የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት በቅርቡ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ይጀምራል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2005 (ዋኢማ ) - በትግራይ ክልል እየተገነባ ያለው 120 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት በመጪው መጋቢት ወር ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡
የፕሮጀክቱ መካኒካል መሐንዲስ አቶ ሰለሞን ይስማ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደተናገሩት መንግሥት የህብረተሰቡን የመብራት ኃይል ፍላጎት ለማሟላት በሚያደርገው ጥረት በትግራይና በአዳማ አካባቢዎች በነፋስ ኃይል የሚሰሩ የኃይል ማመንጫዎች ግንባታ ጀምሯል፡፡
የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት በጠቅላላ 120 ሜጋ ዋት የማመንጨት ኃይል ሲኖረው በአሁኑ ወቅት 90 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው ኃይል ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡ ቀሪው 30 ሜጋ ዋት የሚያመነጨው የነፋስ ኃይልም በመጪው መጋቢት ወር ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር ተናግረዋል፡፡
በኃይል አሰጣጡ ረገድም ቀደም ሲል በነበረው ግንባታ አንዱ ተርማይል 1 ሜጋ ዋት ብቻ የማመንጨት ኃይል እንደነበረው ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት ግን አንዱ ተርማይል 1 ነጥብ 67 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንዳለው ተናግረዋል፡፡ የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት ቀላል ፣ ዘመናዊ እና በአጭር ጊዜ ግንባታቸው ተጠናቆ አገልግሎት በመስጠት ተመራጭ መሆናቸውን ጠቅሰው የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቅቀ የአገሪቱን የመብራት ኃይል አቅርቦት በተወሰነ መልኩ እንደሚያሳድገው ገልጸዋል፡፡
እንደ ኢዜአ ዘገባ በ210 ሚሊዮን ዮሮ እየተገነባ ያለው የአሸጎዳ የነፋስ ኃይል ፕሮጀክት ከመቀሌ ከተማ በ28 ኪሎ ሜትር ርቀት እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


