ከሶማሌ ክልላዊ መንግስት የተሰጠ የሀዘን መግለጫ

  • PDF

የሶማሌ ክልላዊ መንግስትና ህዝብ አገራችንን ላለፉት ሃያ አንድ አመታት በከፍተኛ ብስለትና ብቃት ሲመሩ የቆዩት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ባደረባቸው ህመም ለመፈወስ በውጭ አገር በህክምና ሲረዱ ከቆዩ በኋላ በትናንትናው እለት ከምሽቱ 5፡40 በድንገት ማረፋቸው ሲሰማ ደንግጠናል።

የኢፌዴሪ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከድህነትና ኋልቀርነት ለማላቀቅ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ በቅንነትና በታማኝነት ሀገራቸውን በማገልገል ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ያሳዩ መሪን ህልፈት ስንሰማ የተሰማንን ከፍተኛ ሀዘን ስንገልፅ በተሰበረ ልብ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከምንም ነገር በላይ ሀገራቸውን የሚወዱ፣ ስለዚህች ሀገርና ህዝብ የላቀ ራዕይ የነበራቸው፤ ተስፋቸውንም እውን ማድረግ የጀመሩና አስተማማኝ ውጤት ማምጣት የቻለ ድርጅትና መንግስት የገነቡ፤ ኢትዮጵያ ሀገራችን በዓለም አደባባይ ከፍ ብላ እንድትታይ ማድረግ የቻሉ፣ ሀገራችን ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አቅጣጫ እንድትይዝ ጥራት ያላቸው ፖሊሲዎችና እስትራቴጂዎች በመንደፍ የህዳሴውና ለለውጥ ጉዟችን መሰረት የጣሉ ታላቅ የህዝብ ልጅና የማይረሱ መሪ ናቸው።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በሀገራችን ህገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲገነባ፣ የህዝቦች እኩልነትና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ህገ-መንግስታዊ ዋስትና አግኝተው ተከብረውና ተረጋግተው እንዲኖሩ ያደረጉ፣ ኢትዮጵያ ሀገራችንን በአዲሱ ፅኑ ዴሞክራሲያዊ  መሰረት ላይ ያዋቀሩ ታላቅ አርቆ አሳቢና አስተዋፅ መሪ ነበሩ።

ለሀገራችን ፈጣን ዕድገት መመዝገብ፣ ለሀገሪቱ ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዝግጅት ወሳኙን ሚና የተጫወቱ የጉዞውና የህዳሴያችን ለውጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያስቻሉ ታላቅ የሀገርና የህዝብ ልጅ ነበሩ።

የታላቁ መሪያችን በህይወት ዘመናቸው ራዕያቸው የነበረውን የሰላም፣ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት እሳቸው ቢሞቱም ራዕያቸውን እውን ለማድረግ የሱማሌ ክልል መንግስትና ህዝብ ቃል ገብተዋል።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሶማሌ ክልል ህዝብ ከአርብቶ አደርነት ወደ ከፊል አርብቶ አደርነት እንዲሸጋገር የሚያስችል ስራዎችን ሲመሩ የቆዩ ታላቅ መሪ ሲሆኑ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት ዘመናቸው ሰንቀዋቸው የነበሩትን ሀገራዊና አህጉራዊ ራዕይ ለማስፈፀም የክልሉ ህዝብና መንግስት ራዕያቸውን ለማስፈፀም ይተጋል።

ስለዚህ የሶማሌ ክልልዊ  መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዲ መሀመድ ዑመር፣ የክልሉ ካቢኔ እና የክልሉ ህዝብ፣ በታላቁ መሪ በኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት የተሰማንን ከፍተኛ ሀዘን በተሰበረ ልብ ስንገልጽ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤተሰቦችና ወላጆች ሁሉ መጽናናትን ተመኝተዋል።


ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰጠ የሀዘን መግለጫ


ላለፉት 21 ዓመታት ኢትዮጵያን በከፍተኛ የአመራር ብስለትና ብቃት ሲመሩ የነበሩት የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዜና ዕረፍትን ተከትሎ መላው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አመራርና ሰራተኞች እንዲሁም በውጭ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ቆንጽላ ፅህፈት ቤት ባልደረቦች ከፍተኛና መሪር ሀዘን ተሰምቷቸዋል።

ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን ከድህነትና ኋላቀርነት ለማላቀቅ ሌት ተቀን ያለመሰልቸት ሲደክሙና በቅንነትና በታማኝነት ሀገራቸውን ሲያገለግሉ ቆይተው የልማትና የተስፋ ብርሃን ያሳዩትንና ፈሩን ያስያዙን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ዕረፍት ስንሰማ እጅግ በተሰበረ ልብ መሆኑን ለመግለፅ እንወዳለን።

እኚህ ታላቅ መሪ የሀገራቸውን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያደረጉ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ልማት፣ ዴሞክራሲና መልካም አስተዳደር ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና አግኝተው ተግባራዊ በማድረግ ፋና ወጊ ተግባራትን የፈፀሙና ሀገሪቱን በአዲስ ፅኑ መሰረት ላይ ያዋቀሩ መሪ እንደመሆናቸው ዕረፍታቸው ታላቅ ድንጋጤን ፈጥሮብናል።

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድና ለመላው አፍሪካ  ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ መስፈን የማይዘነጋ አስተዋፅኦ አበርክተዋል። በመሆኑም የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያለጊዜ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ሀዘኑን የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ማህበረሰብ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ በእኚህ አርቆ አሳቢና የለውጥ መሪ የጀመረችውን ሰላማዊና የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች። ይህን አስቸጋሪ ወቅትም በአስተማማኝ ሁኔታ የምታልፍና ለዘላቂ ልማትና ዕድገት እንዲሁም ተጠቃሚነት ከመላው ወዳጆቿ ጋር የምትንቀሳቀስ ትሆናለች። የጠቅላይ ሚኒስትራችንን የጤንነት ሁኔታ ከሰሙ በኋላ መልካም ምኞትና ድጋፋቸውን ለገለፁልን የተለያዩ አገራት መንግስታትና ወዳጆች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምስጋናውን ያቀርባል።

በዚህ አጋጣሚ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እየገለፀ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ቤተሰቦችና ወዳጆች መፅናናትን ይመኛል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ

ከኢትዮጵያ ሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ( ኢሶህዴፓ)
የተሰጠ የሃዘን መግለጫ

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የሀገራችንን ህዝቦች ከኋላቀርነትና ከድህነት እንዲሁም ከድንቁርና ለማላቀቅ በቁርጠኝነት፤ በቅንነትና በታማኝነት ሀገራቸውን መርተው የለውጥ ተስፋን ያሳዩን ታላቅ የሀገርና የህዝቦች ወዳጅ መሪ ነበሩ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ የኢትዮጵያ ብሄር ፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻቸው ህገ - መንግስታዊ ዋስትና አግኝተው በአጠቃላይ የሀገራችን ህዝቦች በመፈቃቀርና በመፈቃቀድ ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖራቸው ያደረጉ ቆራጥ መሪ ነበሩ።

ክቡር ጠቅላይ መለስ ዜናዊ ሀገራችንን በከፍተኛ ደረጃ ለመለወጥ ብሎም ከድህነት በማላቀቅ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ተርታ ለማሰለፍ የታላቁ የዕድገትን ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ እውን እንዲሆንና ሀገራችን የጀመረችው ተከታታይን ፈጣን ዕድገት የማስመዝገብ ጉዞ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ያደረጉ የኢትዮጵያ ጀግና ነበሩ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሀገራችን በልማታዊ ዴሞክራሰያዊ አቅጣጫ እንድትጓዝ ጥራት ያላቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን ነድፈው በብቁ አመራራቸው በገነቧችው ድርጅት አማካይነት ተግባራዊ ማድረግ የቻሉና በሀገራችን በመካሄድ ላይ ያለውን ታላቅ ሀገራዊ የህዳሴ ጉዞ በመሰረ አቅጣጫ እንዲጓዝ ያደረጉ ታላቅ መሪ ነበሩ።

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ኢትዮጵያ ለሶማሊያ ፤ ለደቡብና ለሰሜን ሱዳን ፤ ለሩዋንዳ ፤ለብሩንዲ ፤ ለላይቤሪያ ዘላቂ ሰላም ታሪክና መላ አፍሪካውያን የማይዘነጉት አስተዋጽኦ እንድታበረክት ያደረጉ ተላቅ ነበሩ።


ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የአፍሪካ ሀዝቦች ድምጽ እንዲሰማ፤ በአፍሪካ በንግድና በልማት በዴሞክራሲ በመልካም አስተዳደር በሰላምና መረጋጋት አቅጣጫ እንድትጓዝ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉ ታላቅ የአፍሪካ ልጅ ነበሩ።

ድርጅታቸን ኢሶህዴፓ በክቡር ጠቅላይ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን ዓላማችንም አንድ አርቆ አሳቢ አዕምሮና የለውጥ ሐዋርያ እንዳጣች በጽኑ ሃዘን መንፈስ ይገነዘባል።

ዛሬ ኢትዮጵያ እና ወዳጅ አፍሪካውያን ሁሉ ታላቁን የለውጥ ሀዋርያ የሆነውን ልጃቸውን ማጣታቸው፣ ዛሬ ኢትዮጵያና የአፍሪካ ትንሳኤ ያበሰረው አዲስ የአመራር ትውልድ፣ አርቆ አሳቢ መሪያቸውን መነጠቃቸው፣ ከፍተኛ የህሊና ጉዳት ያደረሰባቸው ቢሆንም ከመቼውም ጊዜ በላቀ ሁኔታ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስን የለውጥና የሀገር ግንባታ ራዕይ ተግባራዊ ለማድረግ በከፍተኛ ቁርጠኝነትና የአንድነት መንፈስ ልንረባረብ የምንገደድበት ወቅት ላይ እንገኛለን።

ድርጅታችን ኢሶህዴፓ ይህ አስቸጋሪ ወቅት በአስተማማኝ ሁኔታ ታልፎ አገራችንን በእርግጥም የተነደፉት የለውጥ ራዕይ ተግባራዊ እንድታደርግ ከመቼውም ጊዜ በላቀ አንድነትና የትግል መንፈስ እንድንረባረብ ጥሪውን ያቀርባል፤ በዚህ አጋጣሚ ለመላው የሀገራችን ህዝቦችና ለታላቁ መሪያችን የአቶ መለስ ዜናዊ ቤተሰቦች መፅናናት ይመኛል።

የኢሶህዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት