የቻይና ኩባንያ ከብሪታኒያው ሂትሮው አክሲዮን ገዛ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2005 (ዋኢማ) - የቻይና ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ( ሲአይሲ) የለንደኑ ሂትሮው ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣቢያ ባለቤት ከሆነው ኩባንያ የአሥር በመቶ ድርሻ ያለው አክሲዮን መግዛቱን ዘገባዎች አመለከቱ። የቻይና ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን ከአገሪቱን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ክምችት (ፎሪን- ኤክስጀንድ ሪዘርቭስ)ከፊሉን በውጭ ኢንቨስትመንት ላይ እንዲያውል ታቅዶ እ.አ.አ በ2007 የተቋቋመ ኩባንያ እንደሆነ ታውቋል።

የቻይና ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን «ሂትሮው ኤርፖርት ሆልዲንግስ ሊሚትድ» ከተባለው ኩባንያ ለገዛው የአሥር በመቶ ድርሻ ወይም አክሲዮን 450 ሚሊዮን ፓውንድ (726 ሚሊዮን ዶላር) እንደሚከፍል ተገልጿል። የቻይና ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን (726) በብሪታኒያ ውስጥ በመሠረተ ልማት ፕሮጀክት ኢንቨስትመንት ሲሳተፍ ይህ ሁለተኛው እንደሆነ ታውቋል። ሲአይሲ እ.አ.አ ጥር 2012 የቴምስ ወንዝ ልማት ፕሮጀክትን ከሚያካሂደው ኩባንያ የ8.68 በመቶ ድርሻ ያለው አክሲዮን መግዛቱ ታውቋል።

የሂትሮው ኩባንያ በለንደኑ ስታንሴድ፣ በሳውዝሃምፕተኑ፣ በሳዘርን ኢግላንድና በስኮትላንዶቹ ግላስጐው አበርዲን አውሮፕላን ጣቢያዎች አክሲዮን እንዳለው ታውቋል። የቻይና ኢንቨስትመንት ኮርፖሬሽን በብሪታኒያ የሚፈጽመውን የአክሲዮን ግዢ አንዳንድ ወገኖች መቃወማቸው ተገልጿል።

ባለፈው ወር የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሮልስ ኮርፖሬሽን የተባለው የቻይና ኩባንያ በአሜሪካ ውስጥ ከነፋስ ኃይል ለማመንጨት በሚያስችል ኢንቨስትመንት ለመሳተፍ ያወጣውን ዕቅድ ከደህንነት ጋር በተያያዘ ሁኔታ ውድቅ ማድረጋቸው ተገልጿል። አሜሪካ ሁዋዊ እና ዜድቴኢ የተባሉት የቻይና ኩባንያዎች ለአሜሪካ ደህንነት አስጊ በመሆናቸው የአገሪቱ ኩባንያዎች ከእነዚህ ተቋማት ጋር ስምምነት እንዳያደርጉ ማስጠንቀቃቸው ታውቋል። አውስትራሊያም ሁዋዊ የተባለው የቻይና ኩባንያ በአገሪቱ ብሔራዊ ብሮድባንድ ኔትወርክ ለመሳተፍ ያቀረበውን ጥያቄ ውድቅ
ማድረጓ ተገልጿል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ በሌሎች አገሮች እነዚህ ሁኔታዎች ቢስተዋሉም በብሪታኒያና በቻይና ኩባንያዎች መካከል የኢንቨስትመንት ግንኙት እያደገ በመምጣት ላይ እንደሆነ ታውቋል።