አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለመሃላ ፈጽሙ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2004 (ዋኢማ) - አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ቃለመሃላ ሲፈጽሙ አቶ ደመቀ መኮንንም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሹመዋል።
የኢህአዴግ ምክትል ሊቀመንበርና የትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን ኢህአዴግ ለምን አቶ ሃይለማሪያምን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት እጩነት እንዳቀረበ ሲገልጹ በ2003 ዓ/ም የተጀመረው የመተካካት መርህ መሰረት በማድረግና የአሰራር ደንቡ በሚፈቅደው መሰረት መሆነን ገልጸዋል።
አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በእንጂነሪንግና በአመራር ሳይንስ ሁለተኛ ድግሪ እንዳላቸው ያስታወሱት አቶ ደመቀ ከዩኒቨርስቲ ዲን እስከ ከፍተኛ የመንግስት የሃላፊነት ቦታ ሲያገለግል እንደነበርም ተናግረዋል።
አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንትነት፣ በደቡብ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት በምክትል ርዕሰመስተዳድርነትና በርዕሰ መስተዳድርነት ማገልገላቸውንም አቶ ደመቀ አስረድተዋል።
አቶ ደመቀ አያይዘውም በተለይ በ2000 ዓ/ም በተደረገው ምርጫ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ከታላቁ የኢትዮጵያ መሪ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በቅርበት ልምድን ቀስመዋል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ከቃለመሃላ በኋላ ባደረጉት ንግግር እንዳስታወቁት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ራዕይ ዳር ለማድረስ ጠንክረን እንሰራለን ነበር ያሉት።
በአገራችን በታላቁ መሪ የተጀመሩትን የሰላም፣ የዴሞክራሲና የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ይደረጋልም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አያይዘውም የታላቁ መሪ የክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ጅምር የሆነው የአምስት አመቱ የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ አካል የታላቁ ህዳሴ ግድ በታቀደለት ጊዜ ከተቻለም ከዚያ ባነሰ ወቅት ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ ተናግረዋል።
አርሶና አርብቶ አደሩ ዘመናዊ የእርሻ አመራረት ዘዴ ተጠቃሚ እንዲሆንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችል አሰራር እንዲከተል እየተደረገ ያለው የግብርና መር የልማት እንቅስቃሴም እንደሚጠናከር ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሪያም ደሳለኝ ገልጸዋል።
አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ አያይዘውም በተለይ ለልማታችን እንቅፋት የሚሆነውን የኪራይ ሰብሳቢነትንና ሙስናን በተቀናጀ መንገድ በመታገል ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ ፈጣን አሰራር ይዘረጋል ብለዋል።
በትምህርት ዘርፍ ለሳይንስና ለሂሳብ ትምህርቶች ትኩረት እንደሚሰጥ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእናቶችንና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የወጣቶች እምቅ አቅም የአገራችን ተስፋ ስለሆነ ተጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ሃይለማሮያም የሴቶች ተሳትፎም በሁለንተናዊ መልኩ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና እንዲጎለብት እናደርጋለን ማለታቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
| < Prev | Next > |
|---|


