የአዲስ አበባ ከተማ 125ኛ ዓመት በዓልን አስመልክቶ የሩጫ ውድድር ተካሄደ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 23/2005 (ዋኢማ) -  “ለአዲስ ለውጥ በአዲስ መንፈስ” በሚል መሪ ቃል የአዲስ አበባን 125ኛ በዓል አስመልክቶ መነሻና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ያደረገ የ10 ኪሜ የሩጫ ውድር ተካሄዷል።

ሩጫው በርካታ የከተማ ነዋሪዎችን ያሳተፈ ሆኗል።ከህጻናት እስከ ወጣቶች ከታዳጊ እስከ አዛውንቶች በሁሉም የእድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ የከተማ ነዋሪዎች በሩጫው ተሳታፊ ሆነዋል።

በርካቶችም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ራዕይ እናሳካለን የሚሉ መፈክሮችን አንግበዋል።

በመደበኛ አትሌቶች በተካሄደው ውድድር በወንዶች ባይሳ ጢቄሳ በሴቶች ደግሞ ሩት ያጋ አሸናፊ ሆነዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች በጋራ ከመሮጣቸው በፊት በተደረገው የመደበኛ አትሌቶች ውድድር በወንዶች ባይሳ ጢቄሳ ከመከላከያ፣ያዕቆብ ጃርሶ ከፌደራል ማረሚያ ቤት፣ ይሳ ባልዳ ከጌታ ዘሩ ከአንደኛ እስከ ሶስተኛ በመውጣት አሸናፊ ሆነዋል።

በሴቶች ሩት ያጋ ከፌደራል ማረሚያ ቤት አንደኛ፣አለምፍቅር ከጌታ ዘሩ ሁለተኛ፣ አለሚቱ አሮጌ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሶስተኛ በመሆን አጠናቀዋል።
እንደ ኢሬቴድ ዘገባ የዕለቱ የክብር እንግዳ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ ለአሸናፊዎች ዋንጫ እና ሜዳሊያዎችን አበርክተዋል።