ድርጅቱ ለ2005 ዓ/ም 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር የፕሮጄክቶች ማስፈጸሚያ መደበ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ መስከረም 5/2004 (ዋኢማ) - የአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት አገልግሎት አሰጣጥን የበለጠ ለማሻሻል የሚያስችሉ የማሻሻያና የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች መከናወናቸውን የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ለ2005 በጀት ዓመት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መድቧል፡፡ የድርጅቱ የሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ ወንድም ተክሉ የ2004 በጀት አመት አፈጻጸምና የ2005 በጀት ዓመት እቅድን በተመለከተ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ውስጥ 15 አውሮፕላኖችን ማቆም የሚችል ሜዳ ግንባታ አከናውናል። ድርጅቱ ከዚህ ቀደም 19 አውሮፕላኖችን ብቻ ማቆም የሚያስችል ሜዳ የነበረው ሲሆን አዳዲስ የተገነቡትን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት 34 አውሮፕላኖችን ለማቆም የሚያስችል አቅም አለው።

አቶ ወንድም እንዳሉት ድርጅቱ አዲስ ከተገነባው የአውሮፕላን የማቆሚያ ሜዳ ጋር የሚጣጣም የመንገደኞች ማስተናገጃ ህንጻ ለመገንባትም በዝግጅት ላይ ይገኛል።

በብሄራዊና በአለም አቀፍ ደረጃ የአየር ትራፊክ ፍሰት በየጊዜው እያደገ በመምጣቱ የኤርፖርቱን አቅም ማሳደግ ማስፈለጉን የተናገሩት አቶ ወንድም በክልል የሚገኙ ኤርፖርቶችን ለማሻሻልም አዳዲስና የማስፋፊያ ሥራዎች መከናወኑን ጠቅሰዋል። በ2004 በጀት አመት ድርጅቱ በሚያስተዳድራቸው ኤርፖርቶች ውስጥ ከ6 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች መስተናገዳቸውንም አመልክተዋል። እንደ ሃላፊው ገለጻ ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዓቀፍ ኤርፖርት በሰው ኃይል ይከናወን የነበረውን የመንገደኞች ፍተሻ አገልግሎት በአዲስ ቴክኖሎጂ ተክቷል።

አዲሱ ቴክኖሎጂ እስከ 10 ደቂቃ ይወሰድ የነበረው የፍተሻ አገልግሎት ወደ ሁለት ደቂቃ ዝቅ አድርጎታል። ድርጅቱ በአዲሱ በጀት አመትም በአዲስ አበባ ቦሌ አለም አቀፍ ኤርፖርት ተጨማሪ 10 አውሮፕላኖች ለማቆም የሚያስችል የማስፋፊያ ሜዳ ግንባታን ጨምሮ የኮምቦልቻ፣የአሶሳ፣የባህርዳርና በጅማ ኤርፖርቶችን የመንገደኞች ማስተናገጃ ህንጻ ግንባታን ለማጠናቀቅ አቅዷል። በድሬዳዋ፣ በመቀሌ፣ በሠመራ ኤርፖርቶች ልዩ ልዩ የማሻሻያ ሥራዎችን በማካሄድ ኤርፖርቶቹ ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ የገለጹት ሃላፊው ለፕሮጀክቶቹ ማስፈጸሚ 1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መመደቡን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በዘንድሮው በጀት ዓመት ከ123 ሺህ በላይ መደበኛና መደበኛ ያልሆኑ በረራዎችን በማስተናገድ ከ9 ሚሊዮን በላይ መንገደኞች አገልግሎት ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 272 guests