ዶክተር መሐመድ ስርሀዬ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ
ጂጂጋ ነሀሴ 2/2004/ዋኢማ/ - የቀድሞው የኢፌድሪ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ የነበሩት ዶክተር መሐመድ ሰርሀዬ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም ትናነት በጂጂጋ ከተማ ቤተሰቦቻቸ፣ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናትና ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል።
ዶክተር መሐመድ ሰርሀዬ በቀብር ስነ-ስርዓታቸው ላይ የተነበበው የህይወት ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፤ በ1944 ዓ.ም በሶማሌ ክልል በቀብሪደሃር ከተማ ከእናታቸው ወይዘሮ አሻ ሃጂ መሀመድና ከአባታቸው አቶ ሰርሃዬ ሂድግ ተወለዱ።
ዶክተር መሐመድ ሰርሀዬ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በቀብሪደሃር ከተማ በልዑል ራስ መኮንን ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በሃረር ከተማ መድሃኒዓለም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ሲሆን፤ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቀድሞዋ ሶቭየት ህብረት፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውንና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በእንግሊዝ አገር በኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ድግሪያቸውንና የዶክትሬት ድግሪያቸውን አግኝተዋል።
ዶክተር መሐመድ ሰርሀዬ በ1983 ዓ.ም የደርግ ስርዓትን መውደቅ ተከትለው ወደ አገራቸው በመግባት በተለያዩ የስራ መስኮች የቆዩ ሲሆን፤ ከ1987 እስከ 2002 ዓ.ም ድረስ የኢፌድሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ-ጉባኤ በመሆን ያገለገሉ ሲሆን፤ በተጠቀሱት ዓመታት የተወከሉበትን የህዝብና የመንግስት ኃላፊነት በቅንነት አገልግለዋል።
እንዲሁም በ2002 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ በሶማሌ ክልል የቀብሪደሃር ወረዳን ህዝብ በመወከል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ተመርጠው ህይወታቸው እስከ ተለየበት ጊዜ የህዝብ ተወካዮች ምክር አባል ሆነው አገልግለዋል።
የኢፌድሪ የፌደሬሽን ምክር ቤትና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ እንዲሁም የሶማሌ ክልላዊ መንግስት በዶክተሩ ሞት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን በቀብር ስነ-ስርዓቱ ላይ የገለጹ ሲሆን፤ ዶክተር መሀመድ ሰርሀዬ ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ የተወጡና በስራቸውና በስነ-ምግባራቸው ምስጉን እንደነበሩ ገልጸዋል።
በቀብር ስነ ስርዓቱ ላይ የኢፌድሪ የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃንን ጨምሮ የክልሉ ፕሬዚዳንትና ሌሎች ከፍተኛ ባለስልጣናት ተገኝተዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


