የመለስ አልፋና ኦሜጋ ዲፕሎማሲ

  • PDF

ቶሎሳ ኡርጌሳ


ተወዳጁ፣ ራሳቸውን ለህዝብ አሳልፈው በመስጠት የኖሩት የፖለቲካው ሊቅ ታላቁ መሪያችን ትተውልን ያለፉት መስመር ዛሬ በእጃችን ላይ ይገኛል። ጠቢብና የልሂቅ አዕምሮ ባለቤት የነበሩት ታጋይ መለስ ከፖለቲካው ባሻገርም የዲፕሎማሲ መሀንዲስነታቸውንም ጥለውልን አልፈዋል።

እናም ምንም እንኳን ሀዘናችን መሪር ቢሆንም፤ ሀዘናችንን ችለን ከእርሳቸው መጨረሻ ከሌለው ዲፕሎማሲ ብዙ በመማር እንደ ዜጋ የየድርሻችንን መወጣት ያለብን ይመስለኛል። እስቲ የሚከተለውን ጥበብ የተሞላበትን

ዲፕሎማሲያዊ አባባል እንመልከት፦
“...ኧረ ለመሆኑ ማነው ማንዴላን ያሰለጠነው?- ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ናቸው፡፡ አድኃሪው ኃይለ ሥላሴ ናቸው-አብዮታዊውን ማንዴላን ያሰለጠኑት፡፡ ...ማነው ሮበርት ሙጋቤ ከሮዴሽያ አገዛዝ ነፃ ለመውጣት በሚፋለምበት ወቅት የረዳው? -መንግሥቱ ነው፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም በሀገር ውስጥ አምባገነንና ጨፍጫፊ ነው፡፡ ነገር ግን በአፍሪካ ጉዳይ  ልክ እንደ ኃይለ ሥላሴ አቋሙ ጠንካራ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ መሪዎች ቢለዋወጡም፣ በአፍሪካ ጉዳይ ላይ ግን አቋማቸው አንድ ነው፡፡ የአዲሱ አፍሪካ ህብረት መቀመጫ አዲስ አበባ መሆን የለበትም፣ ለእኔ ይገባኛል የሚል ካለ እውነቱን ፍርጥርጥ አድርገን ልንነጋገርበት እንችላለን፡፡...”
ይህን አባባል የተናገሩት በቅርቡ ሣምንት በሞት የተለዩን ባለራዕዩ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ እኚህ ታላቅ መሪያችን አባባሉን የገለጹት በአዘቦት ወቅት አይደለም - የአፍሪካ ህብረት ምሥረታ የመሪዎች ጉባዔ በቶጎ ርዕሰ ከተማ ሎሜ ላይ ሲካሄድ ያቀረቡት የመከራከሪያ ሀሳብ እንጂ፡፡


በወቅቱ ጉባዔው ሲካሄድ የሴኔጋል ፕሬዚዳንት የነበሩት አብዱላሂ ዋዴ ‘የህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ይሆናል’ የሚለውን አንቀጽ እንደማይቀበሉት ሲያስታውቁ ነው - ውዱ መሪያችን በበሳል ዲፕሎማሲያዊ አቀራረብ የህብረቱን አባል ሀገራት ለማሳመን አባባሉን የገለጹት፡፡


ታዲያ እኚህ ውድ የኢትዮጵያ ልጅ በወቅቱ የአባል ሀገራቱን መሪዎች በማያወላዳ ሁኔታ በማሳመን የህብረቱ መቀመጫ አዲስ አበባ ሆኖ እንዲቀጥል አድርገዋል፡፡ በዚህም አንዳንድ ለሀገራችን በጎ አመለካከት ያልነበራቸው ሀገራት አዲሱ የአፍሪካ ህብረት ጽሕፈት ቤት ከአዲስ አበባ እንዲነሳ የነበራቸው ሀሳብ ከምኞት እንዳይዘል ያደረጉ ብርቅዬ ዲፕሎማት ነበሩ፡፡


እርግጥ በመግቢያዬ አካባቢ ያነሳሁት የታላቁ መሪያችን በሣልና ብልህነት የተሞላበት የዲፕሎማሲ ክህሎት፣ በመስኩ ካከናወኗቸው ተግባራት ውስጥ “ኢምንት” ነው፡፡ የእርሳቸውን መጨረሻ የሌለውን አልፋና ኦሜጋ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥራዎች በዚህች ውስን ፅሑፍ ለመዘርዘር መሞከር “አባይን በማንኪያ” የመጨለፍ ያህል ነው፡፡


ይሁንና እኚህ በታሪክ ዑደት ውስጥ አንዴ ብቻ ሊፈጠሩ የሚችሉ የሕዝብ ልጅ፤ ውስብስብ በሆነው የዲፕሎማሲው ዓለም ለምሥራቅ አፍሪካ ሠላምና መረጋጋት፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች  የአፍሪካ ሕዝቦች ድምጽ በመሆን ያበረከቱትን የማይተካ አስተዋጽኦን በጥቂቱም ቢሆን በመዳሰስ ከዚህ ፅሑፍ አንባቢ ምን እንደሚጠበቅ ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡


በቅድሚያ ግን ወትሮም ግጭትና አለመረጋጋት በማይለየው የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና ካበረከቱት ወደር የሌለው አስተዋጽኦ እንነሳ፡፡ ታጋይ መለስ የኤርትራ መንግሥት ሀገራችንንና ምሥራቅ አፍሪካን የጦርነት አውድማ ለማድረግ የቀመረውን የሽብር ስትራቴጂ በቅርበት በመከታተልና ብቃትና ብስለት ባለው ዲፕሎማሲያዊ አካሄድ እየተመሩ የአሥመራው አስተዳደር ለመፍጠር የሞከረውን ቀጣናዊ ቀውስ ለማርገብ በቁርጠኝነት ሲሰሩ የነበሩ አፍሪካዊ አባት ናቸው፡፡


ላለፉት 40 እና 50 ዓመታት ሰብዓዊ ጥፋት ያስከተሉ ጦርነቶች የተካሄዱበትን ይህን ቀጣና ማረጋጋት ቀላል ባይሆንም፤ ውዱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ግን ለሠላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆኑ አካሄዶችን በሣል በሆነና ብቃት ባለው አካሄድ እየተመሩ ያጋጥሙ የነበሩ ፈተናዎችን በድል ተወጥተዋል፡፡


ታጋይ መለስ አሸባሪነትና አክራሪነት በቀጣናው እንዳያቆጠቁጥና ምሥራቅ አፍሪካ ከጽንፈኞች ሥጋት ነፃ እንዲሆን ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ መሪ ናቸው፡፡ ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት መንግሥት አልባ በነበረችው ሶማሊያ የመሸገው “እሥላማዊ ፍርድ ቤቶች ህብረት” በወቅቱ በሀገራችን ላይ ደቅኖት የነበረውን ግልጽና ድርስ አደጋ ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ ሰማይ ላይ እንዲያንዣብብ ያደረገውን የጦርነት ደመና ብስለት በተሞላው ዘዴ አስወግደዋል፡፡


በወቅቱ የኢጋድ አባል ሀገራትንና አፍሪካ ህብረትን ከጎናቸው በማሰለፍ የሶማሊያ አክራሪ ፅንፈኞች አከርካሪያቸው እንዲሰበር ለማድረግ ችለዋል፡፡ በዚህም በአንድ መልኩ እንደ መንግሥት በአስተማማኝ ዲፕሎማሲ የሚመሩ መሆናቸውን ያረጋገጡ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ሠራዊታችን ማንኛውንም ግዳጅ በብቃት መፈጸም የሚችል ቁመና እንዳለው ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ አስተማማኝ ወታደራዊ ዲፕሎማሲ የገነቡ ታላቅ መሪ ናቸው፡፡


ራሱን “አል-ሸባብ” እያለ የሚጠራው የሶማሊያ ሽብርተኞች ቡድን በቀጣናው ሠላምን ለማናጋት ያደረገውን አፍራሽ እንቅስቃሴን ፈጥነው በመረዳትም ከምሥራቅ አፍሪካን የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ጋር በመሆን ወሣኝ ድርሻ ያበረከቱ  መሪ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ በኢጋድና በአፍሪካ ህብረት ውስጥ ባከናወኑት ጠንካራ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ሌሎች ሀገራትም ሠራዊታቸውን ወደ ሶማሊያ እንዲልኩ የማግባባት ተግባራትን ፈጽመዋል፡፡


ከዚህ በዘለለም፤ በዚያች ሀገር ውስጥ ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍንና ቋሚ መንግሥት እንዲፈጠር ሌት ተቀን ሲሰሩ ነበር፡፡ በዚህም ዛሬ ሶማሊያውያን ነፃና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያካሂዱ ጥርጊያ መንገድ በማመቻቸት ታጋይ መለስ ወደር የሌለው ሚና ተጫውተዋል፡፡


ከሁሉም ጎረቤት ሀገሮች ጋር በሠላም፣ በጋራ ጥቅምና በእኩልነት ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ለመፍጠር ደፋ ቀና ይሉ የነበሩት እኚህ ታላቅ የአፍሪካ ልጅ፤ ለየትኛውም ወገን የማይወግን የዲፕሎማሲ አካሄዳቸውን በመጠቀም ሱዳንና ደቡብ ሱዳን ችግራቸውን በሠላማዊ መንገድ እንዲፈቱ አስችለዋል፡፡፡


ባላቸው ለማንም ያልወገነ አቋም በሁለቱም ሀገሮች እኩል ተቀባይነት የነበራቸው ታጋይ መለስ፤ በመንግሥታቱ ድርጅት ታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ ሁለቱም ሱዳኖች የኢትዮጵያን መከላከያ ሠራዊት እንዲመርጡ ምቹ ፖለቲካዊና ወታደራዊ ዲፕሎማሲን መፍጠር የቻሉ መሪ ናቸው፡፡


ይህ ብቻ አይደለም፡፡ አቶ መለስ በሱዳን - ዳርፉር የተፈጠረውን ቀውስ ለማርገብ የሱዳን መንግሥትና የደቡብ ሱዳን ነፃነት ንቅናቄ “ሁሉን አቀፍ የሠላም ስምምነት” /Comprehensive Peace Agreement ‘CPA’/ እየተባለ የሚጠራውን ሰነድ እንዲፈራረሙ ብርቱ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት አድርገዋል፡፡


ከዚህ ባሻገርም፤ ለሠላም ካላቸው ፅኑ ፍላጎት በመነሳት የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ህብረት ተልዕኮ በዳርፉር (UNAMID) ጥላ ስር የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት በሠላም አስከባሪነት እንዲሰማራ በማድረግ በዚያች ሀገር መረጋጋት እንዲፈጠር ጥረዋል፡፡ በእነዚህ ቀጣናዊ ተግባሮቻቸው በአፍሪካ ሕዝቦች ዘንድ ታላቅ አክብሮትን ማግኘት የቻሉ አርቆ አስተዋይ መሪ ናቸው፡፡


የባለ ራዕዩ ውድ መለስ ሠላምን የተመረኮዙ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በምሥራቅ አፍሪካ ላይ ብቻ ያተኮሩ አይደሉም፡፡ ከዚህም አልፎ የመላው አፍሪካ ድምፅ በመሆን ዓለም አቀፍ ተቀባይነትን ወደ ማግኘትም የተሸጋገሩ ናቸው፡፡ ታላቁ መሪያችን አፍሪካውያን በመሠረታዊ የጋራ ጥቅም ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም እንዲወስዱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ላይ የአህጉሪቱ ቃል አቀባይ ሆነው ውጤት ማስገኘት የቻሉ ጀግና ኢትዮጵያዊ ናቸው፡፡


በተለይም በየዓመቱ በአማካይ በሁለት ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ይጨምራል ተብሎ በሚጠበቀው ዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ “አፍሪካ ዋነኛዋ ተጎጂ ናት” በማለት የምዕራቡ ዓለም በኢንዱስትሪ ሣቢያ ለፈጠረው የካርቦን ልቀት ለአህጉሪቱ ካሣ እንዲከፍል በመጠየቅ ከአፍሪካ ሕዝቦች ባሻገር ከራሳቸው ካደጉት ሀገራት ጭምር አንቱታን ለማትረፍ ችለዋል፡፡


አቶ መለስ በኮፐንሃገን፣ በሜክሲኮ...ወዘተ በተካሄዱ የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔዎች፤ አፍሪካ በለውጡ ይበልጥ ተጎጂ የሆነችው የአየር ንብረቷ ተጋላጭ፣ ለውጡን ለመቋቋም ያላት ገንዘብና ቴክኖሎጂ ውስን እንዲሁም አህጉሪቱ ዕድገቷን በአዲስ አማራጭ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ለመገንባት ያላት አቅም ከበለጸጉት ሀገሮች በአያሌው ያነሰ መሆኑን በማስረዳት በብርቱው የተከራከሩና አበረታች ውጤት ያመጡ ናቸው፡፡


በዚህ ተግባራቸውም የአፍሪካ አለኝታና መከታ መሆናቸውን በአደባባይ አስመስክረዋል፡፡ ይህን የዲፕሎማሲ እምቅ አቅማቸውንና ክሂላቸውን የተገነዘበው ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በተለይም የበለፀጉት ሀገራት በቡድን ስምንት እና 20 ስብሰባዎች ላይ ከሚገኙት በጣት የሚቆጠሩ የአፍሪካ መሪዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጋበዙ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡ እናም ቀደም ሲል በረሃብና በጦርነት የምትታወቀውን ሀገራችንን ስም በአዲስ የዲፕሎማሲ መንገድ አራማጅነት እንዲቀየር ለማድረግ የቻሉ የሀገራችንና የአፍሪካ ባለውለታ ናቸው፡፡


የብሩህ አዕምሮ ባለቤት የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትራችን በየጊዜው አዳዲስ ሃሳቦችን በማፍለቅም ይታወቃሉ፡፡

ቀደም ሲል የተጠቀሰውን የካርቦን ልቀት ችግርን ለመቋቋም “አረንጓዴ ልማት” የሚል አቅጣጫን በመቀየስ ሌሎች ሀገራት ከኢትዮጵያ ይህንኑ የካርቦን ልቀት መከላከያ ዘዴን እንዲወስዱ ያደረጉ ባለ ራዕይ መሪ ነበሩ፡፡


ሩቅ አሳቢው መለስ ሀገራችን እ.ኤ.አ በ2025 ትርፍ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ የማትለቅበት ደረጃ ላይ እንድትደርስ ሲያልሙ ነበር፡፡ በረዥሙ የአረንጓዴው ልማት ዕቅዳቸውም ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይልን በሰፊው አምርታ ከሚያስፈልጋት በላይ የሆነውን ኃይል ለጎረቤት ሀገር የመሸጥ፣ ነዳጅን ከዕፅዋት የማምረት ስትራቴጂን እንድትከተል እንዲሁም ካርቦንን ከአየር የመምጠጥ አቅሟ በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር ለማድረግ ያለመ ነው፡፡


ይህ የአቶ መለስ “የአረንጓዴ ልማት” አቅጣጫ በአፍሪካም ይሁን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ከማግኘቱም በላይ፤ በርካታ ሀገሮች “ሞዴሉን” በመውሰድ እየተጠቀሙበት ነው፡፡


የታላቁ መሪያችን ብሩህ አዕምሮ ያፈለቀው ይህ የልማት አቅጣጫ ትናንት በረሃብና በድርቅ የምትታወቀውን ሀገራችን፣ ዛሬ ለድርቅና ረሃብ መባባስ ምክንያት የሆነውን የካርቦን ልቀት ለመቋቋም የመፍትሄው አካል ሆና እንድትታይ ያደረገ ወደር የማይገኝለት የዲፕሎማሲ ተግባር ነው — ከትናንት የድርቅ ተጠቂነት ወደ ዛሬ የድርቅ መፍትሄ አመላካችነት የዲፕሎማሲ ድል የዘለቀ፡፡


ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የዲፕሎማሲ ተግባራት ውስጥ የማይረሳው ሌላኛው ታላቅ ክንዋኔ “የሠላም ዲፕሎማሲ” ነው፡፡ አቶ መለስ በህይወት በነበሩበት የመሪነት ዘመናቸው ሀገራችን ለአፍሪካ ሠላም መከበር በቁርጠኝነት የተንቀሳቀሱ መሪ ናቸው፡፡


ላለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያን ሲመሩ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በላይቤሪያና በሱዳን ዳርፉርና አብዬ ግዛት መከላከያ ሠራዊታችንን በማሰማራት ለአፍሪካውያን ሠላም መረጋገጥ ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ የተጉ የአፍሪካዊያን ተቆርቋሪ ነበሩ፡፡ በእርሳቸው አመራር ሰጪነት የተሰማራው ሠራዊታችንም የተሰጠውን ግዳጅ በብቃትና በፍጹም ወታደራዊ ዲስፕሊን በመታገዝ የአፍሪካውያን ኩራት መሆኑን በተግባር አረጋግጧል፡፡


እርግጥ እኚህ ባለራዕይ፣ የአፍሪካ ኩራትና ዲፕሎማት ዓለምን ያስደመሙ በሣልና አርቆ አስተዋይ መሪ ዛሬ በህይወት የሉም፡፡ የሀገራችንን ስም በዓለም አደባባይ የማደስ፣ የአፍሪካን ዘላቂ ጥቅሞች የማስጠበቅ እንዲሁም ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ገንቢ ሀሳቦችን የማቅረብ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸው ሥራዎቻቸው ግን ዛሬም ከእኛ ጋር ናቸው፡፡


ግና እዚህ ላይ የሚል ጥያቄን እንደ ዜጋ ማንሳት ያስፈልጋል፡፡ አዎ! ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ሀገራችንን በመሩባቸው ጊዜያት ያስተማሩን ታላቅ ጥበብ አለ፡፡ ይኸውም በማንኛውም ወቅት ሁሉም ዜጋ የሀገሩ አምባሣደር በመሆን  በግለሰብ ደረጃ የሀገራችንን ገፅታ መገንባት የሚችል መሆኑን ነው፡፡


ማንኛውም ዜጋ በሚሰማራባቸው የሥራ አካባቢዎች ሁሉ የብሔሩ ብሎም የሀገሩ አምባሣደር በመሆን የሀገራችንን ገፅታ መገንባት ይችላል፡፡ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት እንደ ግለሰብ የምንፈፅማቸው ማናቸውም ተግባራት የሀገራችን መገለጫዎች ይሆናሉ፡፡ ባህላችንን፣ ወጋችንን፣ ትውፊቶቻችንን በየተሰማራንበት ቦታ ስናስተዋውቅ ደግሞ እግረ - መንገዳችንን እኛነታችንን እንገልፃለን፡፡


እኛነታችንን ስንገልፅም ሀገራችንን የቱሪስት መዳረሻ እናደርጋለን፡፡

ይህም ገቢያችን እንዲጨምር ያደርጋል። በዚያው ልክም ወደ መካከለኛ ገቢ የምንደረደርበት አቅም ይጨምራል።

ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ተግባር የሚያከናውን ማንኛውም ግለሰብ የሀገርን ገጽታ የሚገነባ ከመሆኑም ባሻገር፣ ሁነኛ የዲፕሎማሲ  ተዋናይ ይሆናል፡፡ የዕድገታችን ዋስ ጠበቃ መሆኑም እንዲሁ። አዎ! አቶ መለስ እንደ ግለሰብም ይሁን እንደ መሪ ያስተማሩን ይህንኑ ነው፡፡


እናም ‘እያንዳንዱ ዜጋ የሀገሩ አምባሣደር ነው’ የሚለውን አባባል ሁሌም በማስታወስና በመተግበር፣ ታሪካቸው ለዝንተ - ዓለም የማይፋቀውን የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችንን የዲፕሎማሲ ራዕይ በየደረጃችን ልናስቀጥል እንችላለን፡፡


እነሆ ተወዳጁ፣ የሩቅ ህልም ያላቸው፣ አስተዋዩ፣ ሁለመናቸውን ለሕዝብ የሰጡት፣ የአፍሪካና የዓለም መከታ ዛሬ በህይወት ባይኖሩም፣ ትግል እንደ ዱላ ቅብብሎሽ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚሸጋገር ነውና  ጅምር የዲፕሎማሲ ሥራዎቻቸው ከእኛው ጋር ህያው ሆነው ይኖራሉ፡፡ ገና ሚሊዮን “መለሶችንም” ይፈጥራሉ፡፡


እናም የሀገራችን ዜጎች ታላቁ መሪያችን ባስተማሩን ጥርጊያ መንገድም ጅምሮቹን የዲፕሎማሲ ተግባራት የሀገራችን አምባሣደር በመሆን ከምንጊዜውም በላይ የምንወጣበት ወቅት አሁን ነው፡፡ አዎ! የመለስን አልፋና ኦሜጋ ረዥም ርቀት የዲፕሎማሲ ሩጫ የኢትዩጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እስካሉ ድረስ መቼም ቢሆን አይቀለበስም! ቸር


ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የአባይን ወንዝ አቅጣጫ የማስቀልበስ ተግባር በኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች ይከናወናል ብለው ገምተው ነበር?




Results

የአባይን ወንዝ አቅጣጫ የማስቀልበስ ተግባር በውጭው ማህበረሰብ ዘንድ በአመዛኙ የሚፈጥረው አስተሳሰብ ምን ይመስልዎታል?





Results