ተመድ ለጓቴማላ ድጋፍ እንደሚሰጥ ዋና ፀሐፊው አስታወቁ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ህዳር 4/2005 (ዋኢማ) - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ለጓቴማላ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚሰጥ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን ማመልከታቸውን ቃል አቀባያቸው አስታወቁ።

የተመድ ዜና ማዕከል ቃል አቀባዩን በመጥቀስ እንደ ገለጸው ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን በጓቴማላ የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ ባደረሰው ጥፋት ማዘናቸውን አመልክተው ድርጅቱ ለሚደረገው የመልሶ ማቋቋም ጥረት አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

በሬክተር መለኪያ 7ነጥብ 4 ኃይል እንደነበረው በተነገረለት የጓቴማላው የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋ 48 ሰዎች ሞተው 150 እንደተጐዱ ሲታወቅ፣ በቤትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመትና ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። የመሬት መንቀጥቀጥ ማዕከሉ ከሜክሲኮ ጋር በሚዋሰነው የባህር ወለል እንደሆነ ታውቋል።

የዋና ፀሐፊ ባን ኪ- ሙን ቃል አቀባይ ኒውዮርክ በሚገኘው የተመድ ዋና መሥሪያ ቤት በሰጡት መግለጫ ድርጅቱ የጓቴማላ መንግሥት ለጀመረው የሰብዓዊ ዕርዳታና የመልሶ ግንባታ እንቅስቃሴ አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ እንደሆነ ዋና ፀሐፊ ማረጋገጣቸውን አስታውቀዋል።

ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን በመሬት መንቀ ጥቀጥ አደጋው ለደረሰው ጥፋትና ጉዳት የተሰማቸውን ኀዘን ለጓቴማላ መንግሥትና ሕዝብ መግለጻቸውንም ቃል አቀባያቸው አረጋግጠዋል።

በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከሁለት ሳምንታት በፊት ሀሪኬን ሳንዲ በሚል ስም የታወቀው ውሃ-አዘል አውሎ ነፋስ ወይም ማዕበል ያደረሰው ጥፋትና ጉዳት ሰለባ የሆነውን ሕዝብ መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ድጋፍ መላኩን የድርጅቱ ዜና ማዕከል ገልጿል። ከበጐ አድራጊዎች ተለግሶ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካይነት ከተላከው ዕርዳታ ውስጥ 40 ቶንስ የሚሆነው ሀሪኬን ሳንዲ ከፍተኛ ጉዳት ወደ አደረሰባት ከተማ ሳንቲያጐ ወደ ኩባ መግባቱ ተገልጿል።

በኩባ የተመድ ዕርዳታ አስተባባሪ ባርባራ ፔሴ ሞንቲየሮ እንዳስታወቁ ለተጐጂዎች በመድረስ ላይ ከሚገኘው ዕርዳታ መካከል ሸራ፣ የውሃ ማጠራቀሚያ፣ የውሃ ማጣሪያ እንክብሎች ፣ የማብሰያና የትምህርት ቤት ዕቃዎች ይገኙባቸዋል።
በበጐ አድራጊዎች ተለግሶ በተመድ አማካይነት የተላከው ዕርዳታ መግባት የጀመረው የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙንና የኩባው ፕሬዚዳንት ፊደል ካስትሮ ሰሞኑን በስልክ ከተነጋገሩ በኋላ እንደሆነም የተመድ ዜና ማዕከል ዘገባ አመልክቷል።

ሀሪኬን ሳንዲ ምሥራቃዊ ኩባን ባለፈው ጥቅምት 11/2012 በመታበት ወቅት 11 ሰዎች ሲሞቱ፣ ሦስት ሚሊዮን ሕዝብ ለጉዳት እንደተዳረገ ተገልጿል። ውሃና አሸዋ አዘሉ ሀሪኬን ሳንዲ ኩባን ፣ሐይቲን፣ የዶሚኒካል ሪፐብሊክን ፣ ሰሜናዊ ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስንና ምሥራቃዊ ካናዳን በመታበት ወቅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ- ሙን ለፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና ለኒውዮርክ ከተማ ካንቲባ ማይክል ብሉምበርግ እንዲሁም ለሌሎች ባለሥልጣኖች ኀዘናቸውን በጽሑፍ መግለጻቸውን ቃል አቀባያቸው አረጋግጠዋል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ የቺሊና የኮሎምቢያ መንግሥታትም ተመድ ለሀሪኬን ሳንዲ ጉዳት ሰለባዎች ዕርዳታ ለማቅረብ በሚያደርገው ጥረት ተባባሪ መሆናቸውን ማስታወቃቸው ተገልጿል። የዓለም የምግብ ፕሮግራምም ለተጐጂዎች ዕርዳታ በመላክ ላይ እንደሆነ ታውቋል።