በኢራን ላይ የሚፈፀም የእሥራኤል ጥቃት አንድ ወር የሚወስድ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2004 (ዋኢማ) - እሥራኤል ኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ለማድረግ የሚያስችል ጥቃት ብትፈፅም በሁለቱም አገሮች መካከል አንድ ወር የሚወስድ ጦርነት ሊቀሰቅስ እንደሚችል መገመቱን የእሥራኤል ካቢኔ የሲቪል መከላከያ ዘርፍ ኃላፊ ማመልከታቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ከኢየሩሳሌም ያስተላለፈው ዜና አመለከተ። በጦርነቱ ሂደት ከኢራን ወደ እሥራኤል በሚተኮሱ ሚሳይሎች 500 እሥራኤላውያን ሊሞቱ እንደሚችሉም ተገምቷል።

በእሥራኤል ካቢኔ የሲቪል መከላከያ ዘርፍ ኃላፊው ማታን ቪልናይ «መአሪቭ» ከተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ ወኪል ጋር ባካሄዱትና ባለፈው ረቡዕ ታትሞ በወጣው ቃለ ምልልስ በኢራን ላይ በእሥራኤል የሚፈፀም ጥቃት በበርካታ ግንባሮች ከፍተኛ ጥፋትና ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ጦርነት እንዲከፈት ሊያደርግ እንደሚችል ማመልከታቸውን አሶሺዬትድ ፕሬስ ገልጿል።

በእሥራኤል ካቢኔ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትርና የሲቪል መከላከያ ዘርፍ ኃላፊው ማታን ቪልናይ ይህን ቃለ ምልልስ ከተጠቀሰው ጋዜጣ ጋር ያካሄዱት የኢራን የኑክሌር ጦር መሣሪያ ባለቤት መሆን በእሥራኤል ሕልውና ላይ የሚያስከትለውን ስጋት በሚመለከትበአገሪቱ ውስጥ በያቅጣጫው ክርክር በሚካሄድበት ወቅት እንደሆነ ታውቋል።

የእሥራኤል ጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም የነበሩት የቀድሞው ጀኔራል ማታን ቪልናይ ለአለፉት አምስት ዓመታት የአገሪቱን የሲቪል መከላከያና ሥርዓት ማለትም የአየር ጥቃት ማስጠንቀቂያን፣ የቦምብ አደጋ መከላከያንና የሕዝብ የአደጋ ዝግጁነት የሚመለከተውን ሥርዓት ሲከታተሉና ደረጃ ውንም ሲያሳድጉ መቆየታቸው ተገልጿል።

በቅርብ ጊዜ ውስጥ በቻይና የእሥራኤል አምባሳደር እንደሚሆኑ የሚጠበቁት ማታን ቪልናይ «መአሪቭ» ከተባለው ዕለታዊ ጋዜጣ ጋር ባካሄዱት በዚሁ ቃለ-ምልልስ የአገሪቱ የሲቪል መከላከያ በከፍተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ መሆኑ የሚያጠያይቅ ባይሆንም፣ ከኢራን ጋር የሚፈጠር ግጭት ሊያስከትል የሚችለውን ከፍተኛ ጉዳት ተገንዝቦ የበለጠ ዝግጁ ሆኖ መገኘት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ማታን ቪልናይ መንግሥት ከኢራን በኩል በሚፈፀም የአፃፋ ጥቃት ሂደት በየቀኑ ወደ እሥራኤል ከተሞች በሚወነጨፉት በመቶዎችና በሺዎች የሚቆጠሩ ሮኬቶችና ሚሳይሎች ቁጥራቸው 500 የሚደርሱ ሰዎች ሊገደሉ እንደሚችሉ በመገመት የራሱን ከፍተኛ ዝግጅት ማድረጉንም አረጋግጠዋል። በቀድሞ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም አገላለጽ በየግንባሩ ከኢራን ጋር የሚካሄደው ጦርነት 30 ቀናት ሊወስድ እንደሚችል ተገምቷል።

እሥራኤል፣ እንዲሁም አሜሪካና ታላላቆቹ ምዕራባውያን አገሮች የኢራን የኑክሌር ምርምር ፕሮግራም በተለይም ዩራኒየም የተባለውን ንጥረ ነገር የማበልጸግ (የጥራት ደረጃ የማሳደግ) ፕሮግራም የኑክሌር ቦምብ የማምረት ዓላማ እንዳለው እንደሚጠረጥሩ ሲያስታውቁ መቆየታቸው ይታወቃል። ኢራን ግን የኑክሌር ምርምር ፕሮግራሟ የአገሪቱን የኢነርጂ ፍላጐት የማሟላት ሰላማዊ ዓላማ እንዳለው በማመልከት በምርምሩ የመቀጠል አቋሟ ፅኑ መሆኑን አመልክታለች።

እሥራኤል የኑክሌር ጦር መሣሪያ (ቦምብ) ባለቤት የሆነችው ኢራን ለሕልውናዋ አስጊ እንደሆነች ትገልጻለች። ኢራን በመመሥረቻ ቻርተሮቻቸው ላይ እሥራኤልን የማጥፋት ዓላማ እንዳላቸው ያስታወቁ አክራሪ ቡድኖችን (የፍልስጥኤሙን ሐማስና የሊባኖሱን ሂዝቦላ) መደገፏም ይህንኑ እንደሚያሳይ አመልክታለች። የኢራኑ መንፈሳዊ መሪ አያቶላ ዓሊ ካማኒ ሰሞኑን በአገሪቱ የአርበኞች በዓል ላይ ባሰሙት ንግግርም እሥራኤል ከአካባቢው የምትጠፋበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆንና ፍልስጥኤምን ከእሥራኤል ወረራ ነፃ ማውጣት የአገራቸው ሃይማኖታዊ ግዴታ እንደሆነ ማመልከታቸውንም አሶሺየትድ ፕሬስ ገልጿል።

የአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ እንዳመለከተው እሥራኤል በኢራን ላይ ጥቃት የምትፈፀመው የኑክሌር ጦር መሣሪያ ለማምረት የሚያስችላትን ፕሮግራም እንድታቆም ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ የሚያደርገው ጥረት ውጤት ለማስገኘት ካልቻለ ብቻ እንደሆነ መሪዎቿ ገልጸዋል።

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ሊዮን ፓኔታ ሰሞኑን ዋሺንግተን ውስጥ በሰጡት መግለጫ ደግሞ በአገራቸው ግምት እሥራኤል በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈፀም ከውሳኔ ላይ እንዳልደረሰች ሲያመለክቱ የጦር ኃይሎች ጥምር ኤታማዦር ሹሞች ሊቀመንበር ጀኔራል ማርቲን ዲምፕሲ ደግሞ እሥራኤል በኢራን ላይ የምትወስደው ወታደራዊ እርምጃ የኢራንን የኑክሌር ምርምር አቅም ወደኋላ ለመጐተት እንጂ ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት እንደማይችል እንደሚገመት ማመልከታቸው ተገልጿል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 208 guests