ከ12 ሚሊየን ሄክታር በላይ መሬት በደን ተሸፈነ
አዲስ አበባ ነሐሴ 03/2004/ዋኢማ/ - ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የመሬት የቆዳ ሽፋን ውስጥ 12 ሚሊዮን 296ሺ ሄክታር መሬት በደንና 41 በመቶ የሚሆነው ደግሞ በእጽዋት መሸፈኑን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት ጥበቃና አጠቃቀም ዳይሬክቶሬት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል እንደገለጹት፤ የሀገሪቱን የደን ሽፋን ለማሳደግ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ጥረቶች 12 ሚሊዮን 296ሺ ሄክታር መሬት በደን መሸፈን ተችሏል።
እንዲሁም 11 በመቶ የሚሆነው የሃገሪቱ የቆዳ ስፋት በደን ከመሸፈኑም በላይ 41 በመቶ በእጽዋት መሸፈን እንደቻለ ተናግረዋል።
ባለፈው የበጀት አመት 5 ነጥብ 8 ቢሊዮን ያህል ችግኞችን ለማዘጋጀት ታቅዶ 3 ነጥብ 5 ቢሊየን ችግኞች እንደተዘጋጁ የገለጹት፤ አቶ ተፈራ ከዚህ ውስጥ 950 ሚሊዮን ያህል ችግኞችን በበጋው ወቅት በተደረገ የህብረተሰብ ተሳትፎ መተከላቸውንና ቀሪዎቹም አሁን በክረምት ወቅት በመተከል ላይ ነው ብለዋል።
በተለያዩ ወቅቶች የተተከሉ ችግኞችን የደረሱበትን ደረጃ ለመከታታል ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን፣ ከብዝሃ ህይወት ኢንስቲትዩቱ፣ ከክልሎችና ከመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ግብር ሃይሎች እንደተቋቋመ ተፈራ ተናግረዋል።
ከተፋሰስ ልማቱ ጋር በተያያዘ ከ13 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነጻ ሆኖ እንዲለማ መደረጉን የገለጹት አቶ ተፈራ በ3 ነጥብ 7 ሚሊየን ሄክታር መሬት ላይ ደግሞ የስነ-ህይወታዊ ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
የደን ሃብትን መጠበቅ የተለያዩ ፈርጀ ብዙ ጥቅሞችን ከማስገኘቱም በላይ የውጪ ምንዛሪ አንደሚያስገኝ የጠቀሱት አቶ ተፈራ ሃገሪቷ ባለፉት አስርት አመታት ውስጥ የባህር ዛፍናቀርከሃን ጨምሮ የተለያዩ የዛፍ ውጤቶችን ወደ ውጪ በመላክ ከ71 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ መገኘቱን ተናግረዋል።
ክፍተት ለመሙላት ሁለት የግል የደን ዘር አቅራቢ ድርጅቶች ሥራ ከመጀመራቸውም በላይ ከጃፓኑ የጃይካ ድርጅት ጋር በመተባበር በአማራ፤ በትግራይ፤ በደቡብና በኦሮሚያ ብሔራዊ ክልሎች የደን ዘር ማባዣ ማዕካላትን በ80 ሚሊዮን ብር በመገንባት ላይ እንደሚገኙ አያይዘው ገልጸዋል፡፡
በ1999 አመተ ምህረት የደን ልማት ፖሊሲ ጸድቆ እንደወጣ የገለጹት አቶ ተፈራ፤ የደን ልማቱን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችለው ደንብ ግን ጸድቆ ባለመውጣቱ ምክንያት ለዘርፉ እድገት ትልቅ ማነቆ ሆኖ እንደቆየና ሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ደንቡን ለማፅደቅ በ2004 አመተ ምህረት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ማቅረቡን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በሃገሪቱ ተክክለኛ የሆነን የደን ቆጠራ ለማካሄድ የአቅም ውስንነት እንደነበር የገለጹት አቶ ተፈራ አሁን ግን ከአለም የምግብና የእርሻ ድርጅት በተገኘ የ480ሺ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ቆጠራውን በ2005 አመተ ምህረት ለማከናወን ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
ህብረተሰቡን የሚያሳትፍ የደን ልማት ፕሮግራም በኦሮሚያ፣ ቤኒሻንጉል፣ አማራና በደቡብ ክልሎች ተግባራዊ ለማድረግ ከአውሮፓ ህብረት 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ዩሮ እንደተገኘ ጠቁመው፤ የበካይ ጋዝ ልቀትን ለመቀነስ የሚያስችል የደል ልማት ፕሮግራም ለማካሄድም ከዓለም ባንክ የ3 ነጥብ 5 ሚሊየን ዶላር ድጋፍ መገኘቱን ገልፀዋል።
የደን ሃብት ጥበቃ የተለያዩ አካላትን ርብርቦሽ የሚጠይቅ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተፈራ ሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ትኩረት ሰጥተው የደን ልማቱን ማካሄድ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


