ሂዩማን ራይትስ ዎች ላይሳካለት ባይደክም ምናለበት?

  • PDF

ሙሉቀን ዘሪሁን

ከመሰንበቻው  በኢትዮጵያ  የእንግሊዝ  መንግስት  የልማት  ትብብር  ሚኒስትር አንድሪው  ሚቼል ለቢቢሲ “ኒውስ ናይት” መሠረተ - ቢስ ዘገባ በተመለከተ፤ “በኢትዮጵያ የዕርዳታ እህል ለፓለቲካ  ጠቀሜታ  አለመዋሉን በተጨባጭ  የመስክ  ቅኝት  አረጋግጠናል”  ሲሉ የሰጡት ምላሽ በእብድነት ሊያስቆጥር የሚችል አስገራሚ  ክስተትን ይዞ ብቅ  ብሏል፡፡  የክስተቱ  ክንዋኔም ከዘገባው  በስተጀርባ  የነበረውን የጉዳዩን ባለቤት  ባልተጠበቀ ፍጥነት  ካለበት ቦታ  ወጥቶ ባልተለመዱ  የቃላት  ውረፋና  ድንፋታ  ወገቡን እየሰበቀ  በስሜት  እንዲወረገረግ  ያደረገው  ነው —ሂዩማን ራይትስ  ዎችን፡፡

ቅሌት  የዘወትር  ምሳቸው  የሆኑትን የመድረክ  አመራሮች  እንደ ትክክለኛ  አስረጅ በመቁጠር  በሐሰት  ዘገባው  ወቅት  “ፈረስ  ያደርሳል እንጂ፤ አይዋጋም”  ብሎ  በቢቢሲ  ሽፋን ራሱን ከልሎ የነበረው ይህ ፅንፈኛ ተቋም፤የእውነታው ቁርጥ ቀን ሲመጣ ሚስተር  ሚቼል የሰጡትን  በመረጃ ላይ የተመኮረዘ  ምላሽ “ከእውነት  የራቀና  ለኢትዮጵያ መንግስት  የተንበረከከ ነው” በማለት  ከሃቅ ጋር  ለመጋፈጥ  ግርዶሹን  ገልጦ  መታየቱ  ማንነቱን  በገሃድ   እንድናውቀው  ያደረገን በመሆኑ “በጄ”  የሚያስብለው  ነው፡፡

ግና የሚኒስትሩን  መረጃ “ከጳጳሱ፣ ቄሱ”  እንዲል ብሂሉ  በመሆን ሠ ውጭ ሀገር  ተቀምጦ በአሉባልታ  ወሬ እየተመራና  በርቀት  መቆጣጠሪያ  መሣሪያ  እየታገዘ  ለማጣጣል የከጀለው  ድርጅቱ፤  ሀገራችን ላይ በተከታታይ  በሚያወጣቸው  የውንጀላ  ሪፖርቶችን  ስመለከት  ‘ምነዋ  እንደ ወገብ  ምንትስ፣ አልላቀቀን አለ?’ የሚል  ጥያቄ  እንዳነሳ  አድርጎኛል፡፡  ታዲያ  ይህን  ጥያቄዬን   ለመመለስ  ‘ለመሆኑ  ሂዩማን  ራይትስ ዎች ማነው?፣ ተግባሩስ?፣  በዘመቻ  መልክ  ኢትዮጵያን  የማጥላላት ምስጢሩስ ምንድነው?’  የሚሉ  ሌሎች  ጥያቄዎችን  አንስቶ ምላሽ  መሻት፤ ለአንባቢዎቼ  የሃቅን  ብርሃን  ፍንትው  አድረገው የሚያሳዩ  በመሆናቸው  እነሆ ብዕሬን  ከወረቀት  ጋር  አገናኝቻለሁ፡፡ መልካም ንባብ፡፡…

በፊት ለፊት  የቁም ትርጉሜው  “ሂዩማን  ራይትስ ዎች “ የሚለው  መጠሪያ   “የሰብዓዊ  መብት  ጥበቃን”  የሚያመላክት  ቢሆንም፤  ድርጅቱ  ግን ላዩ ላይ  ከለጠፈው  ስያሜ  ጋር አይተዋወቅም፡፡  ከዚህ  ይልቅ ‘በመጠሪያው  ማንነት  ጭንብል  ተጀቡኖ  ድብቅ  ፖለቲካዊ አጅንዳን የሚያራምድ ፅንፈኛ ድርጅት ነው’ የሚለው  እሱነቱ  ይበልጥ  ይስማማዋል፡፡ ክቡሩን የሰው  ልጅ  መብት  በታዛነት  ተጠልሎ  የራሱን ርዕዩተ  - ዓለማዊ  አስተሳሰብ  የራሳቸውን ነባራዊ ሁኔታ ተመርኩዘው የተለየ  አማራጭን  በሚከተሉ ሀገሮች  ላይ በኃይል  ለመጫን   የሚጥረው  ይህ አክራሪ  ድርጅት፤ የገንዘብ  ምንጩ  ጆርጅ  ሶሮስ የተባለ  አክራሪ የኒዮ - ሊበራሊዝም ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ የፈጠረው  ከበርቴ  ነው፡፡

እነ ሚስተር  ሶሮስ  ዋነኛ  ዓላማቸው  ባለረብጣ ዶላር  ያደረጋቸውን የኒዮ - ሊበራሊዝም  ርዕዮተ - ዓለም  ልዕልና  እንዳይከስምና  ማነኛውም ሀገር  በዚህ አስተሳሰብ  ብቻ እንዲመራ  የማይፈነቅሉት  ድንጋይ የለም፡፡ በዚሁ ግለሰብ  ብቻ  እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ  100 ሚሊዮን  ዶላር  ልገሳ  የተሰጠው  ሂዩማን  ራይትስ ዎች ፤ ተቀዳሚ  ተግባሩ  በራሳቸው  አቅጣጫ  ማደግ  በመጀመሩ ሀገራት ውስጥ የእነ ሚስተር ሶሮስ  ህልም  የሆነውን  የቀለም  አብዮት  በማስነሳት  ከቻለ  የመንግስት  ለውጥ  ማድረግ፤ ይህ አልሳካም  ካለው  ደግሞ  የመንግስታቱን መልካም  ስም  እንደ  “አቡነ  ዘ-በሰማያት” እየደጋገመ በሚያወጣው የሪፖርት   ጋጋታ  ማጠልሸት  ነው፡፡

ታዲያ  እዚህ ላይ  ለአንባቢዎቼ  ግንዛቤ  ግልጽ ይሆን ዘንድ፤  ሂዩማን  ራይትስ ዎች   ከኒዩ - ሊበራሊዝም  ውጭ  የራሳቸውን የዕድገት  አቅጣጫ በቀመሩ  ሀገራት ውስጥ  “ሆድ  - አደር”  ተቃዋሚዎችን በመጠቀም “ሿሚና ሻሪ”  ለመሆን  እንዲህ  “የሚዋደቅለት”  ኒዩ - ሊበራሊዝም መሠረታዊ  ባህሪው  ምንድነው?፤  በርዕዮቱ ምልከታስ  ለአፍሪካና ለኢትዮጵያ  ይበጃልን? ብሎ መጠየቅ  የግድ  ይለናል፡፡  እንደሚታወቀው የኒዩ-ሊበራሊዝም አስተሳሰብ  በአፍሪካ  ልሣነ - ምድር  ተሞክሮ  ፀሐይ  የጠለቀበት  ሲሆን፤ የሂዩማን ራይትስ ዎች  “ዙፋን  አንጋሽነትም”  በአራዳዎች  ቋንቋ “የተባለ እቁብ” ስልት  መሆኑን  እደሚከተለው  መመልከት  ይቻላል፡፡

የኒዩ  - ሊበራሊዝም  ፖለቲካዊ  - ኢኮኖሚ መሰረት፤ መንግስት  ህግና  ሥርዓትን  ከማስከበር  ውጭ  በኢኮኖሚያዊ  ጉዳዩች  ጣልቃ  መግባት  አይኖርበትም፤  ሁሉንም  ነገር ለገበያውና  ለባለሃብቱ  መተው  አለበት  የሚል ነው፡፡ ርዕዩቱ  እንደ ሚስተር ጆርጅ ሶሮስ  ዓይነት ጥቂት  ቢሊዩነሮችን መፍጠር  እንጂ፣  የብዙሃኑን  ህዝብ  ተጠቃሚነት  ከቁብ  አይቆጥርም፡፡እናም ጥቂት ዲታ ባለሃብቶችን ከመጥቀም በስተቀር አብዛኛው ህዝብ ከእነዚህ ባለሃብቶች ከሚገኝ ታክስ እንዲኖር የሚፈርድ ነው።  ታዲያ በዚህ እሳቤ መሰረት ባለፉት  30  እና 40 ዓመታት ውስጥ በአፍሪካ  ሁሉንም  ነገር ገበያውና ባለሃብቱ  ሊፈቱት  እንደማይችሉ  በገሃድ  ታይቷል፡፡

ያኔ  ኢኮኖሚያቸው  በዳዴ  ይሄድ  የነበረው  የአፍሪካ  ሀገራት  ሁሉንም  ጉዳዮች   ለገበያ   በመተው  ያተረፉት  ነገር ቢኖር፤  በኒዮ - ሊበራሊዝም  ዘራፊ እጆች  ስር ላሉት  ዓለም አቀፍ   የገንዘብ  ተቋማትና  ባንኮች  ተንበርካኪ  መሆንን ብቻ ነው፡፡ ይህም  በወቅቱ  የገንዘብ  ተቋማቱና የኒዩ  - ሊበራሊዝም  አራማጅ  ተቆጣጣሪያቸው በሀገራቱ  ውስጥ  እንደልባቸው  እንዲቦርቁ ፣ አንጡራ  ሃብታቸውን  እንዲዘርፉ፣ እነ ሂዩማን  ራይትስ ዎች   በሰው  ሀገር ገብተው  ያሻቸውን  እንዲሾሙና  እንዲሽሩ  ከማድረግ  እንዲሁም የአህጉሪቱ ህዝብ  የበይ ተመልካች  ሆኖ  ህይወቱን   እንዲገፋ ከመገደድ  ውጭ  ያስገኘላቸው  አንዳችም  ነገር የለም፡፡ እናም  በእነዚያ   ዓመታት  ኒዮ - ሊበራሊዝም  በአፍሪካ  የኢኮኖሚን ቀውስን  ከማባባለና  ጥገኝነትን ከማጠናከር  እንዲሁም በወቅቱ ለጋ  የነበረውን  የአፍሪካን   የልማት  ተስፋ  ከማጠውለግ  ውጭ  ዕድገትን  ሊያመጣ  አልቻለም፡፡

ታዲያ ይህን እውነታ  የተረዱት  የአፍሪካ  ሀገራት  የኒዮ - ሊበራሊዝም  እሳቤ  በአህጉራችን  “የቀን  ጨለማ  የዋጠው”  መሆኑን  ተገንዝበዋል፡፡  ቀደም ሲል  በልካቸው  ያልተስፋውንና በግዳጅ  እንዲለብሱት  የተደረገውን  “የአስተሳሰብ  ሸማ”  አውለቀው በመጣል፤ ከራሳቸው  ባህሪያዊ  ሁኔታ ጋር  አብሮ የሚሄድ  ልማታዊ  አመለካከትን  መቀመር  ጀምረዋል፡፡ በዚህም አፍሪካዊ ዕድገትን  በማስመዝገብ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ  ሀገራት   ውስጥ ደግሞ  ኢትዮጵያ  አብነታዊ  ተጠቃሽ ናት፡፡ እናም  ከዚህ  መሰረታዊ  ሃቅ  በመነሳት  አንባቢዎቼ  የሂዩማን  ራይትስ ዎችን በአፍሪካ  ብሎም በሀገራችን  ላይ እንደ በረዶ የሚያዘንበውን የሪፖርት   መዓት  በአህጉርና  ሀገር  በቀል  የዕድገት  ግለቶች ላይ ውኃ  ለመቸለስ  የሚያደርገውን  ጥረት  መገንዘባችሁ የሚቀር  አይመስለኝም፡፡

አዎ!  የጽንፈኛ ኒዮ - ሊበራሉ  ድርጅት  ፍላጎት  አፍሪካ ውስጥ  እንደ ቀድሞው  የስልጣን  ወንበር  አረካካቢ  ሆኖ  መዝለቅ  ነው፡፡ ይሁንና  አፍሪካን   እንደ  ድሮው  ማሽከርከር  የማይቻል መሆኑን  መገንዘብ  ይኖርበታል፡፡  አህጉሪቱ  ከእንግዲህ  በራሷ  የልማት  አቅጣጫ  እየተጓዘችና  የዕድገቷን  ፍሬዎችም  እያጣጣመች  ስለሆነ፤ ለእነ ሂዩማን ራይትስ ዎች  የማጥላላት ዘመቻ  ጆሮዋን  እንደማትሰጥ ማወቅና  አካሄዱም  የተነቃበት  እንደሆነ  ቢገነዘብ የሚጠቅመው ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም  እንዲህ ዓይነቱ ጥላሸት  የመቀባት  ሴራ  ባለፉት  20 ዓመታትም  በቻይና  ላይ ተሞክሮ  ውጤት  ሊያመጣ  ባለመቻሉ  ነው፡፡

ሆኖም ሂዩማን  ራይትስ ዎች  ትናንት  ቻይናን፣  ዛሬ ደግሞ  በራሷ  የልማት  ፕሮግሞች  ማደግ  የጀመረችው አፍሪካን   በማጥላላት  ያመጣው  ለውጥ  ባይኖርም፤ ድርጅቱ  “ዓይኔን  ግንባር  ያድርገው”  በሚል  ድርቅና  በሰብዓዊ መብት  ስም  የፖለቲካ  ሴራውን  ከማጧጧፍ  ወደ ኋላ  አላለም፡፡ ለዚህም ነው  ሰሞኑን  የእንግሊዝ  መንግስት  የሰጠነውን  እማኝነት  “እኛ  እንጂ  እናንተ  የዕርዳታ  እህል ለፖለቲካ  ጥቅም  መዋሉን  ማረጋገጥ  አትችሉም “  በማለት  የሌላ  አካልን  ክንዋኔ  በመቀማት  የራሱ  ስራ አድርጎ  የጥላቻ   አታሞውን ለመደለቅ  የሞከረው፡፡

እንደሚታወቀው  ጽንፈኛው  የእነ ሚስተር  ሶሮስ  ተላላኪ  ድርጅት  ሀገራችን  ውስጥ ይህ ነው የሚባል በይፋ  የተደራጀ  መዋቅር  የለውም፡፡ ብቸኛ  የወሬ ቋቶቹ  በንድፈ  - ሃሳብ  ደረጃ ‘ ህገ  - መንግስቱን አክብረን  እንንቀሳቀሳለን’  የሚሉ፤  ነገር ግን  በተግባር ባገኙት  አጋጣሚ  ሁሉ  ህገ  - መንግስቱን  ቀዳድደው   ከመጣል  ወደ ኋላ  የማይሉ  ተቃዋሚ  ተብዬዎችና ሀገራችን   በህዝብ ጨራሽ  ምግባራቸው  በአሸባሪነት   የፈረጀቻቸው  ቡድኖች  ናቸው፡፡  የእነዚህ ኃይሎች  ምስክርነት   ደግሞ ምን  ሊሆን  እንደሚችል ከማንም   የተሰወረ  ጉዳይ  አይደለም፡፡  ምክንያቱም እነዚህ ሃይሎች ለህዝብ  ካላቸው  የጠላትነት  ስሜት በመነሳት ያልተፈጠረን ነገር እንደተፈጠረ ፣ የተከናወነን ነገር  እንዳልተከናወነ  በመቀላመድ   በቅዥት ዓለም  ውስጥ  የሚዳክሩ  ለጥፋት  የተሰለፉ  በመሆናቸው  ነው፡፡

መዋሸትንና የሌለ ነገር  ነባራዊ ሁኔታ  መፍጠር  እንደ  መደበኛ  ስራቸው  የያዙት  የእነዚህ  የኒዮ - ሊበራሊዝም  አምሳያ  ቡድኖች ወሬ ፤ በምን ዓይነት  የሂሳብ ቀመር  የሂዩማን  ራይትስ ዎች  ማረጋገጫ  ምንጭ  ሆኖ የእንግሊዙን  የልማት  ትብብር  መስሪያ ቤትን  የመስክ ቅኝት  አላደረክም፤ ከኛ በላይ  አታውቅም እንዳስባለ “ለሰሚው  ግራ” የሚሉት  ዓይነት  እንቆቅልሽ  ነው፡፡  ዳሩ ግን  አንድ  እውነታን በእርግጠኝነት   መናገር  ይቻላል፡፡  ይኸውም ጽንፈኛው   ተቋም  በሰብዓዊ  መብት  ሽፋን  በድብቅ  የሚያራምደውን የፖለቲካ አጀንዳ  የሚያሳካ መስሎ  እስከታየው  ድረስ  የመረጃው  ምንጭ  ማንም ይሁን ምን  ዳቦን “ድንጋይ ነው”  ከማለት  የማይመለስ  መሆኑን  ነው፡፡

እስቲ  ይህን ዕውነታ በአስረጂነት ለመመልከት፣ በአንድ  ወቅት ለህዝቦች  ባለው  የወገንተኝነት  ስሜት  በዓለም  አቀፉ  ማህበረሰብ ከበሬታና እውቅና  የተቸረውን  እንዲሁም  በአሁኑ  ወቅት  ብቸኛው  የሠላም  አስከባሪ  ኃይል  ወደ መሆን  የተሸጋገረውን  መከላከያ  ሠራዊታችንን ስም  ለማጎደፍ  ወደጣረበት  የቅርብ ጊዜው  የፈጠራ  ድርሰቱ ልውሰዳችሁ፡፡

…በወቅቱ በኤርትራ  መንግስትና  በአል -ሸባብ  የሚታገዘው  አሸባሪው  ኦብነግ፣ ኦጋዴን ውስጥ  በአንድ  አካባቢ  ዜጎችን  በማስፈራራት  የፈጠራ ፊልም  ይቀርጻል፡፡ በዚህም  ያልተቃጠሉ  ቤቶችን እንደተቃጠሉ፣ ያልሞቱ  ሰዎችን  እንደ ሞቱ  አድርጎ  በማቅረብ  ለሂዩማን   ራይትስ ዎች  ያቀርባል፡፡ ድርጅቱም  ቦታው ላይ  ተገኝቶ  ሳያጣራ  የአሸባሪውን  ቡድን መረጃ  እንደ አስተማማኝ ምንጭ  በመውሰድ፤ ‘የኢትዮጵያ  መከላከያ  ሠራዊት  በኦጋዴን አካባቢ ሰብዓዊ  መብት  ጥሷል’  ይላል፡፡

እንግዲህ  ልብ በሉ!  ይህ ተግባር  የሂዩማን ራይትስ ዎች  ኢትዮጵያን  የማጥላላት  ዘመቻ  አንድ  አካል  መሆኑ ነው፡፡ ግና  ገለልተኛ ወገኖች  ሁኔታውነ ተከታትለው እንዳጣሩት፣ በጽንፈኛው  ድርጅት  የቀረበው  ሀገራችንን  የመወንጀል ሴራ  መሰረተ - ቢስና በኦብነግ የተቀነባበረ መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ ተቃጠሉ  የተባሉት  ቤቶች  በተጨባጭ  ቦታው ላይ  እንደሚገኙ  እንዲሁም  ሞተዋል  የተባሉ  ሰዎችም “ኧረ አለን፣ ለምን እንሞታለን? የሰይጣን  ጆሮ  አይስማው!”  እያሉ  ምስክርነታቸውን  ሰጡ፡፡ ሂዩማን  ራይትስ ዎች  ግን  እነሆ  አሁን  ድረስ  በጨበጣ  መረጃ “ካፈርኩ አይመልሰኝ”  እያለን  ነው -“የቅሌት  ቀን አይመሽም”  ይሏል እንዲህም  አይደል?

የአክራሪው  ኒዮ - ሊበራል  ድርጅት  ፀረ  - ኢትዮጵያ  አቋም  በዚህ ብቻ  የሚያበቃ  እንዳይመስላችሁ፡፡ በቅድመና ድህረ  - ምርጫ  2002  ወቅቶችም፤ ሲያሻው “100 ተፅዕኖ  መፍጠሪያ  መንገዶች”፣ በል  ቢለው  ደግሞ “የእርዳታ  እህል  ለፖለቲካ  ፍጆታ  እየዋለ  ነው”  በማለት የተለመደ  የውሸት  ሪፖርቶቹን  አዝንቧል— ሀገራችን ውስጥ  የቀለም  አብዮት  ለመፍጠር  የሚያስችል  ምህዳር  አለመኖሩን  ሲያረጋግጥ፡፡ በወቅቱም የመረጃ ምንጮቹ ከድርጅቱ ትርፍራፊ  ለመለቃቀም  የሚቋምጡትና “አንጋሽ” ፍለጋ  በየኤምባሲው  የሚዞሩት የመድረክ  አመራሮች ነበሩ — ሰሞነኛውን  በድርጅቱ  አዝማችነት  የተወጠነውን የቢቢሲ  ዘገባን  ያረጋገጡለት  ጭምርም፡፡

ታዲያ እነዚህ  ግልጽ  የሆኑ  የድርጅቱ   ጣልቃ  ገብነቶች  የሚያመላክቱት፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች  መንግስት  የመቀየር  ቀቢጸ - ተስፋን  ያነገበ  ፖለቲካ  አራማጅ  ድርጅት  እንጂ፤  ለሰብዓዊ  መብት  ጥበቃ ጋር የሚያገናኘው ምንም  ዓይነት ነገር  የሌለው  መሆኑን  ነው፡፡ ይሁንና እዚህ ላይ ይህ ‘ድርጅቱ በአፍሪካም  ይሁን  በሀገራችን  ላይ መቋጫ  የሌለውን  የኒዮ - ሊበራሊዝም ፕሮፓጋንዳን  ለዚህ  ተግባር   ተብለው  በተዘጋጁት  እንደ ቢቢሲ፣ ቪኦኤ  ወዘተ.  ዓይነት  ሚዲያዎች  የሚረጭበት ምስጢር  ምንድ ነው?’ የሚል ጥያቄ  ማንሳት  አግባብ  ይመስለኛል፡፡

ቀደም ሲል  ለመጥቀስ  እንደሞከርኩት፤ ጽንፈኛ  ኒዮ -ሊበራሉ ተቋም ራሱ  ከሚያራምደው ርዕዮት ውጪ  የትኛውም  አህጉርና  አህገር የራሱን አስተሳሰብ እንዲከተል አይፈቅድም፡፡ በተለይም አፍሪካና  ሀገሮቿ  ምንጊዜም የምዕራቡ ዓለም ጥገኛ  ሆነው  እንዲኖሩ የሚፈልግ ተቋም ነው፡፡ ለዚህም  ነው  ‘ለምን  ከኛ  አመለካከት  ውጪ  አደጋችሁ?’ በማለት  አፍሪካንና  ፈጣን  ዕደገቷን  የማናናቅ  አባዜ  ተጠናውቶት  የቤተክርስቲያን ስዕለት  ያለበት  ይመስል  በየጊዜው  በቀጥታ  ሪፖርት ጋጋታ  እና በእጅ  አዙር  ጋዜጠኝነት  አስገራሚ ልቦለዳዊ ትወና  በማካሄድ ላይ የሚገኘው፡፡

እርግጥ ሀገራችን  በራሷ  ልማታዊ  ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ እየተመራች  በአሁኑ ወቅት  ፈጣንና  ተከታታይ  ዕድገት  ማስመዝገቧ ‘ከኒዩ - ሊቢራሊዝም  በስተቀር  ሌሎች  አማራጮች  ለዕድገት  አያበቁም’ ብሎ  የሚያስበውን  አክራሪ  “የፖለቲካ  ድርጅት”  በአያሌው  ብስጭት  ውስጥ እንደከተተው እሙን ነው፡፡ ለዚህም ነው  ለቢቢሲው ዘገባ  ምላሽ  የሰጡትን  ሚኒስትር  ሚቼልንና  የእንግሊዝ  መንግስትን  እጅግ  ጠንካራ  በሆኑ ቃላት እየደነፋ  የወረፈው፡፡ ይሁንና  “የሽሮ  ድንፋታ  ውኃ እስኪገባበት  ድረስ  ነው”  እንዲል ታታሪው ህዝባችን፤  የሂዩማን ራይትስ ድንፋታ  ሃቅን  ተሻግሮ የትም የሚደርስ  አይደለም፡፡ ከዚህ ይልቅ  ድርጅቱ  ኢትዮጵያ  ውስጥ  ያለውን  እውነታ  ዓይኑ  ላይ ያሰረውን የጥላቻ  መሃረብ በመግለጥ  መመልከት  ያለበት ይመስለኛል፡፡

ዛሬ ሀገራችን  ውስጥ  ታሪክ  በአረንጓዴ  የልማት  ቀለም በአዲስ  መልክ  እየተጻፈ ነው፡፡ ልማታዊው መንግስታችን በሚሊዮን የሚቆጠሩ  ዜጎችን ከድህነት  አረንቋ  በማውጣት  የተሳካና ውጤታማ  የሆኑ  የልማት  ስራዎችን  በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡  እስቲ  የሚስማ ከሆነ ጥቂት  አብነቶች  ልጥቀስለት፡፡  ከ15 ዓመት  በፊት  31 በመቶ የነበረው  የትምህርት  ሽፋን ዛሬ  92 በመቶ  ደርሷል፡፡ ከ10 ዓመት  በፊት  ወደ ከፍተኛ  ትምህርት  ተቋማት  ይገቡ  የነበሩት  5 ሺህ  5 መቶ ተማሪዎች  ቁጥር  ዛሬ  አስገራሚ በሆነ ሁኔታ  ወደ  123 ሺህ  5 መቶ አሻቅቧል፡፡ በጤናው  ዘርፍም እንዲሁ  ከ15 ዓመት በፊት  የነበረው  የ22 በመቶ ሽፋን ወደ 83 በመቶ  አድርጓል፡፡ የመሰረተ - ልማት  ዝርጋታም እጅግ  ከፍተኛ በሆነ  ሁኔታ  ተስፋፍቶ  ሀገራችን  ዛሬ  ከአፍሪካ ውስጥ  በግንባር  ቀደምትነት  የስኬታማነት  መገለጫ  ሆናለች - ለዚህም ነው “አልጀዚራ”  የተሰኘው  የቴሌቪዥን  ጣቢያ  በአንድ ወቅት “ፈርሳ  በመገንባት  ላይ ያለች  ሀገር” ሲል አድናቆቱን የገለጸው፡፡…

እናንተዬ  ነገሩ  እንዴት  ነው?... ከነባራዊ ሁኔታ  ተነስቶ በራስ  ልማታዊ እሳቤ  ማደግ  ሂዩማን ራይትስ  ዎችን  ምን እንዲህ  ያሳብደዋል? - ለይስሙላም ቢሆን ‘ለሰው ልጆች መብት  ቆሚያለሁ’ የሚል ተቋም  ባያምንበትም  እንኳን፤ ህዝቦች  ሲያድጉ፣ ድህነትን  አራግፈው ወደ  ብልጽግና  ጎራ  ለመቀላቀል  ደፋ ቀና  ሲሉ  መደገፍ  እንጂ  ‘ዘራፍ  እኔ የኒዩ - ሊበራሊዝም  አሽከር’  ብሎ የልማት  እመርታቸውን ለማቀጨጭ  መሯሯጥ  የሰብዓዊ  መብት  ተናካሽነት  እንጂ፤ ምን ይሉት  ‘ተቆርቋሪነት’ ነው?...

ምንም እንኳን አክራሪ  ድርጅቱ  በዚህ  ተናካሽነቱ  ‘እኔ  ያልኩትን  በግድ  ተቀበሉኝ’ በሚል  እሳቤ  ያለ ተጨባጭ  ማስረጃ ‘የዕርዳታ  እህል  ለፖለቲካ  ጥቅም ውሏል’ እያለ  ቢዘላብድም፤ ሀገራችን  ውስጥ  እንዲህ  ዓይነት  ፍትሐዊ  ያልሆነ  አሰራር  ቢኖር  ኖሮ፣ ቀደም ሲል  የጠቀስኳቸውና  ሌሎች  ልማታዊ  ዕድገቶች  እንደማይመዘገቡ  ማወቅ  ነበረበት፡፡

ሌላው  ቀርቶ  የሚሌኒየሙን የልማት  ግቦች (MDG) ያሳካሉ ተብለው በኒዩ - ሊበራሊዝም  ሚዲያዎች ሳይቀር  ከተጠቀሱት  ጥቂት የአፍሪካ  ሀገሮች  ውስጥ  ኢትዮጵያ አንዷ  መሆኗን  ድርጅቱ  እንደ  እሬት  እየመረረውም ቢሆን  መቀበል  ነበረበት፡፡ ለምን ቢባል፤ ለታዳጊ  ሀገራት  ዕድገት  አጋዥ የሆነውን  እርዳታን  በአግባቡና  ፍትሐዊ  በሆነ  መንገድ  መጠቀም  ሳይቻል፤  ለእንዲህ ዓይነቱ  ስኬት  መብቃት  ስለማይቻል ነው፡፡ እናም  ሂዩማን  ራይትስ ዎች  በሀገራችን  ላይ የሚነዛቸው  የውንጅላ መዓቶች  ኢትዮጵያን የማይመለከቱ ብቻ  ሳይሆኑ፤  ድርጅቱ  ሀገራችንን  እርሱ  በሚፈልገው  መንገድ  ማሽከርከር ባለመቻሉ  ተስፋ  በመቁረጥ  እንዲሁም  አፍሪካዊ  የዕድገት  ተምሳሌትነታችን ስጋት  ውስጥ  ከትቶት  በጭንቀት እየተራወጠ  እንደሚገኝ የሚያመላክቱ ናቸው፡፡

ግና  ጽንፈኛው  ተቋም  ስለምን  በእኛ  ዕድገት  ይሰጋል?-እርግጥ  ለዚህ ጥያቄ  ሩቅ መጓዝ  የሚያስፈልገን አይመስለኝም፡፡ እስቲ  በቅድሚያ  የስጋቱ  ምንጮች  የሆኑትን  ጥቂት  ጉዳዮች  እንይ፡፡ በቅርቡ  ለየመንግስታቱ  ድርጅት  የልማት  ፕሮግራም (UNDP) ኢትዮጵያ  በአማካይ  በ10 በመቶ  እያደገች  መሆኑን ገልጿል፡፡ የተለያዩ  ዓለም  አቀፍ  ተቋማትም  የሀገራችንን  ምጣኔ  ሀብታዊ  ግስጋሴ  በእጅጉ  ተደምመውና  የምስጢሩን ቁልፍ  ለማወቅ  በመሻት  ላይ ይገኛሉ፡፡ መንግስት  የሚከተለው ልማታዊ የዕድገት  መስመር  ለሌሎች  አርአያ  መሆኑን  በመግለፅም አድናቆታቸውን እየቸሩ  ነው፡፡

አዎ! እነዚህን  ነባራዊ  ክስተቶች በልማታዊ  ዴሞክራሲያዊ  መንግስት  አስተሳሰብ  የመጡ እንጂ፤  በኒዩ - ሊበራሊዝም  ፖለቲካዊ  - ኢኮኖሚ  ርዕዮተ  - ዓለም  የተገኙ  ባለመሆናቸው  ሂዩማን  ራይትስ ዎች  መስጋቱ  አግባብነት  አለው፡፡  ምክንያቱም  እንዲህ ዓይነቱ ሀገር  በቀል  አብነታዊ  ዕድገት  በጽንፈኞች  አመክንዩ “ይህች  ባቄላ ያደረች እንደሆን  አትቆረጠምም” እንደሚባለው  ስለሆነ ነው፡፡

እርግጥም ኢትዮጵያ  አፍሪካዊ  የልማት  ምሳሌ  ሆና  መውጣቷ፤ እስካሁን ድረስ  በኒዩ - ሊበራሊዝም የጨለማ  መዳፍ  ስር የሚገኙ  ሌሎች  ሀገሮችም  ዓይናቸውን  ይገልጣሉ  ተብሎ ስለሚታሰብ፤ ድርጅቱ  በሀገራችን  ላይ በሰበብ  አስባቡ  በሰብዓዊ  መብት  ሽፋን በሚያወጣቸው  ከሃቅ ያፈነገጡ ሪፖርቶች  በስጋት ተውጦ ቢያላዝን የሚገርመን  ሊሆን አይችልም፡፡

ይህን እንጂ  ሂዩማን ራይትስ ዎች  በዚህ ዓይነት  ሪፖርት  ፍብረካ  እንዲሁም አህጉርና ሀገር  በቀል  በሆኑ  አስተሳሰቦች  የተገኙ  ተጨባጭ  ለውጦችን  የማንኳሰስ  ተግባሩ  ጊዜው  ያልፈበትና የተነቃ  ድርጊት  መሆኑን  መቼም ቢሆን መዘንጋት የለበትም፡፡ እናም  ምንም ቢሆን   ተቋሙ  የሰለጠነ  ማህበረሰብ አካል  እንደመሆኑ  መጠን፣ ልክ  የዓላማ  አጋሩ  ቢቢሲ  ሰር ቦብ  ጊልዶፍን እንደጠየቀው ሁሉ፣ እርሱም  ይህንኑ  ማድረግ  ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡ በመሆኑም  እስከ ዛሬ  ድረስ “የውሸት  አባት”  ከሆኑ  ተቃዋሚዎች  እንዲሁም ከአሸባሪ ቡድኖች የቃረማቸው አሉባልታዎች  እንዳሳሳቱት  በማመን  የኢትዮጵያን ህዝብና  መንግስት  በይፋ  ይቅርታ  መጠየቅ  አለበት፡፡

ከዚህ ውጪ ዓይኑንና  ጆሮውን ደፍኖ ‘እኔን  ብቻ ስሙኝ’ የሚል ከሆነ፤ ማንም የሚሰማው  አካል  እንደማይኖር መረዳት  ይኖርበታል፡፡  በሪፖርት  ናዳ  የአንድን  ሀገር  ልማታዊ  እመርታ  ማቀጨጭ  ስለማይችልም፤ ላይሳካለት  በባዶ ሜዳ  ላይ  ባይደክም የተሻለ  ነው፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲያዊና  ሰብዓዊ መብቶች  ያልተከበሩባቸውን አምባገነናዊ ሀገራት  የኒዮ - ሊበራሊዝም ተከታዩች መጠቀሚያ  በመሆናቸው  ብቻ  ትንፍሽ ለማለት የማይፈልገው  ይህ ተቋም፤  እንደ  ኢትዮጵያ  ያሉ ከሀገራቸው ተጨባጭ  ሁኔታ  አኳያ  የልማት  ፖሊሲና  ስትራቴጂን  ነድፈው  ዓለም አቀፍ  ዕውቅና  ያስገኘን  ዕድገት  ያስመዘገቡ  ሀገራትን  ‘ጠብ ያለሽ  በዳቦ’ እያለ  ለማንቋሸሽ የሚያደርገው  ጥረት  አንድም  ስንዝር  የሚስኬደው  አይደለም፡፡ ምክንያቱም  በዚህ ዓይነቱ በሁለት ቢላዋ የመብላት ልዩ  የስም ማጥፋት ዘመቻ  የሚንበረከክ  አፍሪካዊ  ሀገር ባለመኖሩ ነው፡፡

ታዲያ  ሀገራችንም  ሆነች  ህዝቦቿ  ለእንዲህ ዓይነቱ  ያረጀ  ያፈጀ  ፕሮፓጋንዳ  እንኳንስ  ሊንበረከኩ ቀርቶ ጉዳዩን የሚሰሙበት ጊዜም  የላቸውም፡፡ እናም  ሂዩማን  ራይትስ ዎች እስካሁን ድረስ “ከዙፋን  አንጋሽነት” ቅዥቱ ያልተላቀቀ ከሆነ፤ አሁንም  ኢትዮጵያ ውስጥ  በውጭ  ኃይሎች ተፈትፍቶ  የሚቦካ  የፖለቲካ  ምህዳር  የሌለ  መሆኑን  መገንዘብ ይኖርበታል —ኢትዮጵያዊያን በታሪካቸው  ለእንዲህ  ዓይነቱ  የባዕዳን የእጅ  አዙር  ቅኝ  አገዛዝ  ተንበርካኪዎች  ሆነው  አያውቁምና፡፡ እናም  የሀገራችንንና  የልማታዊ  መንግስቷን ጥረት  ለማኮስመን  የሚያደርጋቸው ግልጽና  ስውር  የወሬ ዘመቻዎች  የበረሃ  ጩኸት  መሆናቸውን  ተገንዝቦ፤ ላይሳካለት በክንቱ  ባይደክም የሚሻለው መሆኑን  እንደ ዜጋ  በማያሻማ  ቋንቋ  ልንነግረው  ይገባል፡፡

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 284 guests