ሶማሊያ አዲስ ፕሬዚዳንት ሰየመች

  • PDF

አዲስ አበባ፤ መስከረም 2/2003 (ዋኢማ) - ሐሰን ሼክ ማህሙድ የሶማሊያ ፕሬዚዳንት በመሆን ትናንት ተመረጡ። የሶማሊያ ምክር ቤት አባላት ባደረጉት ምርጫ ፕሬዚዳንቱን ከሽግግሩ መንግሥት ፕሬዚዳንት በከፍተኛ ድምፅ ልዩነት አገሪቱን እንዲመሩ መርጠዋቸዋል።

ተመራጩ ፕሬዚዳንት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድን 190 ለ79 በሆነ ድምፅ መምረጣቸውን ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል። በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ በተከናወነው ምርጫ በመጀመሪያው ዙር አንዱም ተወዳዳሪ ሁለት ሦስተኛውን ድምፅ ሳያገኝ ቀርቷል።

በሁለተኛው ዙር በመጀመሪያው ዙር ድምፅ አሰጣጥ ሦስተኛ የወጡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲወሌ መሐመድ ወሌና አራተኛ የሆኑት አብዱልቃድር ኦስቦሌ ራሳቸውን አግልለዋል። ተሰናባቹ ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ በአገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ በምርጫው መሸነፋቸውን አምነዋል። ''በሶማሊያ ከ42 ዓመታት በኋላ ፍትሃዊ ምርጫ በመካሄዱ እጅጉን ተደስቻለሁ'' ሲሉም ተናግረዋል።

በሶማሊያ እየታየ በመጣው መረጋጋት የፕሬዚዳንቱን ምርጫ ለማካሄድ እንዳስቻለም ምንጮቹን የጠቀሰው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘገባ አመልክቷል ። ፕሬዚዳንት ሐሰን በብሄራዊና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚንቀሳቀሱ የሰላምና የልማት ተቋማት የሰሩ ምሁር ናቸው።

እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1981 ከሶማሊያ ብሄራዊ ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቁ ሲሆን፣በሕንዱ ቦፓል ዩኒቨርሲቲ የማስትሬት ዲግሪ ትምህርታቸውንም ተከታትለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት መርጃ ድርጅት(ዩኒሴፍ)በደቡብና ማዕከላዊ ሶማሊያ የትምህርት መኮንን ሆነው አገልግለዋል። ለሲማድ ዩኒቨርሲቲ መነሻ የሆነውን የሶማሊያ ማኔጅመንትና አስተዳደር ልማት ተቋምን በተባባሪነት መስርተዋል።ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት በሊቀመንበርነት የሚመሩትን የሰላምና የልማት ፓርቲም መስርተዋል።

ፕሬዚዳንት ሐሰን ሶማሊያን ከእርስ በርስ ጦርነትና እልቂት የጸዳች በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ ተስፋ እንደተደረገባቸው ዘገባዎቹን ዋቢ ያደረገው ኢዜአ አስታውቋል። በአገሪቱ ከ20ዓመታት በላይ ባስቆጠረው ጦርነትና አለመረጋጋት ሰፍኖ መቆየቱንና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮ (አሚሶም)ና በሽግግር መንግሥቱ ሠራዊት እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውጤት እያስገኘ መጥቷል።


  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 309 guests