በኪሲማዮ 400 ተጠርጣሪ የአልሸባብ ደጋፊዎች ተያዙ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 30/2005 (ዋኢማ) - ባለፈው ወር በአፍሪካ ኅብረት የሶማሊያ ተልዕኮ ወታደሮችና በሶማሊያ መንግሥት ጦር ሠራዊት ከአሸባሪው ቡድን አልሸባብ ቁጥጥር ነፃ በወጣችው ቁልፍ የወደብ ከተማ ኪስማዮ ውስጥ በዚሁ ቡድን ደጋፊነት የተጠረጠሩ 400 ሰዎች መያዛቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመለከተ። እነዚህ ተጠርጣ ሪዎች በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰሞኑን በከተማዋ ውስጥ በፀጥታ ኃይሎች በተካሄደ ከፍተኛ አሰሳ አማካይነት እንደሆነ ተገልጿል።

አንድ የሶማሊያ ሚሊሺያ ኃይል አባል ለቢቢሲ በሰጠው መግለጫ በሰሞኑ አሰሳ በቁጥጥር ሥር የዋሉት 400 ሰዎች ከአል-ቃይዳ ጋር ግንኙነት ያለው አሸባሪ ቡድን አልሸባብ ደጋፊዎች እንደሆኑ የተጠረጠሩ መሆናቸውን አረጋግጧል። በዚሁ የሶማሊያ ሚሊሽያ ኃይል አባል መግለጫ መሠረት አልሸባብ በአፍሪካ ኅብረት ወታደሮችና የሶማሊያ መንግሥት ጦር ሠራዊት ወታ ደራዊ እርምጃ ባለፈው ወር ከኪስማዮ ከተባረረ በኋላ በከተማዋ ውስጥ ተደጋጋሚ የፈንጂ አደጋዎች መፈፀማቸው አልቀረም።

ባለፈው ማክሰኞ በኪስማዮ ከተማ ማዕከላዊ ክፍል በሚገኝ አንድ ሆቴል አጠገብ በተፈፀመ የፈንጂ አደጋ አራት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸው በቢቢሲ ዘገባ ተመልክ ቷል። የራስ ካምቦኒ ሚሊሽያ ኃይል ቃል አቀባይ አብዲናስር ሠራር እንዳረጋገጠው በኪስማዮ ከተማ ከፍተኛ አሰሳ ተካሂዶ 400 በአልሸባብ ደጋፊነት የተጠረጠሩ ሰዎች በቁጥጥር የዋሉት ከተጠቀሰው አደጋ በኋላ በተወሰደ የአሰሳ እርምጃ ነው። በቃል አቀባዩ መግለጫ መሠረት አልሸባብ ኪስማዮን ለቅቆ እንዲወጣ ከተገደበበት ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች በተፈፀሙ የፈንጂ አደጋዎች 20 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል።

በአፍሪካ ሰላም አስከባሪ ኃይልና የሶማሊያ መንግሥት የመከላከያ ኃይሎች በወሰዱትና በመውሰድ ላይ ባሉት ወታደራዊ እርምጃ የሚቆጣጠራቸው አካባቢዎች እየተጠበቡትና ተሰሚነትም እያጣ የመጣው የሶማሊያ አሸባሪ ድርጅት አልሸባብ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ በቀቢፀ-ተስፋ ዓላማውን የሚቃወሙና የሚነቅፉ ታዋቂ ሰዎችን መግደሉ ቀደም ሲልም በቢቢሲ ዘገባ ተመልክቷል።

የአልሸባብ ታጣቂዎች በቅርቡ ታዋቂውን የኪነ-ጥበብ ባለሙያ ዋርሰሜ ሺሬ አዋሬን፣ ገድለዋል። ከእርሱ በፊትም ሞሐመድ ሞሐሙድ ቱሪያሬ የተባለውን የሸብሌ ራዲዮ ጋዜጠኛ መግደላቸው ተገልጿል።

የአልሸባብ ታጣቂዎች በዚህ ዓመት ብቻ 18 ጋዜጠኞችን መግደላቸው ታውቋል።

የአልሸባብ ተዋጊዎች ባለፈው እሁድ አንድ የሶማሊያ ጀኔራል መግደላቸው ተገልጿል።

ያደፈጡ የአልሸባብ ተዋጊዎች ሞሐመድ ኢብራሂም ፋራህ የተባሉትን ጀኔራል ከሌሎች አራት ወታደሮች ጋር የገደሉት በደቡባዊ ሶማሊያ ታችኛው ሸበሌ በተባለው አካባቢ በምትገኘው መርጣ ከተማ አቅራቢያ እንደሆነ ተገልጿል። መርጣ ከአልሸባብ ቁጥጥር ነፃ የሆነችው ባለፈው ነሐሴ ውስጥ እንደሆነ ታውቋል።

በሌላ በኩል የኪስማዮ ነጋዴዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አልሸባብ ከተማዋን ተቆጣጥሮ በቆየበት ወቅት የጣለውን የከሰል ንግድ ዕገዳ እንዲያነሳ መጠየቃቸውን የቢቢሲ ዘገባ አመልክቷል።

ኪስማዮ የአልሸባብ ከሕገወጥ ንግድ የሚገኝ ከፍተኛ ገቢና የጦር መሥሪያ ምንጭ ሆና መቆየቷ ይታወቃል።

ድርጅቱ የአልሸባብን የገቢ ምንጭ ለማድረቅ የጣለው የከሰል ንግድ ዕገዳ በአሸባሪው ቡድን ላይ ተፅዕኖ ቢያሳርፍም ከሰል ወደሳዑዲ አረቢያ፣ ወደዩናይትድ ዓረብ ኢሚሬትስና ወደ ሌሎችም የአካባቢው አገሮች ከመላክ እንዳልቆመ በአንድ የተመድ ሪፖርት መገለጹ ታውቋል። በኪስማዮ ውስጥ ታዋቂ የከሰል ነጋዴ እንደሆነ የተነገረለት ሙሐመድ አብዱላሂ የተባለ ነጋዴ የከሰል ወጪ ንግድ መቀነስና መቆም ኪሣራ ያስከተለበት መሆኑን ማመልከቱ ተገል ጿል።

እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ ተመድ በኪስማዮ ከሰል ወጪ ንግድ ላይ ዕገዳ መጣሉ በከተማዋ ውስጥ ከፍተኛ የከሰል ክምችት እንዲፈጠር አድርጓል። ከዚህ ሁኔታ በመነሳትም የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት ለዚህ ችግር መፍትሔ የሚሆን ውሳኔ እንዲያሳልፍ የአፍሪካ ኅብረት በቅርቡ ማሳሰቢያ መስጠቱን በቢቢሲ ዘገባ ተመልክቷል።