ከተማውን የጤና ሽፋንን መቶ በመቶ ለማድረስ እየተሰራ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ ነሐሴ 5/2004/ዋኢማ/ - የአዲስ አበባ ከተማ የጤና አገልግሎት ሽፋንን መቶ በመቶ ለማድረስ የጤና ጣቢያዎች ግንባታ እያካሄደ መሆኑን የአዲስ አበባ የጤና ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው የህክምናና ተሃድሶ ወሳኝ የሥራ ሂደት ባለቤትና ምክትል የቢሮ ኃላፊ ዶክተር መንግሥቱ በቀለ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለፁት፤ በከተማው ያለውን የጤና ሽፋን መቶ በመቶ ለማድረስ 75 የጤና ጣቢያዎች በመገንባት የጤና ሽፋኑን ለማሳደግ ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

በመገንባት ላይ ካሉት ጤና ጣቢያዎች መካከል 33ቱ ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፤ ከነዚህ መካከልም ሃያ ሶስቱ ተገቢው የህክምና ቁሳቁስ ተሟልቶላቸው አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ፣ አስሩ ግንባታቸው በቅርቡ እንደሚጠናቀቅና አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።

እንዲሁም 42 የሚሆኑ የጤና ጣቢያዎች ግንባታቸው በመፋጠን ላይ እንደሚገኝና በተያዘው በጀት አመት ህዳር ወር ላይ ይጠናቀቃሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ኃላፊው ዶክተር መንግስቱ ተናግረዋል፡፡

ከአዳዲስ የህክምና ጣቢያዎች በተጨማሪ በአምስት ነባር የከተማዋ ሆስፒታሎችን ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የማስፋፊያ ግንባታዎች እየተካሄደላቸው መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር መንግስቱ፤ በህክምና መሣሪያዎች ረገድ ያለባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ በዘንድሮ የበጀት አመት ለእያንዳንዱ ሆስፒታል 10 ሚሊዮን ብር ተመድቧል ብለዋል።

ባለፈው የበጀት አመት ለ200መቶሺ አቅም ለሌላቸው ወገኖች የነጻ ህክምና አገልገሎት ተጠቃሚዎች እንዲሆኑ በማድረግ የ8 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በአዲስ አበባ ጤና ቢሮ የሚሰጠውን አገልግሎት ይበልጥ ለማስፋፋትና ለማሻሻል የተለያዩ የለውጥ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ጤና ቢሮው የሚሰጠውን አገልግሎት ለማስፋትና ባለሙያዎችን ይበልጥ ለማበረታታት የማትጊያ ዘዴዎችን ዘርግቶ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶክተር መንግሥቱ ባለሙያዎቹ በመንግሥት ሆስፒታል በትርፍ ሰአታቸው እንዲሰሩ በማድረግ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት ሆስፒታሎች የሚታየውን የመድሀኒት አቅርቦትና የተቋማቱ የንጽህና መጓደል ጋር በተገልጋዩ የሚነሱ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች እንደሚቀርቡ የተናገሩት ዶክተር መንግሥቱ ወደፊቱ የተገልጋዩን ፍላጎት ያማከለ የመደኃኒት አቅርቦትና የህክምና አገልግሎትን ለመስጠት ጥረት ይደረጋል ብለዋል፡፡