የኢኮዋስ መሪዎች ወደሰሜናዊ ማሊ ሠራዊት ለመላክ ተስማሙ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2005 (ዋኢማ) - የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) መሪዎች ሰሜናዊ ማሊን ከፅንፈኞች ቁጥጥር ነፃ የሚያወጣ 3,300 አባሎች የሚኖሩት የጦር ኃይል ለመላክ መስማማታቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ።
የኢኮዋስ መሪዎች ከእዚህ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ከትናንት በስቲያ ያስታወቁት የወቅቱ የድርጅቱ ሊቀመንበር የሆኑት የኮትዲቯር ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ መሆናቸውን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።

የመሪዎች ጉባኤ ሰሞኑን በናይጄሪያ ዋና ከተማ አቡጃ ውስጥ ያካሄዱት ስብሰባ ከተፈፀመ በኋላ የኢኮዋስ የወቅቱ ሊመቀንበር እዚያው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ድርጅቱ በሰሜናዊ ማሊ የሚገኙትን ሽብርተኞችና የዘርጉትን የወንጀል አውታር የሚያጠፋ ወታደራዊ ኃይል ለመላክ ዝግጁ እንደሆነ አረጋግጠዋል።

ይህንኑ አቢይ ተግባር ለመፈፀም የሚላከው የኢኮዋስ ወታደራዊ ኃይል ከናይጄሪያ፣ ከኒጀር፣ ከቡርኪናፋሶና ከሌሎችም የሚውጣጣ እንደሚሆን ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ አመልክተዋል።

ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድኖችና የቱዋሬግ አማፅያን ሰሜናዊ ማሊን የተቆጣጠሩት የቀድሞውን የማሊ ፕሬዚዳንት አማዱ ቱማኒ ቱሬን መንግሥት ያስወገደውንና ባለፈው መጋቢት ውስጥ የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ እንደሆነ ይታወቃል።

በሻምበል አማዱ ሳኖጐ የተመራው ወታደራዊ ቡድን ወታደራዊ የመፈንቅለ-መንግሥት እርምጃውን ለመውሰድ የተገደደው የፕሬዚዳንት አማዱ ቱማኒ ቱሬ መንግሥት በሰሜናዊ ማሊ ውስጥ በቱዋሬግ አማፅያን የሚካሄደውን የነፃነት ንቅናቄ ለመቋቋምና ለማስወገድ በሚደረገው ጥረት የአመራር ድክመት አሳይቷል በሚል ምክንያት እንደሆነ ማመልከቱ ተገልጿል።

ወታደራዊ የመፈንቅለ-መንግሥት እርምጃው በፈጠረው የደህንነት ክፍተት የተጠቁሙት ፅንፈኞችና የቱዋሬግ አማፅያን ቡድኖች ሰሜናዊውን የአገሪቱ ክፍል በቀላሉ ለመቆጣጠር ችለዋል።

ከኢስላማዊ ማግሬብ አልቃይዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የተነገረለት አንሳር ዲኔ የተባለው ፅንፈኛ እስላማዊ ቡድንና ሌሎች ሁለት ፅንፈኛ ቡድኖች በሂደት የቱዋሬግ ነፃነት ንቅናቄ በሚል ስም የሚታወቀውን ቡድን አሸንፈው አካባቢውን በመላ ተቆጣጥረዋል። ፅንፈኛ አሸባሪ ቡድኖችና ተባባሪዎቻቸው አካባቢውን መቆጣጠራቸው ደግሞ በማሊ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው አገሮች ሰላም ላይ ስጋት እንደፈጠረ ተረጋግጧል።

እነዚህን ቡድኖች ለማስወገድ ከአካባቢ የተውጣጣ ወታደራዊ ኃይል ማሰማራት አስፈላጊ የሆነውም በእዚሁ ምክንያት እንደሆነ ተገልጿል።

የኢኮዋስ መሪዎች ሰሞኑን አቡጃ ውስጥ ባካሄዱት ስብሰባ 3,300 አባሎች የሚኖሩ ወታደራዊ ኃይል ወደሰሜናዊ ማሊ እንዲዘምት የደረሱበትን ስምምነት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤት በእዚህ ወር መጨረሻ ወይም በታኅሣሥ መግቢያ ላይ ሊያፅደቀው እንደሚችል የታመነ መሆኑንም የወቅቱ የኢኮዋስ ሊቀመንበር ፕሬዚዳንት አላሳን ዋታራ በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫቸው አመልክተዋል።በዋነኛነት ከናይጄሪያ፣ ከኒጀርና ከቡርኪና ፋሶ የሚውጣጣውን ዘማች ጦር ኃይል የማዋጣት፣ ሥልጠና የመስጠትና የዘማቹን ጦር ሠፈሮች በደቡባዊ ማሊ ውስጥ የማዘጋጀቱ ጥረት ስድስት ወራት ሊወስድ የተገመተ መሆኑንም ሊቀመንበሩ ማመልከታቸው ተገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤት እ.አ.አ ከጥቅምት 12/2012 አንስቶ በ45 ቀናት ውስጥ የአካባቢው መሪዎች ወደሰሜናዊ ማሊ የውጭ ኃይል ለማስገባት የሚያስችል ዕቅድ አውጥተው እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ ውሳኔ እንዳሳለፈ መገለጹ ይታወሳል።

ከአቡጃው የኢኮዋስ የመሪዎች ስብሰባ ፍጻሜ በኋላ የወጣ መግለጫ በማሊ የተፈጠረውን ችግር ለማቃለልና ለማስወገድ ድርድር አስፈላጊ እንደሆነ ቢታመንም ለአካባቢውና ለመላው ዓለም ሰላምና ደህንነት አስጊ የሆነውን የሽብርተኝነት አውታር መበጣጠስ የሚታለፍ እንዳልሆነ ገልጿል። የቡርኪናፋሶ ፕሬዚዳንት ብሌዝ ኮምፓወሬ ኢኮዋስ በሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት የማሊን ጊዜያዊ መንግሥትና አንሳር ዲኔ የተባለውን ፅንፈኛ ቡድን ተወካዮች በቅርቡ ዋጋዱጉ ውስጥ ማነጋገራቸው ተገልጿል።

ፕሬዚዳንቱ ያነጋገሩት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ታይማን ኩሊባሊ የተመራውን የማሊ ጊዜያዊ መንግሥት ልዑካን ቡድንና አልጋባስ ኢግኢንታላ በተባለው ፅንፈኛ የተመራውን የአንሳር ዲኔ ልዑካን ቡድን እንደሆነ ተገልጿል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ በብሌዝ ኮምፓወሬ አደራዳሪነት የሚካሄደው ውይይት ግን በሰሜናዊ ማሊ ወታደራዊ ዘመቻ ለመክፈት በሚደረገው ዝግጅት ላይ ተፅዕኖ የሚፈጥር እንዳልሆነ የቡርኪና ፋሶው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጂብሪል ባሶል ማመልከታቸውን የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ ማመልከቱ ተገልጿል። ጂብሪል ባሶል አንሳር ዲኔ የተባለው አክራሪ ቡድን ወደውይይት መድረክ እንዲመጣ ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው ታውቋል።