ከኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰጠ ድርጅታዊ መግለጫ
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባላትና
መላ የትግላችን ወዳጆች
በዛሬው ዕለት ድርጅታችንን ገና ከወልደቱ በመምራት ለታላቅ አገራዊ ለውጥ ያበቃንና በአገራችን ታሪክ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያስቻለን ታላቁ የድርጅታችን መሪ ጓድ መለስ ዜናዊ ለእልፈተ ህይወት በመብቃቱ የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተሰማውን ከፍተኛ ሃዘን ይገልጻል።
ዛሬ በእርግጥም ድርጅታችንና መላ የአገራችን ህዝቦች ታላቁን የለውጥ መሪያችንን ተነጥቀናል። የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በድርጅታችን ሊቀመንበር በጓድ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማውን ልባዊ ሃዘን እየገለጸ ለመላ የአገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላት እንዲሁም ለመላ ቤተሰቦቹ ከፍተኛ መጽናናትን ይመኛል።
የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ገና ከውልደቱ አመራር እየሰጠ ለዚህ ያበቃው ኢህአዴግና መላ አባላቱ በድርጅታችን ታላቅ መሪ ከዚህ ዓለም በሞት መለየት ከፍተኛ ምሬትና ሃዘን የሚሰማን ቢሆንም በታላቁ መሪያችን አኩሪ ስራና ጥሎልን ባለፍው ትክክለኛና የጠራ የትግል መስመር ጸንተን በመታገል ራዕዩን እውን ለማድርግ በከፍተኛ ቁርጠኝነት መነሳታችንን እንገልጻለን።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች፤
የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባላትና
መላ የትግላችን ወዳጆች
የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ከምንም ነገር በላይ የለውጥ ሃሳቦችን በማፍለቅና እነዚህን ተግባራዊ የሚያደርግ ጠንካራ ድርጅትና መንግስት በመገንባት የሚያምንና ይህንኑም በተግባር ላይ ያዋለ ጽኑ የህዝብ ልጅ ነበር።
መሪያችን ጓድ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን በእውቀትና በዘመናዊ መንገድ ብቻ መምራት እንደሚቻል አውቆ ሁሌም ራሱን ለማስተማርና በጥረቱም ያካበተውን እውቀትና ልምድ ኢትዮጵያን ለመለወጥ በከፍተኛ የትግል ጽናት ተግባራዊ ያደረገ ታላቅ መሪ ነበር።
ከድህነትና ከመሃይምነት በላይ ጠላት የለም ብሎ የሚያምነው ጓድ መለስ ዜናዊ ዕድሜውን በሙሉ ድህነትን፤ መሃይምነትንና ኋላቀርነትን ሲፋለም ኖሯል።
ድህነት የሚረታው በጠራ የትግል መስመር እየተመሩ ነው ብሎ በማመን ድርጅቱን ጥራት ያለው የትግል መስመር ባለቤት ያደረገ ታላቅ የለወጥ ሃዋርያ ነበር።
የመሃይምነት ተራራ የሚናደው በትምህርት ጥይት ነው ብሎ በማመን በአገራችን ዘመናዊ ትምህርትን ወደር በሌለው ደረጃ ያስፋፋ ታላቅ የህዘብ ልጅ ነበር።
ታላቁ የድርጅታቸን መሪ ጓድ መለስ ዜናዊ ድርጅታቸን በየምዕራፉ ያጋጠሙትን ፈተናዎች ሁሉ በብስለትና በጽናት እንዲያልፍ ያስቻለ በሳልና አርቆ አስተዋይ መሪ ነበር።
በአገራችን አምባገነናዊ አገዛዝ ተወግዶ ህዝቦች ለፍትህና ለእኩልንት እንዲበቁ በተካሄደው ትግል ጓድ መለስ ዜናዊ ብቁ ፖለቲካዊ ፤ ወታደራዊና ድርጅታዊ አመራር ተሰጥቷል። የደርግ መንግስት ተገርስሶ በአገራችን የሽግግር መንግስት ከተመሰረተ በኋላ በአንድ በኩል ኢትዮጵያ ለአዲስ ዴሞክራሲያዊ ህገ-መንግስት እንድትበቃ፤በሌላ በኩል ከዕዝ ኢኮኖሚ ወደ ገበያ ኢኮኖሚ የሚደረገው ሽግግር ሰላማዊና ህብረተሰባዊ መናጋት በሌለበት አኳሃን እንዲፈጸም ለማድረግ ያስቻለ ብቁ አመራር ሰጥቷል።
ጓድ መለስ ዜናዊ በአገራችን የሽግግሩ ሂደት አብቅቶ በህዝብ ምርጫ ዴሞክራሰያዊ መንግሰት ከተመሰረተ በኋላ ፌዴራላዊ ስርዓት በመገንባትና የመጀመሪያውና ሁለተኛው የልማት መርሃ ግብር በተግባር ተተርጎሞ አገራችን በፈጣን ዕድገት አቅጣጫ እንድትረማመድ ውጤታማ አመራር ሰጥታል።
በመቀጠልም እኛን በመሰለ ህብረተሰብ የሚያጋጥመውን የእድገት መገታት መሰረታዊ መንስዔ በማጥናት ድርጅታችንና አገራችን በማያቋርጥ የተሃድሶ አቅጣጫ እንዲራመዱ በሳል አመራር ሰጥቷል። ጓድ መለስ መቼም ቢሆን ከትምህርት የማይቦዝነውን ብሩህ አእምሮውን በመጠቀም አገራችን ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት ያረጋገጠችውን ፈጣን እድገት በመሃንዲስነትና በቀያሽነት ብቻ ሳይሆን ሰርቶ በሚያሰራ ብቁ አመራር ተግባራዊ ለማድረግ አስችሎናል። ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ ደግሞ ታላቁ የድርጅታችን መሪ አገራችንን ለመለወጥ ያስችላል ብሎ ያመነበትንና ኢትዮጵያውያን ተረባርበን ተግባራዊ ልናደርገው የምንችለውን የእድገትና የትራንስፎርሜሽን እቅድ ነድፎ ለሁለት ዓመታት ያህል ከህመሙ ጋር እየታገለ ተግባራዊ ለማድረግና ከፍተኛ ውጤት ለማምጣት ሲረባረብ ቆይቷል።
የድርጅታችንን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ድህነትንና ኋላቀርነትን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት ወሳኙን ርብርብ ለዘመናት በተዘነጉት ገጠሮችና በአርሶ አደሩ አካባቢ እንዲጀመር አበክሮ አስተምሯል፤ ተግባራዊ አመራርም ሰጥቷል። እነሆ ኢትዮጵያ የረሃብ ተምሳሌትነቷ ማብቃት አለበት ብሎ የተነሳው መሪያችንና ድርጅታችን ከኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ ድህነት ከገጠር ለመመንገል ያልተቆጠበ ርብርብ በማድረግ ኢትዮጵያ በርግጥም የዳቦ ቅርጫት የምትሆንበትን አረንጓዴ ልማት በገጠር አቀጣጥሏል። አርሶ አደሩን ከመሬቱ ለማፈናቀል የተደረጉ ጥርትችን ሁሉ በፅናት ተፋልሞ በማሸነፍ ዛሬ የአገራችን አርሶ አደሮች የዘመናዊ ግብዓትና ማዳበሪያ ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ ኑሮአቸውንም ደረጃ በደረጃ እንዲለውጡ በሳል አመራር ሰጥተዋል።
ጓድ መለስ ዜናዊ በከተሞችም የኢንዱስትሪና የአገልግሎት ሴክተሩ እንዲነቃቃና ተወዳዳሪ እንዲሆን፣ ዜጎች ሰርተው የሚበለፅጉባት ኢትዮጵያ እንድተፈጠርና በካፒታላቸውና በእውቀታቸው ተጠቅመው በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርትና አገልግሎት የሚያቀርቡ አገራዊ ባለሀብቶች እንዲፈጠሩ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል። ዜጎች በራሳቸው ተማምነው ከድህነት ለመውጣት በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ተደራጅተው እንዲረባረቡና ለአገራቸው ልማትና እድገት የድርሻቸውን እንዲወጡ መሰረት የጣለ መሪም ነበር።
የመላ ኢትዮጵያውያን የዘመናት ህልም የሆነውን የአባይን ወንዝ ለኢትዮጵያ ልማት ለማዋል ባዘጋጀው እቅድና ባካሄደው ተግባራዊ እንቅስቃሴ "አባይን የደፈረ ጀግና" የሚል ስም ያተረፈው ታላቁ የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ የዘመናዊ መሰረተ ልማት ባለቤት እንድትሆን ሌት ተቀን ተረባርቧል። የስልክና የኤሌክትሪክ፣ የመኪና መንገድና የባቡር መሰረተ ልማት ግንባታ እንዲጀመርና እንዲስፋፋ ያስቻለ ብቁ አመራር ሰጥቷል። ጓድ መለስ ዜናዊ በሰጠው አመራር ኢትዮጵያ የድህነትና የኋላቀርነት ተምሳሌት መሆኗ እየቀረ በዓለማችን በፈጣን እድገታቸው ከሚታወቁ ጥቂት አገሮች አንዷ እንድትሆን አብቅቷታል።
የድርጅታችን ሊቀመንበር ጓድ መለስ ዜናዊ በድርጅታችንና በአገራችን ውስጥ ከተጫወተው የበሰለ የአመራር ሚና ባሻገር ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከተ፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች የአፍሪካ ህዝቦች ድምፅ እንዲሰማ የተሟገተ፣ በዚህ ታላቅ የአመራር ሚናውም በመላው የአፍሪካ ህዝቦች ዘንድ ታላቅ አክብሮትን ያፈራ በዓለምም ደረጃ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያተረፈ ታላቅ መሪ ነበር።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦች
መላ የኢህአዴግ አባላትና
መላ የትግላችን ወዳጆች
ጓድ መለስ ዜናዊ መታመሙ ከተሰማ ጀምሮ ስለደህነቱ ጭንቀታችሁንና መልካም ምኞታችሁን ስትገልፁ መቆየታችሁ የሚታወስ ነው። በዚህ ወቅት የኢህአዴግ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ መላ የአገራችን ህዝቦችና የድርጅታችን አባላት በመሪያችን በጓድ መለስ ዜናዊ ህልፈተ ህይወት ለደረሰባችሁ መሪር ሀዘን መፅናናትን ይመኛል።
የተከበራችሁ የአገራችን ህዝቦችና የትግላችን ወዳጆች!
በታላቁ መሪያችን በጓድ መለስ ዜናዊ ሞት የተሰማን ሀዘን እጅግ ጥልቅ ቢሆንም በርሱ ራዕይና ብቁ አመራር በአገራችን የተጀመረው የለውጥና የእድገት ብሩህ ተስፋ ህያው ሆኖ እንደሚቀጥል የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ያረጋግጣል። በአገራችን የተጀመረው ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በላቀ ውጤታማነት እንዲቀጥል ለማድርግ ከዚህ በፊት ከታላቁ መሪያችንና ከድርጅታችን ጎን ተሰልፋችሁ አንፀባራቂ ድሎችን እንዳስመዘገባችሁ ሁሉ ዛሬም ለበለፀገችና ለዳበረች ኢትዮጵያ ግንባታ የጀመራችሁትን ተጓደሎ በፅናት እንድትቀጥሉ የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በድጋሚ ጥሪውን ያቀርባል።
የተከበራችሁ የኢህአዴግ አባላት!
መሪያችንን በማጣታችን ከፍተኛ ሃዘን ቢሰማንም እርሱ ጥሎልን ያለፈውን ጠንካራ ድርጅትና መንግስት አጥብቀን ይዘን በፅናት ራዕያችንን ለማሳካት የመረባረብ ድርጅታዊ ባህላችንን ዛሬም ተግባራዊ እንደምናደርግ እሙን ነው። የመሪያችን የጓድ መለስ ዜናዊ ራዕይ ዛሬ የመላ የድርጅታችን አባላትና የ80 ሚሊየን የአገራችን ህዝቦች ራዕይ ሆኗል። በፈጠርነው ጠንካራ ድርጅትና በመሰረትነው ልማታዊ መንግስት እየተመራን የድርጅታችንን መሪ ፈለግ ተከትለን የጋራ ራዕያችንን ተግባራዊ ለማድረግ እንዳለፉት አመታት ሁሉ ዛሬም በፅናት እንራመድ።
የመለስና ኢህአዴግ ራዕይ ህይው ሆኖ ይቀጥላል!!
የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም
| < Prev | Next > |
|---|


