380 ግራም የሚመዝን ኮምፒውተር

  • PDF

የቴክኖሎጂ ማደግና መሻሻል የሚጠበቅ ነው፡፡ ዛሬ በየቢሯችን የምንጠቀምበት ኮምፒዩተር ሲፈበረክ ተአምር አሰኝቶ ነበር፡፡ ምክንያቱም የመጀመሪያዎቹ ኮምፒዩተሮች ከግዙፍነታቸው የተነሳ ከቦታ ቦታ ለማንቀሳቀስ አዳጋች ነበሩና፡፡ ኮምፒዩተሮቹን ለመጠቀምም የሚያስፈሩ ነበሩ፡፡ ከምትሀትና ከሰይጣናዊ እሳቤ ጋር ያመሳሰሉትም አልጠፉም፡፡    

እድሜ ለቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መጥቶ በየቢሮው ያሉት ዴስክቶፖች ኮምፒዩተሮች በላፕቶፕና በፍላት ስክሪን ቀልጣፋ ኮምፒዩተሮችም እየተተኩ ነው፡፡ የላፕቶፕ ኮምፒዩተሮች ዘመናዊነትም እጅግ በሚያስገርም ፍጥነት እየዘመነ መጥቶ የእጅ መዳፍ በምታክለው ኮምፒዩተር ተአምር ሊባል የሚችል ሥራዎችን ለመሥራት ተችሏል፡፡ ከመላው ዓለም ጋርም በመረጃ መረብ ለማገናኘት ፈጣኖች ሆነዋል፡፡

ሰሞኑን የሳምሰንግ ኩባንያ በርሊን ላይ ያስተዋወቀውና በዘመናዊ የኮምፒዩተር ቴክኖሎጂ የዘመነው አነስተኛ ኮምፒዩተር ወደ ገበያ ለመግባት በዝግጅት ላይ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቦታል፡፡

በርሊን ከተማ በተካሄደው የቴክኖሎጂ ኮንፈረንስ ላይ ሳምሰንግ ኩባንያ ያስተዋወቀው አነስተኛ ኮምፒዩተር ‘’ጋላክሲ ታብ’’ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ የብዙዎችን ቀልብ የሳበውና አድናቆትን ያተረፈው ጋላክስ ታብ የአይፖድ መጠን ያለው ሲሆን፣ አጠቃላይ ክብደቱም 380 ግራም ብቻ ነው፡፡ ጋላክሲ ታብ 18 ሴንቲ ሜትር ስክሪን እንደተገጠመለትና ከአንድ ወር በኋላ ቮዳፎን የተባለው ኩባንያ ለአውሮፓ ገበያ ለማከፋፈል መስማማቱን ዘገባው ጨምሮ ገልጿል፡፡

ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነው አነስተኛ ኮምፒዩተር እስካሁን ድረስ በምን ያህል ዋጋ እንደሚሸጥ በውል ያልተገለጸ ቢሆንም፣ ከሌሎቹ መሰል ኮምፒዩተሮች የተሻለ ዋጋ ሊሸጥ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ የአውሮፓን ገበያ ይቆጣጠረዋል ተብሎም ተተንብዮለታል፡፡
/አዲስ ዘመን/