በራያ ዓዘቦ ለመስኖ የሚውሉ 36 ጥልቅ ጉድጓዶች ለመቆፈር እንቅስቃሴ ተጀመረ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 4/2005 (ዋኢማ) - በትግራይ ክልል በራያ ዓዘቦ ወረዳ ከ105 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለመስኖ የሚውሉ 36 ጥልቅ ጉድጓዶችን ለመቆፈር ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን የወረዳው ውኃ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡
የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ማንአየ ጌታሁን እንደተናገሩት መንግሥት በመስኖ ስራ አርሶ አደሩን የበለጠ ተጠቃሚ ለማድረግ በዘንድሮ ዓመት አላማጣን ጨምሮ በወረዳው ለመስኖ የሚያገልግሉ 36 ጥልቅ ጉድጓዶች ለመቆፈር እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡
በክልሉና በፌዴራል መንግሥት በተመደበ በጀት የሚቆፈሩት ጥልቅ ጉድጓዶቹ ከአንድ ዓመት በኋላ ሲጠናቀቁ 18 ሺህ ሄክታር መሬት የማልማት አቅም ይኖራቸዋል፡፡
በዚህም በወረዳው የሚገኙ 15 ሺህ 450 አርሶ አደሮች ከመስኖ ልማቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አስታውቀዋል፡፡ በወረዳው የመስኖ ስራ መስፋፋት አርሶ አደሩ ከዝናብ ጥገኝነት ተላቆ በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ በማምረት በምግብ እህል ራስን ለመቻል የሚደረገውን ሁልንተናዊ ጥረት እንዲሳካ የሚያደርግ ነው፡፡
በራያ ዓዘቦ አካባቢ ከፍተኛ የሆነ የከርሰ ምድርና የገጸ ምድር ውኃ ክምችት በመኖሩ የጥልቅ ጉድጓዶች የቁፈራ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡
በወረዳው ባለፉት ጥቂት ዓመታት 5 ነጥብ 5 በመቶ የነበረው የመስኖ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ቁጥር በአሁኑ ወቅት ወደ 6 ነጥብ 8 በመቶ መድረሱንም ገልጸዋል፡፡ መንግሥት በሚከተለው ግብርና መር ፖሊሲ በወረዳው በርካታ አርሶ አደሮች የመስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው በተለይ አርሶ አደሩን የዘመናዊ መስኖ ተጠቃሚ ባለቤት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ከምንጊዜውም በላይ ተጠናክሮ መቀጠሉን መግለጻቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


