ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት የበለጠ ማጠናከር ትፈልጋለች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2004 (ዋኢማ) - የኢፌዴሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ጋር በሁለቱ ሀገሮች ግንኙነት ዙሪያ ላይ ተወያዩ።
የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ሬክ ማቻር ትናንት በውይይቱ ወቅት እንደተናገሩት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው በመመረጣቸው የእንኳን ደስ ያለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል በእሳቸው ጊዜም የሁለቱ ሀገሮች ግንኙነትም የበለጠ እንደሚጠናከር ያላቸውን ፅኑ እምነት ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በህይወት ባሉ ጊዜ ደቡብ ሱዳን ከኢትዮጵያ ጋር የነበራትን ጥብቅ ግንኙነት ያስታወሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ አሁንም አጠናክራ የምትሔድ መሆኗን ለመግለጽና ግንኙነቱን የበለጠ ለማዳበር ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ተናግረዋል።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ዶክተር ማቻር እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳን ታደርግ የነበረውን ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ፅኑ ፍላጐት አላቸው። በቀጣይም አዲስ አበባ ላይ የሚካሄደውን የደቡብ ሱዳንና ሰሜን ሱዳን ውይይት አመልክተው ለአቶ ኃይለ ማርያም ሃሳባቸውን ገልፀውላቸውል ።
ምክትል ፕሬዚዳንቱ ማቻር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዜና እረፍት የተሰማቸውን ጥልቅ ኅዘን በድጋሚ ገልጸዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በበኩላቸው፤ ከዚህ ቀደም
ሲያገኙት የነበረው ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ ሁለቱ ሱዳኖች የተረጋጉ እንዲሆኑ ድጋፍ እንደምታደርግም አመልክተው፤ በተለይም አዲሲቷ ሀገር ደቡብ ሱዳን የተረጋጋችና የበለፀገች ሀገር እንድትሆን ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።
በሁለቱ ሀገሮች መካከል በርካታ ልዩነቶች መኖራቸውን ያመለከቱት አምባሳደር ዲና፤ በአብነትም የፀጥታና የድንበር ጉዳይን ጠቅሰዋል። በእነዚህና በመሳሰሉትም ልዩነታቸው ዙሪያ አዲስ አበባ ውስጥ ብዙ ጊዜ ውይይት መካሄዱን አስታውሰው፤ ስምምነት ላይ የደረሱባቸው ጉዳዮች እንዳሉም ጠቁመዋል።
ይሁን እንጂ ገና ስምምነትን የሚጠይቁ ጉዳዮች እንዳሉ ጠቁመው፤ በተለይ በፀጥታና ድንበር ጉዳይ ላይ እንደሆነም አብራርተዋል። በእነዚህም ጉዳይ ላይ ቢሆንም የመቀራረብ አዝማሚያ እንዳለ አመልክተዋል።
በተያዘው ወር መጨረሻም በሚያደርጉት ውይይት ስምምነት ላይ ይደርሳሉ የሚል እምነት መኖሩን ጠቁመው። ኢትዮጵያም ለሁለቱ ሀገሮች ካላት ቅርበት የተነሳ ድጋፍ እንደምታደርግ ተናግረዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


