ኮርፖሬሽኑ በሶስት ስኳር ፋብሪካዎች የካይዘን የስራ አመራርን ተግባራዊ ሊያደርግ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ጥቅምት 1/2005 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን በወንጂ፣ መተሃራና ፊንጫ ስኳር ፋብሪካዎች የካይዘን የሥራ አመራርን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑ ተገለፀ።

በሚኒስትር ማዕረግ የኮርፖሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይ  ፀሃዬ  ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል ዘርፉን ወደ ምርታማነትና ተወዳዳሪነት ለማሸጋገር የሚያስችል የከፍተኛና መካከለኛ አመራር አባላት የውይይት መድረክ በተከፈተበት ወቅት እንደተናገሩት፤   የካይዘን አሰራር በመላው አለም በስፋት ጥቅም ላይ ከዋለ ወዲህ በርካታ  ኮርፖሬሽኖች ወጪን በመቀነስና ጥራትን በማሻሻል ተወዳዳሪነታቸውን  እንዲጨምሩ አስችሏል።

ኮርፖሬሽኑ ቀደም ባሉት ጊዜያት የካይዘን የስራ አመራርን በሙከራ ደረጃ ተግባራዊ አድርጎ እንደነበር ጠቁመው፤ አሁን ግን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ በማድረግ ዘርፉን በአጭር ጊዜ ወደ ተወዳዳሪነት ለማሸጋገር ታቅዷል ብለዋል።

የስኳር  ዘርፉ  ለአገሪቱ ፈርጀ ብዙ  ጥቅም  የሚሰጥ  መሆኑን  የጠቆሙት  አቶ አባይ  መንግሥት ልዩ  ትኩረት  ሰጥቶት በመሥራት  ላይ  እንደሚገኝ አመልክተዋል።

በወንጂ፣ በመተሃራና በፊንጫ ነባር የስኳር ፋብሪካዎች ላይ የካይዘን የስራ አመራር ትግበራ እንዲጀመር ማድረግ ለሌሎች በግንባታ ላይ ለሚገኙ አዳዲስ የስኳር   ፋብሪካዎች በምሳሌነት ያገለግላል ያሉት አቶ አባይ የካይዘን  አሰራር የስኳር  ልማቱን በማፋጠን፣ ወጪን በመቀነስና ምርታማነትን በማሳደግ ዘርፉን በአለም አቀፍ  ደረጃ ተወዳዳሪ  ለማድረግ ያስችላል ብለዋል።

የሶስቱ ነባር ፋብሪካዎች የካይዘን ቡድን መሪዎች ለተወያዮች እንደገለጹት፤   በየፋብሪካዎቻቸው የትግበራ ሥራ መጀመሩ ለዘርፉ ውጤታማነት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።


በተመሳሳይም   የመተሃራ  ስኳር ፋብሪካ  ሥራ  አስኪያጅ አቶ  ብዙነህ  አሰፋ ፤ የወንጂ  ስኳር  ፋብሪካ  ሥራ  አስኪያጅ  አቶ  መካሻ  ቀጥይበሉ እንዲሁም  በፊንጫ  ስኳር ፋብሪካ የእርሻ ሥራዎች ስራ አስኪያጅ  አቶ ነሚ ገለታ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ ተግባራዊ የተደረገው የካይዘን አሰራር ብክነትን በመከላከልና  ወጪ ቆጣቢ አሰራርን በማስተዋወቅ ምርታማነትን በተጨባጭ መጨመር ያስችላል ሲሉ ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ  ካይዘን  ኢንስቲትዩት ዳይሬክተር  አቶ ታደሰ ጌታሁን  በበኩላቸው፤ አሰራሩ ምርትና ምርታማነትን ከማሳደጉም በላይ የሰራተኛውን  ሁለንተናዊ  አቅምና ብስለት የሚያጎለብት ነው ብለዋል ፡፡  

እንደ አቶ ጌታሁን ገለጻ፤ የኢትዮጵያ ስኳር ፕሮጀክቶች ሁሉንም ክልሎች  የሚያማክል በመሆኑ የካይዘን የሥራ ፍልስፍናን  በቀላሉ  በመላ  ሃገሪቷ  ለማዳረስ  ይቻላል ሲሉም ገልፀዋል።

አንዳንድ የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው፤ የካይዘን አሰራርን በየፋብሪካዎቻቸው   ተግባራዊ ማድረጉ ምርታማነታቸውን ሊያሻሽለው እንደሚችል ጠቁመው፤ ይህም ለሰራተኛው ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትና እድገት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው መናገራቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።