ከመሬት መንቀጥቀጥ የሚታደገው አልጋ

  • PDF

የሥራ ፈጠራ ችግር ፈቺ መሆን እንዳለበት ይናገራሉ ባለሙያዎች፡፡ አንድ ችግር አጢኖ መፍትሄ የሚፈልግ ለራሱ ብልጽግናን፣ ለወገኑም አለኝታነትን ያተርፋል፡፡

የ66 ዓመቱ ቻይናዊ ፈጠራ ግን ችግር ፈቺ ብቻ ሳይሆን ነፍስ አድን ህይወት ታዳጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ዋንግ ዌንዚ የተባሉት አዛውንት የመሬት መንቀጥቀጥን የሚቋቋም አልጋ ሠርተዋል፡፡   

አዛውንቱ የመሬት መንቀጥቀጥ ሲያጋጥም ወዲያውኑ ወደ ጠንካራ ሳጥንነት የሚለወጥ አልጋ ዲዛይን ሠርተው በማቅረባቸው የባለቤትነት መብት አግኝተዋል፡፡

አልጋው ውሃ፣ የታሸገ ምግብ፣ የድምፅ ማጉሊያና መሠርሠሪያ በሁለቱም ጫፎቹ ማስቀመጥ ይችላል፡፡

ተጠቃሚዎቹን ፍርስራሽ እንዳይጐዳቸውም በሚገባ እንደሚከላከል ተገልጿል፡፡   አዛውንቱ በሰጡት አስተያየት #በዋንቹአንና ዩሹ የደረሱት የመሬት መንቀጥቀጥ አደጋዎች ያደረሱትን ውድመት ላይ ህይወትን የሚታደግ ነገር ለመሥራት በጥልቅ አሰብኩ፡፡

አልጋው በጡብና በኮንክሪት ከጠነከሩ ህንፃዎች መደረማመስ ይታደጋል; ብለዋል፡፡  

ጡረተኛው ዋንግ ዊንዚ የሌሎች አምስት የፈጠራ ሥራዎች የባለቤትነት መብትም አላቸው፡፡ ነገር ግን ወደ ገበያ አልወጡላቸውም፡፡   

እ.ኤ.አ. በግንቦት 2008 በደረሰው የመሬት መንቀጥቀጥ በዋንቹ አን 87ሺ በዩሹ ደግሞ 2ሺ 700 ያህል ሰዎች ሞተዋል፡፡ ጠፍተዋልም፡፡

የአልጋው ዲዛይን ተሰርቶ ሲወጣ ለቻይና ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም የመሬት መንቀጥቀጥ ለሚያሰጋቸው አገራት ጠቃሚ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡

የጡረታ ዘመን ከሠሩበት እንዲህ ያለ ጠቃሚና አስደናቂ ፈጠራ የሚገኝበት መሆኑን አዛውንቱ ለዓለም አሳይተዋል፡፡

/አዲስ ዘመን/