በስፔን አገር አቋራጭ ውድድር ኢማና መርጋ ግምት አግኝቷል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2005 (ዋኢማ) - የዓለም አገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር አሸናፊው ኢማና መርጋ የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በሚያዘጋጀው የስፔን ሀገር አቋራጭ የሩጫ ውድድር ላይ የአሸናፊነት ቅድመ ግምት ተሰጥቶታል።

የፊታችን እሁድ በሚካሄደው በእዚህ ውድድር አትሌት ኢማና የአሸናፊነት ግምት ቢሰጠውም ከሌሎች ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች ብርቱ ፉክክር ሊገጥመው እንደሚችል ተገምቷል።

በውድድሩ በለንደን ኦሊምፒክና በዴጉ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የአምስት ሺ ሜትር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ደጀን ገብረመስቀል ኢማናን ሊፈትኑት ከሚችሉ አትሌቶች ቀዳሚው ነው።ያለፈው ዓመት የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር የብር ሜዳሊያ አሸናፊው ኬንያዊው ቪንሰንት ቺፕኮክም በውድድሩ ጥሩ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ይገኛል።

ባለፈው መስከረም ወር አካባቢ «ቫንዳም ሚሞሪያል»በተባለው የብራሰልስ የአስር ሺሜትር የሩጫ ውድድር 26፡51፡16 በሆነ ሰዓት ውድድሩን የፈፀመው ኢማኑኤል ቤት የተሰጠው ግምትም ቀላል አይደለም።እ.ኤ.አ በ2010 የዓለም አገር አቋራጭ ውድድር ላይ የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ የነበረው ኤርትራዊው ተክለማርያም መድህንም በውድድሩ ጥሩ ተፎካካሪ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

በዚህ ውድድር ኢማናና ደጀን የሚያደርጉት ፉክክር ከወዲሁ የብዙዎችን ቀልብ የገዛ ሲሆን ሁለቱ አትሌቶች በአንድ ላይ መሮጣቸው ውድድድሩን አጓጊ አድርጎታል።
በተመሳሳይ በሴቶች በሚደረገው ውድድር ኬንያዊቷ ሊኔት ማሳይ የአሸናፊነት ግምት ተሰጥቷታል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የዓለም አገር አቋራጭ ውድድሮችን በመሳተፍ ልምድ ያካበተችው ማሳይ በሦስት ተመሳሳይ ውድድሮች የነሃስ ሜዳሊያ አሸናፊ ነች። እድሜዋ ገና ሃያ ሁለት ከመሆኑና ልምድ ከማካበቷ አኳያ የእሁዱ ውድድር ሊቀላት እንደሚችል ተገምቷል።

በዚህ ውድድር ኢትዮጵያውያኑ አትሌቶችም ጥሩ ግምት ተሰጥቷቸዋል። በተለይ በላይነሽ አልጂራና ህይወት ውዴ ኬንያዊቷን ማሳይ በብርቱ ይፈታተኗታል ተብሎ ተገምቷል።

ባለፈው የለንደን ኦሊምፒክ በአስር ሺ ሜትር አምስተኛ ደረጃን ይዛ ውድድሯን የፈፀመችው አትሌት በላይነሽ እንዲሁም በተመሳሳይ በሦስት ሺ ሜትር መሰናክል በአምስተኛነት ያጠናቀቀችው አትሌት ህይወት ልምድ ካላት ማሳይ አንፃር የተሰጣቸው ግምት ዝቅተኛ ቢሆንም በውድድሩ ሊያሸንፉ የሚችሉበት አጋጣሚ ሊኖር እንደሚችልም ተገምቷል።

የማሳይ የምንጊዜም ተቀናቃኝ የሆነችውና አ.ኤ.አ የ2006ተመሳሳይ ውድድር የነሃስ አሸናፊዋ ፕሪስካህ ጄፕሌቲንግና እንዲሁም ሜርሲ ቼሮኖ በውድድሩ የተሻለ ግምት ከተሰጣቸው አትሌቶች መካከል ይገኛሉ።የቀድሞዋ የአውሮፓ ሻምፒዮን አየርላንዳዊቷ ፊኦናላ ብሪተንና ፖርቹጋላዊቷ ሳራሞሬራ በውድድሩ እንደሚሳተፉና ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር ለ2012 ምርጥ አትሌቶች ምርጫ በዕጩነት ካቀረባቸው ወንድና ሴት አትሌቶች መካከል በሁለቱም ፆታዎች ለመጨረሻው ውድድር ያለፉትን ሦስት ሦስት አትሌቶች ስም በድረ-ገጹ ይፋ አድርጓል።

በዚህም መሠረት በወንዶች ጃማይካዊው የ100 እና የ200 ሜትሮች የዓለምና የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ዩሴን ቦልት፣ አሜሪካዊው የ110 ሜትር መሠናክል የዓለም ክብረወሠን ባለቤት አሪስ ሜሪት እና ኬንያዊው የስምንት መቶ ሜትር የዓለምና የኦሊምፒከ ሻምፒዮን ዴቪድ ሩዲሻ በወንዶች ለመጨረሻው ምርጫ የሚፎካከሩ አትሌቶች ሆነዋል።

በሴቶች በኩል ሲካሄድ በሰነበተው ተመሳሳይ ምርጫም በአሎሎ ውርወራ የሁለት ኦሊምፒኮች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ኒውዚላንዳዊቷ ቫለሪ አዳምስ፣ እንግሊዛዊቷ የ100 ሜትር መሠናክል የወቅቱ የኦሊምፒክ ሻምፒዮን ጄሲካ ኤኒስ እና አሜሪካዊቷ የ 200 ሜትር የዓለምና የኦሊምፒክ ሻምፒዮኗ አሊሰን ፌሊክስ ለመጨረሻው ምርጫ የቀረቡ ሦስቱ ሴት አትሌቶች ሆነዋል።

የምርጫው ሂደት ለ20ቀናት ሲካሄድ ከቆየ በኋላ የታወቁት እነዚህ ዕጩ አትሌቶች ለመጨረሻው ዙር የደረሱት በዓለም ዙሪያ ካሉ ሁለት ሺ አራት መቶ ተመልካቾችና በዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማህበር አባል ፌዴሬሽኖች፣ በማህበሩ ኮሚቴና ኮሚሽን አባላት በታዋቂ የአትሌቶች ተወካዮች፣ ታዋቂ ዓለም አቀፍ አትሌቶችና በተመረጡ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችና በማህበሩ ስታፍ አባላት ከተሰበሰበው ድምጽ አብላጫውን በማግኘታቸው ነው።

እያንዳንዱ ድምጽ ሰጪ ለአንድ ወንድና ለአንድ ሴት አትሌቶች ብቻ ድምጽ የሰጠ ሲሆን፤ የ2012 ምርጥ አትሌትነት ምርጫን የሚያሸንፉ አትሌቶች የፊታችን ኅዳር 15 ቀን 2005 ዓ.ም በባርሴሎና ከማህበሩ 100ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ በሚደረግ ሥነ-ሥርዓት ሽልማታቸውን የሚቀበሉ ይሆናል።

በተያያዘ የአትሌቲክስ ዜና የዓለም አቀፉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ትናንት በተለያዩ ርቀቶች በህጋዊነት የተመዘገቡ አዳዲስ የዓለም ክብረ ወሰኖችን ይፋ አድርጓል። ከእነዚህም መካከል ኬንያዊው ዴቪድ ሩዲሻ በስምንት መቶ ሜትር ለንደን ኦሊምፒክ ላይ ያስመዘገበው 1፡40፡91 ዋነኛው ነው።በዚህ ርቀት ቀደም ሲል ተይዞ የነበረው ክብረወሰንም በራሱ በሩዲሻ 1፡41፡01 ነበር።

በአራት መቶ ሜትር የዱላ ቅብብል ለንደንላይ ጃማይካዎቹ ኔስታ ካርተር፤ሚካኤል ፍራተር፤ዮሃን ብሌክና ዩሴን ቦልት በጋራ ያስመዘገቡት 36፡84 ሰዓት ከተመዘገቡት ክብረወሰኖች መካከል ይገኛል።በዚህ ርቀት ቀደም ሲል ተይዞ የነበረው ክብረወሰን ኮሪያ ዴጉ ላይ የተመዘገበው 37፡04 የሆነ ሰዓት ነው።

ሌላው ክብረወሰን በሴቶች አራት መቶ ሜትር ዱላ ቅብብል አሜሪካና ለንደን ላይ ቲና፤ማዲሰን አይሰን ፌሊክስ፤ ቢያንካ ናይትና ካርሜሊታ ጂተር ያስመዘገቡት 40፡82 ሰዓት አንዱ ነው። በዚህ ርቀት ቀደም ሲል ተመዝግቦ የነበረው ክብረ ወሰን ጀርመን ላይ የተመዘገበው 41፡37 ሰዓት ነበር።

በሃያ ኪሎ ሜትር እርምጃ ለንደን ላይ ኢሌና ላሽማኖቫ ያስመዘገበችው 1፡25፡02 ሰዓት አለም አቀፉ ፌዴሬሽን ከመዘገበው አዳዲስ ክብር ወሰኖች ውስጥ ይገኛል። በዚህ ርቀት ቀደም ሲል ተመዝግቦ የነበረው ክብረ ወሰን ሩሲያ ላይ ቬራ ሶኮሎቫ ያስመዘገበችው 1፡25፡08 ሰዓት ነው።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ በወጣቶች ስምንት መቶ ሜትር ኒጄል አሞስ ያስመዘገበው 1፡41፡73 ሰዓት በክብር ወሰንነት ተይዟል።በዚህ ርቀት ቀደም ሲል ተመዝግቦ የቆየው ሱዳናዊው አቡበከር ካኪ ኦስሎ ላይ ያስመዘገበው 1፡42፡69 ሰዓት ነበር።