የ1433ኛው የኢድ አልፈጥር በዓል ዛሬ ማታ ጨረቃ ከታየች ቅዳሜ፤ ካልታየች እሁድ ይከበራል

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 12/2004 (ዋኢማ) - ሙስሊሙ ኅብረተሰብ የኢድ አል ፈጢር በዓልን ሲያከብር በተፈጥሮ አደጋና በኤች አይ ቪ/ኤድስ ምክንያት የተጎዱ ወገኖቹ በገንዘብና በጉልበት መርዳት እንደሚገባ የኢትዮጵያ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ገለፀ።


የ1433ኛው የኢድ አል ፈጥር በዓል ዛሬ ማታ ጨረቃ ከታየት ቅዳሜ ካልታየች እሁድ እንደሚከበር ተገለፀ።


የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሼህ አሕመዲን ሼህ አብዱላሂ በዓሉን አስመልክቶ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት የረመዳን ኢድ ሲከበር የተቸገሩ ወገኖች ሊያስባቸውና አቅም በፈቀደ መጠን በመርዳት እስላማዊ ግዴታውን መወጣት ይጠበቅበታል።


ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በረመዳን ወር ያዳበራቸውን መልካም ሥራዎች ሁሉ፤ ከረመዳን ውጪም በመፈፀም ችግረኞችን ለመርዳት ያደርግ የነበረውን የመረዳዳት ሥራ ወደፊትም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል።


በሌላ በኩል ጥቂት ግለሰቦች ምን ዓይነት ችግር በሌለበት አገር በስመ ኃይማኖት ሁከትና ረብሻ ለመቀስቀስ ከአገር ቤት እስከ ውጭ በዘረጓቸው የሽብር መረቦቻቸው ኅብረተሰቡን ለማደናገር ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉ እንደሚስተዋል ተናግረዋል።


ስለዚህ ማህበረሰቡ የእነዚህን ኃይሎች እንቅስቃሴ በምንም መልኩ ከኃይማኖት ጋር ግንኙነት እንደሌለው በመገንዘብ በረመዳን ወር ሲያሳይ የቆየውን እስላማዊ ሥነ ምግባርና ወንድማማችነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።


ከዚህ ጋር ተያይዞ የኢድ ሰላት በሚከናወንበት ዕለት በዓሉን ወደ ሁከትና ረብሻ ለመቀየር የሚሞክሩ እንዳንድ ግለሰቦች ካጋጠሙት ሙስሊሙ ኅብረተሰብ ምክር ሊለግሳቸው እንደሚገባ ገልጸው፣ በምክር የማይመሰሉ ከሆነ ግን ለሕግ አካል አሳልፎ መስጠት እንዳለበት አስገንዝበዋል።


ከምንም በላይ የኢድ ሰላት የሚካሄድበት ቦታ የረብሻና የግርግር ቦታ ሳይሆን የኢባዳ ቦታ መሆኑን ሼክ አህመዲን አሳስበዋል።


ከዚህ ባሻገር ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በግልም ሆነ በጋራ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በገንዘቡ፣በዕውቀቱና በጉልበቱ እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።


በአጠቃላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በኃይማኖት፣ በዘር፣ በጎሳና በቀለም ሳይለያይ በሰላምና በፍቅር እጅ ለእጅ ተያይዞ የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን ለማካሳካት ሁሉም ድርሻውን እንዲወጣ ፕሬዚዳንቱ አስገንዝበዋል።


በዓሉ በተለይ የኢድ ሰላት ሥነ ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማ ሙስሊም ኅብረተሰብ፣ ከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት፣ አምባሳደሮች ዲፕሎማቶችና የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተወከዮች በሚገኙበት በአዲስ አበባ ስታዲዬም በደመቀ ሁኔታ እንደሚከበር አስታውቀዋል።


በዓሉ የሰላም፣ የደስታና የብልፅግና እንዲሆን ሼክ አህመዲ መልካም ምኞታቸውን መግለጻቸውንም የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 237 guests