ኢትዮጵያን ከግማሽ ሚሊየን በላይ ጎብኝዎች ጎበኟት

  • PDF

አዲስ አበባ ነሐሴ 5/2004/ዋኢማ/ - በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የውጭ አገራት ቱሪስቶች ኢትዮጵያን መጎብኘታቸውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለፀ።

በሚኒስቴሩ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አወቀ ጤናው እንደገለጹት፤ በበጀት ዓመቱ 584 ሺ 498 የውጭ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን ጎብኝተው 773 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

የጎብኚዎቹ ቁጥር ከ2003 ዓ.ም ጋር ሲነፃፃር 14 በመቶ ብልጫ ያለው ሲሆን፤ ሚኒስቴሩ የቱሪስት ፍሰትን ለመጨመር ሰፊ የማስተዋወቅ ሥራ ማከናወኑ ለተገኘው ውጤት ጉልህ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

በተለይ በተመረጡ አገራት በተካሄዱ ዓለም አቀፍ የቱሪዝምና የንግድ ትርኢቶች ላይ ዘጠኝ ጊዜ በመሳተፍ ባህላዊና ታሪካዊ እንዲሁም ተፈጥሯዊ ኃብቶችን በማስተዋወቅ የገፅታ ግንባታ ሥራ መሰራቱ ለፍሰቱ መጨመር ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

በጀርመን አገር በተካሄደው የንግድ ትርኢት ላይ ክልሎችና ተጠሪ ተቋማት የራሳቸውን ምርትና መስህቦችን እንዲተዋወቅ ማድረጋቸውም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም በስፓኒሽ፣ በጣሊያንኛ፣ በጀርመንኛና በሩስኪ ቋንቋዎች በራሪ ወረቀቶችን በማዘጋጀት ጎብኚዎች የተሻለ ግንዛቤ እንዲያገኙ መደረጉ ጠቃሚ ድርሻ እንደነበረው ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡

የዘርፉን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ዓይነት፣ መጠንና ደረጃ ለማሳደግ ለ442 ሆቴሎች፣ ለ11 ሬስቶራንቶችና ለሦስት ባህላዊ ምግብ ቤቶች እንዲሁም ለ26 አስጎብኚ ድርጅቶች የብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ መሰጠቱንም ገልጸዋል፡፡

የቱሪዝም መዳረሻዎችን ለማልማት በተደረገው እንቅስቃሴ በብሔራዊ ፓርኮችና ለቱሪስት አገልግሎት በሚውል ጥብቅ ቦታዎች ላይ 1 ሺህ 468 ኪሎ ሜትር የመንገድ ጥገና ተከናውኗል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡


  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 290 guests