የሶሪያ የተቃዋሚዎች ጥምረት አዲስ መሪ መረጠ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2005 (ዋኢማ) - በኳታር ዋና ከተማ ዶሃ ውስጥ ስብሰባ ሲያካሂዱ የሰነበቱ የሶሪያ ተቃዋሚ ቡድኖች ጥምረት ፈጥረው አዲስ መሪ መምረጣቸው ተገለጸ።

በቢቢሲ ዘገባ መሠረት አዲሱን የተቃዋሚ ቡድኖች ጥምረት እንዲመሩ የተመረጡት ባለፈው ሐምሌ ውስጥ ከደማስቆ በመሸሽ ወደካይሮ የሄዱት የሃይማኖት መሪ ሞአዝ አልካቲብ ናቸው። ሞአዝ አልካቲብ ቀድሞ የደማስቆው ኡማያድ መስጊድ ኢማም እንደነበሩ ተገልጿል። ሱኒ ሙስሊም የሆኑት ሞአዝ አልካቲብ አክራሪ እንዳልሆኑ ተነግሮላቸዋል።

የ52 ዓመቱ ሞአዝ አልካቲብ ቀደም ሲል ከተመረጠውና ጆርጅ ሳብራ በተባሉት ተቃዋሚ ከሚመራው የሶሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጋር ጥምረት የፈጠረውን ስምምነት በፈረሙበት ወቅት ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የራሱን ሕዝብ በመጨ ፍጨፍ ላይ የሚገኘውን የፕሬዚዳንት ባሻር አልአሳድን መንግሥት ለማስወገድ ለሚታገሉት ተቃዋሚ ቡድኖች ድጋፍ ለመስጠት የገባውን ቃል በተግባር እንዲያረጋግጥ መጠየቃቸውን ለኤኤፍፒ በሰጡት መግለጫ ተመልክቷል።

ሰሞኑን ዶሃ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ የተ መሠረተውና ሞአዝ አልካቲብን ፕሬዚዳንት አደርጐ የመረጠው የሶሪያ ተቃዋሚ ቡድኖች ጥምረት ሁለት ምክትል ፕሬዚዳንቶችንም መምረጡ ተገልጿል። እነርሱም ሪያድ ሰይፍ እና ሱሄር አልአታሲ ናቸው። በአዲሱ ጥምረት ውስጥ 60 አባሎች እንደሚገኙበት ተገልጿል።

ጥምረቱ በአሁኑ ጊዜ በሶሪያ ውስጥ ከመንግሥቱ ጦር ኃይሎች ጋር የሚፋለመውን ነፃ ሠራዊት (ፍሪ-አርሚ) ጭምር የሚያካትት አዲስ ወታደራዊ ምክር ቤት እንደሚኖረውም በዘገባው ተመልክቷል። የጥምረቱ ስምምነት ዶሃ ውስጥ በተደረገበት ወቅት የተገኙት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አህሜት ዳቩ ቶግሉ ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ከእዚህ ውጤት በመነሳት ለሶሪያተ ቃዋሚዎች ጥምረት ዕውቅና እንዲሰጥ ጠይቀዋል።

የቀድሞው የደማስቆው ኡማያድ መስጊ ድኢማም ሞአዝ አልካቲብ ሶሪያን ከጥፋት ለማዳን አስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ መፈለግ አስፈላጊ እንደሆነ ባለፈው ወር ማስገንዘባቸው ተገልጿል።

በሶሪያ ጉዳይ ላይ የሚካሄድ ድርድር መንግሥቱን ሊያድን እንደማይችል፣ ነገር ግን የከፋ ጉዳት ሳይደርስበት ከሥልጣን እንዲወገድ ሊያደርግ እንደሚችል የሚገመት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል። የቀድሞው ኢማም ወደካይሮ ከመሰደዳቸው ቀደም ሲል የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት እንዲቆም ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ተነግሮላቸዋል።

ከተጀመረ ሃያ ወራትን ያስቆጠረውና ከ36,000 በላይ ሰዎች ተገድለው ከ700,000 በላይ ሰዎች ለስደት የተዳረጉበትና ሁለት ሚሊዮን ሕዝብ ዕርዳታ ፈላጊ የሆነበት የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት በአገር ውስጥ ሳይወሰን ወደአካባቢው በመዝመት ላይ መሆኑ እየተነገረ ነው።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ በሊባኖስ ውስጥ በሶሪያ መንግሥት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል ተደጋጋሚ ግጭት መካሄዱ ሲገለጽ፣ በቱርክና በሶሪያ ኃይሎች መካከል የተኩስ ልውውጦች መደረጋቸው ታውቋል። ሰሞኑን ደግሞ በሶሪያና በእሥራኤል ኃይሎች መካከል በጐላን ኮረብታ አካባቢ የተኩስ ልውውጥ መካሄዱ ተገልጿል። በሁለቱ አገሮች መካከል የተኩስ ልውውጥ ሲካሄድ እ.እ.አ ከ1973 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደሆነ ታውቋል።