ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለፁ
አዲስ አበባ ነሀሴ 14/ 2004/ዋኢማ/ - የኢፌዲሪ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ሞት የተሰማቸውን ሃዘን ገለፁ።
አቶ ሃይለማርያም የቅዱስነታቸውን ሞት ተከትሎ በጠቅላይ ቤተክህነት በተዘጋጀው የሃዘን መግለጫ መዝገብ ላይ ነው የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን የገለፁት።
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ባለፉት 20 ዓመታት በተካሄደው የሰላምና የልማት ግንባታ እንቅስቃሴ ውስጥ ግንባር ቀደም ሚና የነበራቸው ታላቅ አባት ነበሩ ነው ያሉት።
በአለም አቀፍ መድረክ የነበራቸውን ተሰሚነት በመጠቀምም ኢትዮጵያን ለማስተዋወቅ ያበረከቱት አስተዋፅኦ ታሪክ የማይረሳው እውነት ነው ብለዋል።
ፓትሪያርኩ ኤች አይ ቪ ኤድስን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥም አባታዊ ሃላፊነታቸውን ለመወጣት ሲተጉ እንደነበረ አቶ ሃይለማሪያም ተናግረዋል።
በተመሳሳይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ በብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ እረፍት ጥልቅ ሃዘን እንደተሰማቸው፤ የሮማ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ቤኔዲክት 16ኛ ገለፁ።
ሊቀ ጳጳሱ በላኩት የሃዘን መግለጫ ቅዱስነታቸው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና በካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን ግንኙነታቸውና ወዳጅነታቸው እንዲጠናከሩ ያደረጉት ጥረት ከፍተኛ እንደነበር አውስተዋል ።
በታላላቅ ዓለም አቀፍ መድረኮች ላይም የእምነት ተቋማት ለሰላም መከበር በጋራ እንዲሰሩ ያደረጉት አስተዋፅኦ የላቀ ነበር ብለዋል።
ቤተ ክርስቲያናቸው በፓትርያርኩ ድንገተኛ ሞትም ማዘኗን ገልፀው፤ ለእምነቱ ተከታዮችም መፅናናትን እንደተመኙ የዘገበው ኢዜአ ነው ።
| < Prev | Next > |
|---|


