ለካንሰር በሽታዎች ሕክምና የሚያገለግሉ መሳሪያዎች ወደ አገር ውስጥ እየገቡ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤  ጥቅምት 21/2005 (ዋኢማ) -  የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ለጡትና ለተለያዩ የካንሰር በሽታዎች ሕክምና የሚያገለግሉ ዘመናዊ መሳሪያዎችን በመግዛት ወደ አገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን አስታወቀ ፡፡ ዓለም አቀፍ የጡት ካንሰር ግንዛቤ ማስጨበጫ የእግር ጉዞ አዲስ አበባ ውስጥ ተካሄዷል፡፡

በግንዛቤ ማስጨበጫና በእግር ጉዞ ፕሮግራሙ ዛሬ ሲካሄድ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኃላፊ ፥ አቶ አህመድ ኢማኖ እንደተናገሩት የዚህ ዓመት ዋና ዕቅድ የጨረር ህክምናን በአገሪቱ ማስፋፋት ነው፡፡

መንግስት ሲቲስካንና ሜሞግራፊ የተባሉ መሳሪያዎችን ጨምሮ የተለያዩ የጨረር ሕክምና መገልገያ መሳሪዎችን ፥ በአሁኑ ወቅት እየገዛና ወደ አገር ውስጥ እያስገባ መሆኑን ገልጸው በዘርፉ የሚያገለግሉ 60 ከፍተኛ ባለሙያዎችን እያሰለጠነ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ካንሰርን ጨምሮ የተለያዩ የሕክምና አግልገሎት የሚሰጡ የሆስፒታሎች ቁጥር እያደገ መምጣቱን ጠቅሰው ፥ ቀድሞ 72 የነበረው የሆስፒታል አሃዝ በአሁኑ ወቅት ከ200 በላይ ማደጉንና የአገልግሎት ጥራት ማሻሻያም መደረጉን አስታውቀዋል፡፡

ከሆስፒታሎች በተጨማሪ ተላላፊና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን በየቀበሌው ለመከላከል 15 ሺህ 95 በላይ የጤና ኬላዎች ፥ እንዲሁም ከ2 ሺህ 850 በላይ የጤና ጣቢያዎች በመላ አገሪቱ መቋቋማቸውንም አስረድተዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ከካንሰር ማህበራት ጋር በሽታውን በመከላከልና የሕክምና አገልግሎት አድማስን በማስፋት ረገድ ፥ ወደፊትም ተባብሮ እንደሚሰራም በስነ ስርዓቱ ላይ ቃል ገብተዋል፡፡

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ፣ የኢትዮጵያ ካንሰር አሶሴሽንና ካንስር ኬር ኢትዮጵያ ከሌሎች አጋሮች ጋር ባዘጋጁት የእግር ጉዞ ላይ ቁጥሩ አንድ ሺህ በላይ ህዝብ ተሳታፊ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡