አራት አገሮች ዜጐቻቸው ከሊባኖስ እንዲወጡ ጠየቁ
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 23/2004 (ዋኢማ) - ሳዑዲ አረቢያ፣ ዩናይትድ ዓረብ ኤሚሬትስ፣ ካታርና ኩዌት የሶሪያ ግጭት ወደአካባቢው የመዛመት አዝማሚያ ማሳየቱ ከፈጠረባቸው ስጋት በመነሳት የሶሪያ ጐረቤት በሆነችው ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ ዜጐቻቸው እንዲወጡ ጥሪ ማድረጋቸውን የአሶሺየት ፕሬስ ዘገባ አመል ክቷል።
አራቱ አገሮች ለዜጐቻቸው ጥሪውን ያስተላለፉት በርካታ ሱኒ ሙስሊሞች በአገሪቱ ውስጥ ተሰሚነቱ ከፍተኛ እንደሆነ በሚነገርለት አንድ የሺያ(ሺያይት) ጐሳ እየታፈኑ መወሰዳ ቸው ከተገለጸ በኋላ መሆኑንም ዘገባው ጨምሮ ገልጿል።
አልማግዳድ የተባለው የሊባኖስ ሺያ ጐሳ ከሶሪያ አማፅያን ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የተጠረጠሩ 20 ሱኒዎችን ማገቱን ማስታወቁ ተገልጿል። ከእነዚህ መካከል አንዱ «ፍሪ አርሚ» በሚል ስም የሚታወቀው ተቃዋሚ ተዋጊ ኃይል ሻምበል እንደሆነ ታውቋል። ከታገቱት መካከል አንዱ የቱርክ ነጋዴና አንድ የሳዑዲ አረቢያ ዜጋ እንደሚገኙባቸውም ተገልጿል።
በአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ መሠረት አልማግዳድ የተባሉ የሺያ ጐሳ ሱኒ ሙስሊሞችን ያፈነው ደማስቆ ውስጥ በአማፅያ ቡድን ተዋጊዎች የታገተ አባላቸውን አፃፋ ለመመለስ ነው። በሌላ በኩል የሳዑዲ አረቢያው የሙስሊም አገሮች ትብብር ድርጅት የመሪዎች ጉባዔ ሶሪያን ከአባልነት ማገዱ ተገልጿል። ይህንኑ በሚመለከት የሙስሊም አገሮች ትብብር ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኢክሜሊዲን ኢህሳኖግሉ በሰጡት መግለጫ ድርጅቱ ሕዝቡን ለሚገድል መንግሥት ቦታ እንደሌለው አረጋግጠዋል።
እንደ አዲስ ዘመን ዘገባ የሳዑዲ አረቢያው የሙስሊም አገሮች ትብብር ድርጅት የመሪዎች ጉባዔ ሶሪያን ከአባልነት በማገድ የወሰደው እርምጃ የፕሬዚዳንት ባሻር አልአሳድ መንግሥት በዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱን አመላካች እንደሆነም በዘገባው ተመልክቷል። ቀደም ሲልም የዓረብ ሊግ ሶሪያን ከአባልነት ማገዱ ይታወቃል።
በአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ መሠረት የሶሪያ መንግሥት የጦር አውሮፕላኖች ከሰሜናዊ ከተማ አሌፖ በስተሰሜን በምትገኘው አዛዝ ከተማ ላይ የፈፀሙትና ሰላሳ ሰለማዊ ሰዎችን የገደሉበት ጥቃት በሊባኖስ ዜጐች ላይም ጉዳት ማድረሱን ጦርነቱ ወደጐረቤት አገሮች በመዛመት ላይ መሆኑን አመላካች ነው። በዚህ አደጋ ሰባት ሊባኖሳውያንም መገደላቸው ታውቋል።
| < Prev | Next > |
|---|


