከአምስት ሺ ሜትር በኋላ ፉክክሩን በኡጋንዳዊው ሞሰስ ኪቤትና በስፔናዊው አያድ ላምዳሰም መካከል ሆኖ ነበር።የእነዚህ አትሌቶች ፉክክር ብዙም ሳይቆይ ቀዳሚ ሆነው ባጠናቀቁት አትሌቶች መካከል ሊሆን ችሏል።

ከኡጋንዳዊው አትሌት ሞሰስ ተረክቦ ውድድሩን ከፊት ከፊት ሲመራ የነበረው ኬንያዊው ቤት ውድድሩ እስኪጠናቀቅ ያለውን ጉልበት በአግባቡ ተቆጣጥሮ መጠቀም ባለመቻሉ ወደኋላ ሊቀር ችሏል።ኢማናና ቺፕኮክ ቤትን ተከትለው በእርሱ ትንፋሽ መሮጣቸው ውድድሩ ሊጠናቀቅ ጥቂት ሲቀረው ፍጥነታቸውን ጨምረው እንዲሮጡ አስችሏቸዋል።

በስፔን ባደረጋቸው ሦስት ውድድሮች ሦስቱንም በማሸነፍ በስፔናውያን ዘንድ ትልቅ ክብር ማግኘት የቻለው ኢማና «በእውነቱ ለመናገር ውድድሩ ጠንካራ ፉክክር የተደረገበት ነበር፤ቤትና ቺፕኮክ ውድደሩን ከባድ አድርገውታል ማለት እችላለሁ፤በአጨራረስ ብቃቴ ስለምተማመን እስከመጨረሻው ድረስ ልታገሳቸው ወሰንኩ ተሳካልኝም»በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል።ከዓመት በፊት በፑንታ አምብሪያ ተመሳሳይ ውድድር አሸንፏል።

በሴቶች በተደረገው ተመሳሳይ ውድድር ብዙም ግምት ያልተሰጣት ህይወት አያሌው አሸናፊ ሆናለች።ህይወት ውድድሩን በቀዳሚነት ያጠናቀቀችው የአሸናፊነት ግምት የተሰጣትን ኬንያዊቷን ሊኔት ማሳይን ቀድማ ነው።

በለንደን ኦሊምፒክ የሦስት ሺ ሜትር መሰናክል አምስተኛ ደረጃን ይዛ ያጠናቀቀችው ህይወት ኬንያዊቷ ቼሞስን ብቻሳይሆን ፖርቹጋላዊቷ ሳራ ሞሬራን፤ፕሪስካህ ቼሮኖን፤አቫ ሁቺንሰንን የመሳሰሉ አትሌቶችን ታሸንፋለች ብሎ የገመተ አልነበረም።
በርካታ አትሌቶችና የጤና ተሳታፊዎች በተሳተፉበት በዚህ ውድድር ህይወት በቀዳሚነት ውድድሯን የፈፀመችው 25፡01 በሆነ ፈጣን ሰዓት ነው።ህይወት ውድድሩን ስታጠናቅቅ ከተፎካካሪዎቿ ከሃምሳ ሜትር በላይ ርቃ ነበር።

ትኩረት አግኝታ የነበረችው ማሳይ ከህይወት አስራ ስምንት ሰከንድ ዘግይታ ሁለተኛ በመሆን ውድድሯን አጠናቅቃለች።አየርላንዳዊቷ ፊዮናላ ብሪተን በአስደናቂ ሁኔታ ግምት አግኝተው የነበሩትን አትሌቶች ቀድማ ሶስተኛ መሆኗ አስገራሚ ክስተት ሆኗል።

«በውድድሩ ማሳይና እኔ ጠንካራ ፉክክር አድርገናል፤እንደ አጋጣሚ ሆኖ ማሳይ ወደ መጨረሻ ላይ ባትወድቅ ኖሮ እንደሷ ያለን የርቀቱን ንጉሥ ማሸነፍ ይከብዳል»በማለት ህይወት አስተያየቷን ሰጥታለች።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ ማሳይ በበኩሏ «በርካታ ቁጥር ያላቸው ተወዳዳሪዎች በማየቴ ተደንቄአለሁ፤በውድድሩ መጨረሻ አካባቢ ወድቄ አንደኛ ባለመውጣቴ ደጋፊዎቼን ይቅርታ እጠይቃለሁ፤በውድድሩ ግን በጣም ደስተኛ ነኝ»በማለት እስተያየቷን ሰጥታለች።