የኢህአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መደበኛ ስብሰባ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቀቀ

  • PDF

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ጥቅምት 24/2005 የጀመረውን መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት የተለያዩ ውሳኔዎችን በማሳለፍ አጠናቋል፡፡ የክልሎችን የ2004 ዕቅድ አፈፃፀም ማጠቃለያና የ2005  ዕቅድ ዝግጅትና ፈፃሚ ማዘጋጀት ሥራዎችን በመፈተሸ ስብሰባውን የጀመረው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ባለፈው ዓመት የገጠር ልማትን በተመለከተ በተፋሰስ፣ በመስኖና በሰብል ልማት ሥራዎች አፈፃፀም የነበረው አንፃራዊ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በሁሉም ክልሎች የተሻለ እንቅስቃሴና ውጤት መታየቱን አረጋግጧል፡፡ ይኸው አበረታች እንቅስቃሴ በ2005 የአርሶ አደሩን ምርታማናትና አጠቃላይ ሀገራዊ ምርትን ለማሳደግ ለሚደረገው ርብርብ አወንታዊ ድርሻ እንዳለው ገምግሟል፡፡

በማህበራዊ ልማት ዘርፍም በተለይም የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረጉንና በወላጅ፣ በመምህራንና በተማሪዎች የተደራጀ ጥረት አመርቂ ውጤት መታየቱን አረጋግጧል፡፡ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራሙን በሰፊ የህዝብ ተሳትፎ በማስፋፋት የእናቶችና ህፃናትን ሞት ለመቀነስና በአጠቃላይ ጤንነቱ የተጠበቀ ህብረተሰብ በመገንባት የጀመርነውን ፈጣን ዕድገትና የሀገሪቱን ህዳሴ ለማስቀጠል በተለይ የሴቶች አደረጃጀቶች ላይ ተመስርቶ የተደረገው ጥረት ከፍተኛ ውጤት በማሳየቱ በሁሉም ክልሎች የተገኙትን ልምዶች በመቀመር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥቶ መክሮበታል፡፡

ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ በገጠሩ የተሻለ ሁኔታ መኖሩን የገመገመው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የተገኘውን ለውጥ መሠረት በማድረግና የተጀመረውን የህዝቡን ልማታዊ እንቅስቃሴ በማጠናከር በህዝቡ በራሱ ተሳትፎ አልፎ አልፎ የሚገጥሙ ችግሮችን ማስወገድ የሚችልበት ሁኔታ መፈጠሩን በመገምገም ከስምምነት ላይ ደርሷል፡፡

የከተማ ሥራዎችን በተመለከተ በዋነኝነት የከተማውን ነዋሪ የገቢ አቅም ለማሳደግ የተካሄደው የሥራ ዕድል ፈጠራና የጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ልማት በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ከተቀመጠው ግብ አንፃር አበረታች ርቀት የተሄደበት መሆኑንና ይኸው ሥራ በ2005ትም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስቧል፡፡ በመልካም አስተዳደር ያሉትን ሁኔታዎች በመፈተሸም በተለይ ባለፈው ዓመት ተጀምሮ የነበረው በሁሉም ክልሎች ከነዋሪው ጋር በችግሮችና መፍትሔዎች ዙሪያ በምልልስ ይደረግ የነበረው ህዝቡን ያሳተፈ የማጥራትና የመልካም አስተዳደር ማስፈን እንቅስቃሴ በያዝነው ዓመትም የሲቪል ሰርቪስና የፍትህ ሥርዓት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን በተጠናከረ ሁኔታ ለመተግበር ከሚደረገው ጥረት በተጨማሪ በየወቅቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለማስወገድ የተጀመረውን የህዝቡን ተሳትፎ ቀጣይነት በማረጋገጥ ትርጉም ያለው መሻሻል ለማምጣት በሚቻልባቸው አቅጣጫዎች ዙሪያ አፅንኦት ሰጥቶ ተወያይቷል፡፡

የ2004 ልምዶችን በመቀመር በያዝነው ዓመት በሰፊ የህዝብ ንቅናቄ በገጠርና በከተማ ልማት ሥራዎች በዕድገትና ትራስፎርሽን ዕቅዱ የተቀመጠውን የተለጠጠ ግብ ለማሳካት ወሳኝ የሆነውን ፈፃሚን የማዘጋጀት ሥራ በተቀመጠለት አቅጣጫ መሠረት ወደተግባር እየተሸጋገረ መሆኑን የገመገመው ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የዝግጅት ሥራዎቹ በሁሉም ክልሎች በፍጥነት ተጠናቀው ያለፈውን ክረምት ሥራዎች በማጠቃለል የበጋው ሥራ እንዲጀመር አሳስቧል፡፡ የድርጅቱ አባላትና ህዝቡ በታላቁ መሪና እርሱም በሚመራው ኢህአዴግ የተጀመረውን የህዳሴና የብልፅግና ጉዞ በየተሰማራበት ሁሉ አጠናክሮ ለመቀጠል ያሳየው ተነሳሽነትና ቁጭት ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ግብአት በመሆኑ የዝግጅት ሥራው ይኽንኑ ታሳቢ አድርጎ እየተካሄደ መሆኑን በማረጋገጥ በዚሁ ግለት መቀጠል እንዳለበት ስምምነት ላይ ደርሷለ፡፡

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በሌላ አጀንዳ ስር የአካባቢና የማሟያ ምርጫ እና የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባላት ምርጫ ዝግጅትን የገመገመ ሲሆን ምርጫው ሰላማዊ፣ ነፃና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚደረግ አረጋግጧል፡፡ ከዚህ በፊት ፓርቲው በህግ ከተደነገገው የፓርቲዎች የስነ-ምግባር ህግ እና ሌሎች የምርጫ ህጎች በተጨማሪ አባላቱ የሚገዙበትን  የስነ-ምግባር መመሪያ በማውጣት አርአያነቱን ለማረጋገጥ የተንቀሳቀሰ ሲሆን በዚህ ምርጫም ይህንኑ አጠናክሮ እንደሚቀጥል እና ከፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት ጋር በመመካከር ባለፉት ዓመታት የተጀመረውን ችግሮችን በጋራ ተወያይቶ የመፍታት እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንደሚገፋበት በማረጋገጥ በድርጅት ደረጃ የምርጫውን ሥራ በማዕከልና በየደረጃው የሚያስተባብሩ ኮሚቴዎች አደረጃጀት ላይ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በያዝነው ዓመት የሚካሄደውን 9ኛውን የግንባሩን ድርጅታዊ ጉባኤ ዝግጅቶችንም ገምግሟል፡፡ 9ኛው ጉባኤ የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እኩሌታ አፈፃፀም የሚፈተሸበትና የቀጣይ ዓመታት አቅጣጫ የሚቀመጥበት ከመሆኑም ባሻገር በታላቁ መሪ ቀያሽነት የተጀመረው የድርጅቱ የተሃድሶ እንቅስቃሴ በተቀጣጠለባቸው ባለፉት 12 ዓመታት የሀገራችንን ህዳሴ በማፋጠን የተደረሰበት ደረጃ የሚቃኝበት በመሆኑ ከወዲሁ የተጀመሩት የዝግጅት ሥራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ በማሳሰብ የዝግጅት ኮሚቴው በሰው ኃይል የሚጠናከርበትን አቅጣጫ በማስቀመጥ እና ከቤቱ በቀረቡ ሌሎችም አጀንዳዎች ዙሪያ በሰፊው በመምከር መደበኛ ስብሰባውን ዛሬ ከሰዓት በኋላ አጠናቋል፡፡