ጅምሩን ዳር እናድርስ
አያሌው
ሀገራቸውን በዓለም መድረክ ያኮሩ፣ ለሀገራቸው ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ሌት ተቀን የተጉና የጣሩ፣ ለአፍሪካ ጥቅም የተሟገቱ፣ አብረዋቸው ለሚሰሩ ጓዶቻቸው አርአያ የነበሩ ታላቅ መሪ - ታጋይ መለስ ዜናዊ፡፡
አሁን የምንገኝበት ይህ ወቅት ለመላ ኢትዮጵያውያን እጅግ ከባድ የሀዘን ጊዜ ነው፡፡ ሁለንተናችን የምንለውን ታላቁን፣ የብልጽግና ብርሀን የፈነጠቀልንን መሪያችንን ባላሰብነውና ባልጠበቅነው ሁኔታ ያለጊዜው የተነጠቅንበት ወቅት ነው፡፡
ታጋይ መለስ ከሕዝብ የተገኙ፣ ለሕዝብ የኖሩ፣ በሕዝብ ያለፉ ቁልፍ ሰው ነበሩ። ላለፉት 38 ዓመታት በኢትዮጵያ ሠላም፣ ዴሞክራሲ፣ ዕድገትና ብልጽግንና እውን ለማድረግ ሳይታክቱ ታግለዋል፡፡ በጽናት የተታገሉለት ዓላማም እውን ሆኗል፡፡
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የህወኃት ሊቀመንበር በኋላም የኢህአዴግ ሊቀመንበር በመሆን ፓርቲውን ያገለገሉና ለውጤት ያበቁት ታጋይ መለስ በሽግግር ወቅት ሀገሪቱን በፕሬዚዳንትነት ቀጥሎም በጠቅላይ ሚኒስትርነት በብቃት ኃላፊነታቸውን የተወጡ ታላቅ መሪ ነበሩ።
ታጋይ መለስ አገርን ከመምራት ባሻገር ከነበራቸው አጭር ጊዜ በመቆጠብ በእውቀት ራሳቸውን ለማነፅ በመትጋታቸው እንግሊዝ ሀገር ከሚገኘው ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን የማስትሬት ዲግሪ፣ ኔዘርላንድስ ከሚገኘው ኤራስመስ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የማስትሬት ዲግሪ በከፍተኛ ማዕረግ አግኝተዋል፡፡
ከደቡብ ኮሪያ ሀናም ዩኒቨርሲቲም በፖለቲካል ሣይንስ የክብር ዶክትሬት ዲግሪ አግኝተዋል፡፡
“የአፍሪካን ቀንድ በማረጋጋት ለዓለም ሠላም አስተዋጽኦ ያደረጉ መሪ” ሆነው በመገኘታቸው የዓለም ሠላም ተሸላሚ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በ1997 ዓ.ም የ“አፍሪካን አሜሪካን ኢንተርፕሪነርስ ኦርጋናይዜሽን” ሽልማት ተቀብለዋል፡፡ በተመሣሣይ ዓመትም መሠረቱን አሜሪካ ባደረገ “ክርስታል ኤግል ሊደርሺፕ አዋርድ” ተሸላሚ ሆነዋል፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ አስቸጋሪ ሁኔታ በገጠማት ወቅት ጥሩ አመራር በመስጠታቸው “ጉድ ጋቨርናንስ አዋርድ ፎረ አፍሪካ” በተባለ ተቋምም ተሸልመዋል፡፡ በኖርዌይ ኦስሎ የያራ ፋውንዴሽን በ1997 ዓ.ም ያገኙትን የገንዘብ ሽልማት በገጠር ለሚኖሩ ችግረኛ ሴቶች ማስተማሪያ እንዲውል አበርክተዋል፡፡
ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽንም በ1999 ዓ.ም የ“ጎልድ ኦፍ ሜሪት አዋርድ”ን ከመሸለማቸው በተጨማሪ መሠረቱን አሜሪካ ባደረገውና “አፍሪካን ፖለቲካል ሊደርሽፕ አዋርድ” በተሰኘው ጋዜጣ በ2000 ዓ.ም ተሸላሚ ሆነዋል፡፡
ታጋይ መለስ በዓለም አቀፍ የትብብር መስኮች ላይ በመሪነት በመገኘት በ1998 ዓ.ም የቻይና አፍሪካ የልማት ትብብር ፎረምን መርተዋል፡፡ በዚህ ፎረም የቻይናና የአፍሪካን የልማት ትብብር እውን ለማድረግ የቤጂንግ የድርጊት መርሃ ግብርን በመቅረጽ ተሳትፈዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ከ1987 እስከ 1988 ዓ.ም የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሆነው በከፍተኛ ብቃት አገልግለዋል፡፡ "አዲስ አጋርነት ለአፍሪካ ልማት /ኔፓድ/" የተባለውን የልማት ትብብርን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠው ሰርተዋል፡፡ አቶ መለስ አፍሪካን በመወከል ለአህጉሩ የአየር ንብረትና አካባቢ ጥበቃ የአፍሪካ ልሣን በመሆን በዓለም አቀፍ መድረክ ተሟግተው ከፍተኛ ውጤትን አስመዝግበዋል፡፡
ታጋይ መለስ ገና ከወጣትነታቸው ጀምሮ ድህነት ከምድረ ኢትዮጵያ መጥፋት አለበት፤ ኢትዮጵያውያን ቀላል የማይባል የተፈጥሮ ሀብት ይዘው መራብ አይኖርባቸውም የሚል ሀሳብ ነበራቸው።
አርሶ አደሩ የዘመናዊ ግብርና ተጠቃሚ ባለመሆኑ በትጥቅ ትግሉ ወቅት ለእንግሊዝ የዜና ማሰራጫ ኮርፖሬሽን /ቢቢሲ/ በሰጡት ቃለ ምልልስ “ሕዝብ በረሀብ እያለቀ ነው፤ የዘመናዊ ግብርና ተጠቃሚ ባለመሆኑ ረሀብ እየገደለው፣ ለስደትም እየተዳረገ ነው፤ ከዚህ የበለጠ አሳዛኝ ነገር በሕይወቴ የገጠመኝ ጊዜ የለም፤ ይህ ለእኔ ፈታኝ ወቅት ነው፤ የምንዋጋውም ይህንን ችግር ለመቅረፍ ነው።” ነበር ያሉት፡፡
በአሁኑ በአገራችን ተተግብሮ የአርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን ህይወት እየቀየረ ያለው ፖሊሲና ስትራቴጂ ገና በበረሃ እያሉ የተናገሩት ነበር፡፡ ይህ ፖሊሲና ስትራቴጂ አርሶ አደሩንና አርብቶ አደሩን የዘመናዊ ግብርና ተጠቃሚ ማድረግ በመቻሉ ምርትንና ምርታማነትን ማሳደግ ችለዋል።
ዕድሜያቸው ለትምህርት የደረሱ ህጻናት የትምህርት ማዕድ ተቋዳሽ እንዲሆን አድርገዋል። የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ እንዲያድግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት አቶ መለስ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከመኖሪያ መንደር ከሦስት ኪሎ ሜትር በማይበልጥ ርቀት እንዲገነቡ በማድረግ የአርሶ አደሩና አርብቶ አደሩ ልጆች የትምህርት እድል ተቋዳሽ እንዲሆኑ ተደርጓል።
የሁለተኛ ደረጃና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በማስፋፋትና የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተከፍተው አገልግሎት እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር ባሻገር ተቋማቱ የሚያሰለጥኗቸው ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ የትምህርት ፖሊሲው በአዲስ የትምህርት ሥርዓት ተቃኝቶ አገልግሎት ላይ እንዲውል የበሰለ አመራር በመስጠታቸው ስኬትን አስመዝገበዋል።
በከተማዎች ሥራ አጥነትን ለመቅረፍም በልዩ ልዩ ዘርፎች አነስተኛና ጥቃቅን በማደራጀት፣ ወጣቶች ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ በገንዘብና በቁሳቁስ በመደገፍ በርካቶች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ብሎም ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ ዕድሉ ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ከዚሁ ተነስተው ወደ ከፍተኛ የልማት መስክ የተሸጋገሩ መኖራቸው በተግባር ታይቷል፡፡
በግንባታው መስክ በመንገድ ልማት ገጠሩን ከከተማ ለማገናኘት በከተማ ያሉትን መንገዶችም የማሳደግና ጥራታቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይን በማፍሰስ ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል፡፡ አብዛኛው ኅብረተሰብ በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደርና በቤት ኪራይ ችግር የሚሰቃይ በመሆኑ ይህንኑ ችግር ለማቃለል የጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ በስፋት እንዲካሄድ አድርገዋል ታጋይ መለስ ዜናዊ።
በሀገሪቱ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የማስፈንና የመገንባት ሂደት የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲፈጠር መደላድሎችን በማመቻቸት፣ የምርጫ ቦርድ በማቋቋም፣ ፓርቲዎች ጠቃሚ ፕሮግራም እንዲኖራቸው ሥልጠና እንዲያገኙ በማድረግ፣ የመተዳደሪያ ደንብ በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ምቹ ሥራዎች እንዲከናወኑ አድርገዋል።
በዚህም ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት ተጥሎ ሕዝቡም በነፃነት ይበጁኛል ያላቸውን ወኪሎቹን በምርጫ ሥልጣን ላይ የማውጣት መብት ተጐናጽፏል፡፡የብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች መብት በሕገ - መንግሥቱ መሠረት መከበሩ ለሀገሪቱና ለዜጎቿ ህልውና መረጋገጥ ወሣኝ ነው፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝቦች በራሳቸው ቋንቋ የመማር፣ የመሥራት፣ የመደራጀትና ራሱን የማስተዳደር መብት እንዲኖረው ዕድል አግኝቷል፡፡ በዚህም ከእርስ በርስ ግጭት በመላቀቅ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ልዩነታቸው ውበታቸው ሆኖ አንድነታቸው እንዲጠበቅ ያስቻለ ሥርዓት እንዲሰፍን አድርገዋል፡፡
ክልሎች ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ በሕገ-መንግሥቱ በመደንገጉ እያንዳንዱ ክልል ለመልማት በሚያስፈልገው መጠንና ደረጃ ብርቱ እንቅስቃሴ በማድረግ የእኩል ተጠቃሚነትና የጋራ እድገት እንዲኖር ያስቸለ ስርዓትን ፈጥረዋል፡፡
የሕዝቦች በነፃነት የመናገርና የመደራጀት መብት ገደብ እንዳይኖረውና የሕገ -መንግሥቱን ድንጋጌ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ የግል መገናኛ ብዙኃን እንደ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ራዲዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመሳሰሉት እንበለገደብ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
የሀገሪቱ የጤና ፖሊሲ የኅብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያማከለ እንዲሆን በገጠር ምንም ህክምና ሳያገኝ ለዘመናት በተላላፊ በሽታዎችና በሞት ይጠቃ የነበረውን ኅብረተሰብ ለመታደግ በየትኛውም የገጠር አካባቢ ክሊኒክ፣ የጤና ጣቢያና ሆስፒታሎች በየደረጃው ተገንብተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር በጤና ባለሙያዎች የጤና ክብካቤ ትምህርት በመሰጠቱ የኅብረተሰቡ ጤና የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲገኝ አስችለዋል፡፡ በሀገራችን የተቀየሰው የጤና ፖሊሲ ውጤታማ ከመሆን ባሻገር ትልቅ እመርታ በማሳየቱ ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ያከናወነችው ተግባር ለሌሎች አርአያ ሆኖ በዓለም መድረክ እውቅና ለማግኘት አብቅቶናል፡፡
የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገት ወደተሻለ ደረጃ እየተሸጋገረ ሲሄድ የኃይል አቅርቦት በእጅጉ በማስፈለጉና ቀደም ሲል የነበረው ዕድገቱንና ፍላጐቱን መሸከም ባለመቻሉ የሀገሪቱ የውሀ ሀብት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ መትጋት አማራጭ አልነበረውም፡፡ በመሆኑም ግልገል ጊቤ አንድ፣ ሁለትና በመገንባት ላይ ያለው ግልገል ጊቤ ሦስት ታቅደው ወደ ተግባር እንዲሸጋገሩ በመደረጉ የተሻለ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር በማድረግ ምጣኔ ሀብታዊ ዕድገቱ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ በሀገሪቱ ግዙፍ የሲሚንቶና የማምረቻ ፋብሪካዎች እንዲገነቡ ዕድሉን ተመቻችቷል፤ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ግንባታም የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦ ግንባታቸው እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ቀንድና ለዓለም ሠላም መስፈን ያላትን ቁርጠኝነት ለማሳየት በሩዋንዳ፣ በላይቤሪያ፣ በብሩንዲ፣ በሱዳንና በሶማሊያ ለሠላም ማስከበር ዘብ በመቆም ሠራዊቷን በሀገሮቹ በተባበሩት መንግሥታት ጥላ ሥር በማሰማራት የሠላም አጋርነቷን እንድታረጋግጥ አስችሏታል፡፡ ይህም ዓለም አቀፍ ክብርን አጐናጽፏቸዋል፡፡
ተጋይ መለስ ዜናዊ በመሪነት ዘመናቸው አሻራቸውን ካሳረፉባቸው የልማት ሥራዎች በተጨማሪ ኢትዮጵያ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገራት ተርታ እንድትሰለፍ ታላቅ ራዕይ ሰንቀው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የመጀመሪያ ምዕራፍ ዕቅድ በመንደፍና የትግበራ መመሪያ በማውጣት፤ በዙሪያቸው የተሰባሰቡትን የሥራ አጋሮቻቸውን በማሰለፍ በመሪነት አኩሪ ተግባር ፈፅመው አሁን ላለንበት ምዕራፍ አድርሰውናል፡፡
የታይ መለስ ዜና እረፍት ከተሰማ ጀምሮ መላ ኢትዮጵያውያን ውድ መሪያቸውን በማጣታቸው በእንባ እየተራጩ ሀዘናቸው ከብዶ ይገኛል፡፡ ብዙ ሰርተው ያሰሩናል፤ ሀገሪቱን ወደላቀ ደረጃ ያሸጋግሩዋታል ብለን ያሰብናቸው መሪያችን ድንገት ሲለዩን ቀን የጨለመብን ያህል ተሰምቶናል፡፡
ይሁን እንጂ ኢትዮጵያውያን እጅና ጓንት ሆነን የተጀመረውን የእድገት ጉዞና የሠላም አቅጣጫ በማስቀጠል የመሪያችንን ጅምር ከግብ በማድረስ ህያው ሆነው እንዲኖሩ ለማድረግ ቆርጠን ተነስተናል።
የታጋይ መለስ ዜና እረፍት ዓለምን በሀዘን ያናወጠ ጉዳይ ነው፡፡ የዓለም መሪዎች፣ ታዋቂ ሰዎችና የመገናኛ ብዙኃን ስለ ታጋይ መለስ ዜና እረፍት በሰሙበት ወቅት መሪር ሀዘናቸውን በተለያየ አግባብ የገለፁትም ለዚህ ነበር። ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ቢሆኑ በተመሣሣይ መልኩ ነበር የዘገቡት። ታጋይ መለስ የኢትዮጵያ ብርሃን ነበሩ፤ የአፍሪካ ተሟጋችና ጠበቃ የዓለም ሠላም ተዋናይ ታላቅ መሪ። የእኚህን ታላቅ መሪ ጅምር ዳር በማድረስ ለዘለዓለም ህያው ሆነው እንዲኖሩ እናደርጋለን፡፡ ጅምራቸውንም ዳር እናደርሳለን - ሠላም፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


