በነገው እለት 7 ሺ 300 የጋራ መኖሪያ ቤቶች በእጣ ይከፋፈላል
አዲስ አበባ ነሃሴ 12/2004/ዋኢማ/- በነገው ዕለት የልደታ መልሶ ማልማት የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ጨምሮ 7ሺ 300 ቤቶች በእጣ እንደሚከፋፈሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮንስትራክሽንና የቤቶች ልማት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ጌታቸው ኃይለማሪያም ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ነገ እጣ ከሚወጣባቸው ቤቶች አብዛኞቹ ስቱዱዮና ባለ 1 መኝታ ናቸው።
በተሻለ ጥራት ከተሰሩት የልደታ መልሶ ማልማት 1ሺ 990 ቤቶች መካከል 1ሺ 859 የሚሆኑት እጣ ይወጣባቸዋል በማለት ተናግረዋል።
እጣው የሚወጣላቸው እድለኞች ከሰኞ ጀምሮ ስም ዝርዝር በጋዜጣና በተለያዩ ድረ ገጾች ይፋ እንደሚሆን ጠቁመው፤ የቤት ርክክብ ውሉን በ1 ወር ጊዜ ውስጥ መፈፀም እንደሚገባም አሳስበዋል።
ውሉን የማይፈጽሙ እድለኞች በተሰጠው ጊዜ ውስጥ የማይዋዋሉ ከሆነ የማይስተናገዱ በመሆናቸው ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ኃላፊዎቹ ተናግረዋል።
በእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ መሰረት በከተማውው ውስጥ 95ሺ ቤቶችን ለመገንባት የታቀደ መሆኑን ገልፀው፤ በአሁኑ ወቅት የ84 ሺ ቤቶች ግንባታ በመካሄድ ላይ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተጀመሩት ቤቶች ውስጥም ከ50ሺ የሚሆነውን በተያዘው የጀት አመት ለዕድለኞች በዕጣ እንደሚተላለፍ ተገልጿል።
በነገው ዕለት የሚተላለፉት እስቱዲዮ ቤቶች ዋጋ 56 ሺ ብር ሲሆን፣ 12 ሺ 600 ብር ቅድሚያ ክፍያም የሚጠበቅባቸው መሆኑን ጠቁመው፤ ባለ 1 መኝታ ቤቶች ዋጋ ደግሞ ወደ 153 ሺ ብር መድረሱንና ቅድመ ክፍያውም 29 ሺ ብር መሆኑ አመልክተዋል።
በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት ለተጠቃሚ የማስተላለፉ ስራ ነገ የሚወጣውን ጨምሮ ለሰባተኛ ጊዜ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል።
| < Prev | Next > |
|---|


