ሀገራቱ ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ
አዲስ አበባ ነሐሴ 5/2004/ዋኢማ/- በኢትዮጵያና በኔዘርላንድ መንግስታት መካከል የሚደረገውን የንግድ፣ የኢንቨስትመንትና የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴ ለማሳደግ ሁለቱ አገራት ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።
በገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስቴር በተካሄደው የፊርማ ሥነ ሥርዓት ላይ በኢትዮጵያ በኩል የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ አለማየሁ ጉጆ በኔዘርላንድ በኩል ደግሞ በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሀንስ ብላንኬን ቤርግ ስምምነቱን ፈርመዋል።
በሁለቱ አገራት መካከል የተደረገው ስምምነት የአንዱ አገር ሰው ወይም ድርጅት በሚያገኘው አንድ ዓይነት ገቢ ላይ በሁለቱም አገሮች ተመሳሳይ ግብር እንዲከፍል መደረጉ ለካፒታል ፍሰት፣ ለዕቃዎችና ለአገልግሎቶች ልውውጥ የሚፈጥረውን እንቅፋት ለማስወገድ ያስችላል።
በተለይ ሁለቱ አገራት ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት ስምምነት ላይ መድረሳቸው የኢንቨስትመንት ፍሰትን ለመጨመር አመቺ ሁኔታን ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል።
ስምምነቱ ተፈፃሚ የሚሆነው በገቢ ላይ በተጣሉ የግብር ዓይነቶች ላይ ብቻ ሲሆን ቀጥተኛ ያልሆኑ ታክሶችን የማያካትት እንደሆነም በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።
እንዲሁም ስምምነቱ ተጠቃሚ የሚያደርገው የሁለቱን አገሮች ዜጎች ብቻ ሳይሆን በአገሮቹ ነዋሪ የሆኑ ሰዎችንም ጭምር ተጠቃሚ የሚያደርግ ሲሆን በየትኛውም የመንግስት የአስተዳደር እርከን የተጣሉና በሚጣሉ የግብር ዓይነቶች ላይ ተፈፃሚነት ይኖረዋል።
የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ አለማየሁ ጉጆ በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ላይ እንደገለጹት ስምምነቱ ሁለቱ አገራት ያላቸውን ታሪካዊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋግረዋል።
ስምምነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል የቴክኖሎጂ፣ የእውቀትና የክህሎት ሽግግር ለማድረግ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ የኢኮኖሚ ትብብርን የሚያጠናክር መሆኑን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የኔዘርላንድ አምባሳደር ሀንስ ብላንኬን ቤርግ በበኩላቸው ሁለቱ አገሮች ተደራራቢ ግብርን ለማስቀረት የሚያስችል ስምምነት ላይ መድረሳቸው በአገራቱ በመካከል ያለውን የንግድና የኢንቨስትመንት ግንኙነት የሚያጠናክር ነው ብለዋል።
ከሁለቱ አገራት የተውጣጡ ባለሙያዎች ለአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ በሁለቱ አገራት ያለውን የግብር ሥርዓትና ፖሊሲ ጥናትና ውይይት ማድረጋቸውን ያስታወሱት አምባሳደሩ በኢትዮጵያ የግብር ከፋዮችን ቁጥር ለማሳደግና አገሪቱ ግብር የመሰብሰብ አቅሟን የሚያሳድግ መሆኑን ገልጸዋል።
በሁለቱ አገሮች የግብር ሕጎች መካከል በማስከፈያ ምጣኔ፣ ተቀባይነት ባላቸው የወጪ ዓይነቶች፣ በግብር አጣጣል ዘዴ ላይ ባሉ ልዩነቶች የሚፈጠረውን አለመጣጣም ለማስቀረት በእያንዳንዱ የግብር ዓይነት ላይ ሁለቱ አገሮች ሊከተሉት የሚገባ የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል።
ኔዘርላንድ በተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የምትገኝ አገር በመሆኗ በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎቿ በኢትዮጵያ ውስጥ በኢንቨስትመንት ተሰማርተው የሚገኙ በመሆኑ ኢትዮጵያ ከኔዘርላንድ ኩባንያዎች ከፍተኛ ገቢ ለመሰብሰብ የሚያስችል ዕድል አላት።
በኢትዮጵያና በኔዘርላንድ መንግስታት መካከል የተደረገው ተደራራቢ ግብር ለማስቀረት የሚያስችለው ስምምነት በሥራ ላይ የሚውለው በሁለቱ አገሮች ፓርላማዎች ሲጸድቅ መሆኑን የዘገበው ኢዜአ ነው።
| < Prev | Next > |
|---|


