በኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ ስልክ ብዛት ኬንያን ልትበልጥ ትችላለች

  • PDF

ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመታት በኋላ በተንቀሳቃሽ ስልክ ደንበኞች ብዛት ኬንያን ልትበልጥ እንደምትችል አንድ ጥናት አመለከተ።

በደቡብ አፍሪካ የሚገኝ ተቋም ያደረገው ጥናት እንዳስታወቀው በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የተንቀሳቃሽ ስልክ ያላት ኬንያ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2014 በኢትዮጵያ የምትበልጥበት አዝማሚያ እየታየ ነው።

''ምንም እንኳን ኬንያ በአውሮፓውያኑ 2012 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት በከፍተኛ የተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥር ገበያውን በ28ሚሊዮን ደንበኞች ብትቆጣጠረውም፤እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2010 የነበረው የደንበኞች ቁጥር ከ34 በመቶ ወደ 29 በመቶ ቀንሷል። በአንጻሩ የኢትዮጵያ ገበያ በከፍተኛ ደረጃ ደርቷል'' ሲል ያብራራል።

ኢትዮጵያ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት 173 በመቶ በማስመዝገብ ከፍተኛ ውጤት ማግኘቷንም ዘገባው ያስረዳል።

ቡሩንዲ በ43 በመቶ፣ ሩዋንዳ በ31በመቶ፣ ዑጋንዳ በ23 በመቶ ዕድገት ሲያስመዘግቡ ኬንያ ዕድገቷ 15 በመቶ በመሆኑ ከክፍለ አህጉሩ አማካይ እንኳን በግማሽ ያህል ወደ ኋላ መቅረቷን ጥናቱ ይገልጻል።

የምሥራቅ አፍሪካ የቴሌኮሙኒኬሽን ገበያ በተንቀሳቃሽ ስልክ ሥር መውደቁንና ከጠቅላላውም ተገልጋዮች 98 በመቶው የስልኩ ባለቤቶች መሆናቸውን የተቋሙ ከፍተኛ ባለሙያ ቴክላ ምቡንጉ ተናግረዋል።

በክፍለ አህጉሩ በሩብ ዓመቱ ከ100 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ይሁንና ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ሕዝብ 60 ከመቶው የተንቀሳቃሽ ስልክ አገልግሎት ተጠቃሚ ያለመሆኑንና በኢትዮጵያም አገልግሎቱን ለማዳረስ ሰፊ እንቅስቃሴ መደረግ እንዳለበት ባለሙያው ገልጸዋል።

በምሥራቅ አፍሪካ በጠቅላላ የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሽፋን ኬንያ 67 በመቶ በመያዝ ቀዳሚ ስትሆን፣ ታንዛንያ፣ ዑጋንዳ፣ ቡሩንዲና ኢትዮጵያ ተከታዮቹን ደረጃዎች መያዛቸውን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።