ኋላፊነት የጎደለው አሳፋሪ አስተያየት አተያይ!

  • PDF

ከሲኢድ መሐመድ (ሐምሌ 2004)

ባለፉት ሦስት ሣምንታት የሚዲያዎች ዐበይት የትኩረት አቅጣጫ ከነበሩት መካከል ከፍተኛ - የመወያያ አጀንዳ ሆኖ የሰነበተውና አሁንም ሕብረተሰቡ እየተነጋገረበት ያለው ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የጤና ሁኔታ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በጤና መታወክ ምክንያት የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው እንደነበርና በሃኪሞቻቸው ትእዛዝ እረፍት እንዲወስዱ መደረጉን የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታውቋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በህዝብ የሚነሱና አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች የሚያነሷቸው ነጥቦች ተበራክተዋል፡፡ አገሪቱን እንመራለን የሚሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮች ያወጧቸው ዘገባዎች ህዝቡን ያስቆጡና ማነነታቸውንና የፖለቲካ ንቃተ ህሊናቸው ዴጃን ያሳዩ ነበሩ፡፡ በአራጋቢ ሚዲያዎቻቸው በኩል ከቀረቡት አስተያየቶች አንዱ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ አስተያየት ይገኝበታል፡፡ አስተያየቱን የሰማ ሰው ሁሉ “የማይሰማ ጉድ የለም!” ነበር ያለው፡፡

በዚህ ጽሁፍ የዶክተር ነጋሶ ጊዳዳን ወስደን ለአብነት ያህል እንይ እንጂ በጉዩ ዙሪያ የተሰጡ በለአብነት ያህል እንውሰድ፡፡ ግለሰቡ በኢህአዴግ መዋቅር ገብተው አጭር ለማይባል ጊዜ ሰርተዋል፡፡ በርካታ ነገሮችን ሲፈተፍቱ ነበር፡፡ የፖሊሲ ማስተካከል ያስፈልግ ከነበረም ፖሊሲውን ካጸደቁ ሰዎች አንዱ ስለነበሩ ያኔ አንስተው አቋማቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ ይፋ አድርገው ቢሆን ኑሮ ባማረባቸው ነበር፡፡ ፖሊሲውን ሲተገብሩና እንዲተገበር ሲያደርጉ ለአንድ የምርጫ ጊዜ ከዘለቁ በኋላ የቆይታ ጊዚያቸው ሲያበቃ ይከተሉት ከነበረው የፖለቲካ ህይወት ጋር ጨርሶ ተቃራኒ ወደ ሆነ ህይወት ገቡ፡፡

እንደዚህ ዓይነቱ የግል ጥቅምንና ስልጣንን ማሳደድ ቀደም ሲል ተጸናውቷቸው እንደነበር በአንደበታቸው መስክረዋል፡፡ መጀመሪያ የኦነግ አባል ሆነው ሲንቀሳቀሱ ነበር፡፡ ከዚያም ተሳስቻለሁ ብለው የኢህአዴግ አባል ሆነው መስራት ጀመሩ፡፡ ኢህአዴግን የመረጠው ህዝብ ድርጅቱን ወክለው ሲቀርቡ ተመረጡ፡፡ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት መሆን ቻሉ፡፡ ከዚያም መልሰው የመድረክ አባል ሆኑ፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ እየታዘባቸው ቢሆንም እሳቸው ግን ምንም አልመሰላቸውም፡፡ አሁንም ጥሩ የፖለቲካ ስብእና ያላቸው ይመስል በየመድረኩ ውሃ የማይቋጥር ንግግር በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከአንድ ወደ ሌላ የፖለቲካ ድርጅት መገለባበጣቸው አንድ ቋሚ እምነት የሌላቸው መሆኑን ከማሳየት አልፎ ሌላ የሚፈይደው ነገር የለም፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ህመም ጋር ተያይዞ ያቀረቡት አስተያየትም ከዚሁ ባህሪያቸው የመነጨ ነው፡፡ “አቶ መለስ ተሽሏቸው ሲመለሱ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ አለባቸው” ነበር ያሉት፡፡
ከዚህ የምንገነዘበው ነገር ቢኖር ግለሰቡ ፖሊሲ የሚቀየረው በምን ምክንያት እንደሆነ፤ የአገሪቱ የበላይ ሕግ ምን እንደሚል፤ የኢትዮጵያ መንግስት አወቃቀር ምን እንደሚመስል ለመገንዘብ አለመቻላቸው ነው፡፡ ለመሆኑ የማይታመም የሰው ልጅ አለ? ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሰው የመሆናቸውን ያህል ይችን አገር ወደሌላ ምእራፍ ለማሸጋገር ከተሸከሙት የስራ ጫና አንጻር ቢታመሙ ምን ይገርማል፡፡ ይህስ ከፖሊሲ ጋር ምን ያገናኘዋል?

የአቶ መለስ ዜናዊን የስራ ጫና በሚገባ የሚያውቁት ህመሙ ተሽሏቸው ሲመለሱ የፖሊሲ ማስተካከያ ማድረግ ይኖርባቸዋል የሚል ሃሳብ ማቅረባቸው በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ማንነታቸውን ያጋለጠ አጋጣሚ ሆኗል፡፡

አገር እንመራለን፣ ከኢህአዴግ የተሻለ ዴሞክራሲ እናሰፍናለን በማለት ሲያደነቁሩን ከነበሩት የተቃዋሚ አመራሮች መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ነጋሶ አገርን የመምራት እድል ቢያጋጥማቸው ምን እንደሚያደርጉ ለመገመት አያዳግትም፡፡

ከኦነግ ወደ ኢህአዴግ ከኢህአዴግ ወደ መድረክ እየተገለባበጡ እንደኖሩት ሁሉ በታመሙና ሌላ ተፈጥሯዊ ችግር ባጋጠማቸው ቁጥር ፖሊሲውን እንዳሻቸው ለመቀያየር የሚያስችላቸውን የፈላጭ ቆራጭ ስርዓትን ማስፈን እንደሚፈልጉ ያመላክታል፡፡

በእውነቱ ከሆነ የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መታመም አገሪቱን ከነበረችበት የድህነት አዘቅት ለማውጣትና በልማት፣ ሰላምና ዴሞክራሲ ጎዳና ለማሰለፍ ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነው ያደረጉት ተጋድሎ ከፍተኛ ጫና ማሳደሩ ይቀራል ብሎ መገመት ከእውነታ መራቅ ይሆናል፡፡ ጫናው ጤንነታቸው ላይ የሚያደርሰው ተጽእኖ መኖሩ የሚያስገርም አይሆንም፡፡

የከሰሩ ፖለቲከኞች እስካሁን ድረስ በከፍተኛ ደረጃ ለፖለቲካ ተግባራቸው ይጠቀሙበት የነበረውና አሁንም በቀጣይነት እየተጠቀሙበት ያለው ሃይማኖትን ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ማንኛውም የሰው ልጅ የሚያጋጥመውን ተፈጥራዊ የሆነውን ህመምን ለፖለቲካ ፍጆታ ለማዋል ሲቋምጡ መስተዋላቸው በኢተዮጵያ ህዝብ ዘንድ የሚያስንቃቸው እንጂ ይበል የሚያስብላቸውና የሚያስከብራቸው አለመሆኑን በተገነዘቡ ነበር፤ ህሊና ቢኖራቸው፡፡

መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ግን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የጤንነት ሁኔታ አሳስዝኖታል፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ድረስ ህይወታቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳልፈው ከሰጡ ኢትዮጵያውያን አንዱ መሆናቸውን ስለሚያውቅ፡፡ እንኳንስ መላ ህይወቱን ለህዝብ ደህንነትና ብልጽግና አሳልፎ ለሰጠ ዜጋ ይቅርና ለሌላ ሰውም ቢሆን በባህላችን መሠረት ለታመመ ሰው ማዘንና በጎውን መመኘት የተለመደ ነው፡፡

ለዚህም ነው መላው የኢትዮጵያ ህዝብ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤንነት ሁኔታ ያሳሰበውና ለማወቅም የጓጓው፡፡ ይሁን እንጂ ተቃዋሚዎች ህመምን ለፖለቲካ ፍጆታ መጠቀሙን ቀጥለውበታል፡፡ በኢህአዴግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድ የስልጣን ሽኩቻ ተፈጥሯል፤ አገሪቱ ወደ ግጭት ሊታመራ ነው፤ አሁን ተቃዋሚዎች አንድ ሆነን ሁከትንና ብጥብጥን ማንገስ አለብን የሚሉ አጀንዳዎች አንግበው እየተንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡

በኢህአዴግ ባለስልጣናት ዘንድ ለስልጣን ሽኩቻ መሰረት እንደሌለው ግን ጠፍቷቸው አይመስለኝም - ሁኔታው ህዝቡን ለማወናበድ ሊጠቀሙበት በመከጀላቸው እንጂ፡፡ የኢህአዴግ ከፍተኛው የስልጣን አካል ጉባኤው ነው፡፡ ጉባኤው በየሁለት ዓመት አንድ ጊዜ የሚደረግ ሲሆን አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም በማንኛውም ጊዜ ሊጠራና ውሳኔዎችን ሊያስተላልፍ ይችላል፡፡ ከዚህ በመቀጠል የዕለት ተለት ስራዎችን በበላይ የሚመራው የኢህአዴግ ምክር ቤት ነው፡፡ ምክር ቤቱ ከአራቱ የኢህአዴግ የፖለቲካ ድርጅት የተውጣጡ 180 አባላትን የያዘ ነው፡፡ ከእያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት 45 አባላት ተወክለውበታል፡፡ ምክር ቤቱ ከጉባኤው ቀጥሎ ትልቅ ስልጣን ያለው አካል መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሶስተኛ ደረጃ ስራዎችን ለማከናወን ከምክር ቤቱ ውክልና ያገኘው ከአራቱም የፖለቲካ ድርጅቶች የተውጣጡ 36 አባላትን የያዘው የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታ በእነዚህ አካላት የታየ ምንም ዓይነት ክፍተት የለም፡፡ ከዚህ አንጻር በገዢው ፓርቲ ደረጃ የተፈጠረ ምንም ዓይነት ክፍተት የለም፡፡

በመንግስት ደረጃም ሲታይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ያለው መንግስት በህዝብ የተመረጠ ነው፡፡ በዚህ ረገድ ከፍተኛው የስልጣን አካል ህዝብ ሲሆን በመቀጠልም ህዝብ የወከለው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አለ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማይኖሩበት ወቅት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወክሎ የሚሰራበት አግባብ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በፌዴራል ደረጃ የስልጣን ሽኩቻ ምንም ዓይነት ቦታ የለውም፡፡ በክልሎች ያለውን ሁኔታ በሚናይበት ጊዜ ደግሞ የክልል መንግስታት ራሳቸውን ችለው የሚሰሩበት ሁኔታ አለ፡፡ በዚህም ደረጃ ክፍተት የለም፡፡
በገዢው ፓርቲ የስልጣን ሽኩቻ አለ እየተባለ የሚራገበው ከእውነታ የራቀ ነው፡፡ የስልጣን ሽኩቻ የሚኖረው በምን ዓይነት ሁኔታ ነው፡፡ ወሳኝ አካል አንድ አምባገነናዊ መሪ ወይም ባለስልጣን ሲሆን ነው፡፡ በስልጣን መሞትንና ህይወትህን ለህዝብ አሳልፎ መስጠት ባለበት ስርዓት ሳይሆን በስልጣን ተጠቃሚነት በነገሰበት የአሰራር ስርዓት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ስራዎች እንደ አካል በቡድን የሚሰሩበት አግባብ በመኖሩ የስልጣን ሽኩቻ ቦታ ሊኖረው አይችልም፡፡

የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶች በጠቅላይ ሚኒስትሩ የጤና ሁኔታ ዙሪያ መልካም ነገር ከመመኘት ይልቅ ሌላ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ማሰራጨታቸው ግን መላውን የኢትዮጵያ ህዝብ አሳዝኗል፡፡ በተለያየ አጋጣሚ ካነጋገርኳቸው ነዋሪዎች ለመረዳት እንደቻልኩት ጥቂት ግለሰቦች የፖለቲካ ልዩነታቸውን ለህዝብ በተለያየ ጊዜ እያቀረቡ የነበሩ ሲሆን አሁን ግን ከጤና ጋር አያይዘው ተደማጭነትን ለማግኘት ያደረጉት ጥረት ከንቱ መሆኑን ነው፡፡ አገርን እንመራለን የሚሉ የተቃዋሚ ድርጅቶች መሪዎች እንደዚህ ዓይነት አስተያየት መሰንዘራቸው ያላቸው የፖለቲካ አቅም ግምት ውስጥ ያስገባ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከፍተኛ የሆነ የሥራ ጫና እንደነበራቸው ለማንም ግልጽ ነው፡፡ ከልጅነት እስከ እውቀት ህይወታቸውን ለኢትዮጵያ ህዝብ አሳልፈው ሰጥተዋል፡፡ የኖሩትም የሚኖሩትም ለኢትዮጵያ ህዝብ ሆኗል፡፡ ለኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ አገራት በማገዝ ረገድም ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር ከአንዳንድ ጨለምተኞች በስተቀር የኢትዮጵያ ህዝብ በህመማቸው የተሰማው ሃዘን ከፍተኛ ነው።

ህመሙ ቀሎላቸው ወደ ሥራቸው መመለስ ይችሉ ዘንድም ፈጣሪውን ሲማጠን ይደመጣል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የነበራቸው የሥራ ጫና፣ የሰሩቸው ተግባራትና ያስመዘገቡት ስኬት መዳሰሱ ጤናቸው ላይ የደረሰውን እንከን ለመገንዘብ ያግዛል፡፡

አቶ መለስ ወደ ትጥቅ ትግል የገቡበት በወጣትነት ዘመናቸው ነበር፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ሁለመናቸውን ለህዝብ አሳልፈው የሰጡት፡፡ ያከናወኑት የነበረውን አጠቃላይ ስራና ይዘውት የተጓዙት ትእግስት የተሞላው የአመራር ብስለት እንደዚሁም ያስመዘገቡት ስኬትን በዚህ አጭር ጽሁፍ መቃኘት ባይቻልም በጨረፍታ ብቻ ግን ማየት ይቻል ይሆናል፡፡ በመሆኑም በዚህ ጽሁፍ የአቶ መለስን ሙሉ ገጽታ ማየት አይቻልም። እንደዚያ ዓይነቱን ጽሁፍ ለማቅረብ አንድ ትልቅ መጽሐፍም አይበቃም። ታሪካቸው ብዙ፣ ጥረታቸው የት የለሌ፣ እውቀታቸው ተዝቆ የማያልቅ፣ ያስገኙት ውጤትም በዚያን ልክ በመሆኑ በጨረፍታ ብቻ እናያለን።
አንዳንዶች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሲገልጹ “መለስ ብዙ ሰው ነው” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡ በበሰለ አመራር አገራቸውን መምራታቸውና የአፍሪካን ድምጽ ለዓለም ሕብረተሰብ ማሰማት መቻላቸው እንዳለ ሆኖ ንቁ የፖለቲካ አካዳሚ ተመራማሪ፣ አዲስ ንድፈ ሃሳብ አፍላቂ እና የጠለቀ ዓለም አቀፋዊ መረዳት እንዳላቸው በመግለጽም አባባላቸውን ለማስረጽ ይሞክራሉ፡፡

በሚያዚያ ወር 1947 ዓ.ም በትግራይ አድዋ ከተማ ነው የተወለዱት፤ ለገሰ ዜናዊ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁት በንግስተ ሳባ ሲሆን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በዊንጌት አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትለዋል፡፡ በ1964 ዓ.ም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የህክምና ፋክሊቲ በመግባት የሁለት ዓመታት የህክምና ትምህርታቸው መከታተላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ለገሰ ዜናዊ በትምህርታቸው ጎበዝ እንደነበሩም በወቅቱ አብረዋቸው ሲማሩ የነበሩ የትምህርት ቤት ጓደኞቻቸው በተለያየ ወቅትና አጋጣሚ መስክረዋል፡፡ ከዚያም በርካታ መጻህፍትን እንዳነበቡና ብዙ ጥናቶችን ማድረጋቸውም ይታወቃል።

የትግራይ ህዝብ እንደሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ በአገሪቱ ሰፍኖ የነበረው የግፍ አገዛዝ አንገፍግፎት በነበረበት ወቅት ለገሰ ዜናዊና ሌሎች የትግል አጋሮቹ የመማር እድል ያግኙ እንጂ አብዛኛው የትግራይ ወጣት ትምህርት ሳይሆን የጥይት ማእድ ነበር የቀረበለት። ህዝቡ በቋንቋው እንዳይጠቀም፣ ባህሉ እንዳያከብርና እምነትና ነጻነት እንዳይኖረው ከፍተኛ ጫና ይደረግበት ነበር። ከአገሪቱ ሠላም ርቆ ሁከትና ብጥብጥ ነግሶ ነበር። ወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄሮችና ህዝቦች የእኩልነት መብታቸው የተገፈፈበት፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የማይታሰብበት እና አምባገነናዊ ሥርዓት የሰፈነበት ነበር፡፡ ያንን አስከፊ ስርዓት በመገርሰስ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማስፈንና የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነት ለማረጋገጥ ወደ ሜዳ ከሄዱት ወጣቶች አንዱ አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ።

አቶ ሐሴት ፍስሃ ‘’ቅያ ትግራይ” በሚል ርዕስ በ2004 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሃፍ ላይ በፎቶግራፍ አስደግፎ እንዳሰፈሩት ወደ ትግል ሜዳ ቀድመው ከተጓዙ ሃያ የህወሓት ታጋዮች መካከል አንዱ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ እንደነበሩና 19ኙም ስሑል፣ ሙሴ፣ አግአዚ፣ ስዩም፣ አባይ፣ ስብሃት፣ ግደይ፣ በሪሁ፣ አስፍሃ፣ ዋልታ፣ ሸዊት፣ ሃይሉ፣ አውዓሎም፣ ስየ፣ ፀሃየ፣ ቀለበት፣ አሰግድ፣ አሕፈሮም፣ ተኽለ እና ፍትዊ እንደነበሩ ጠቅሰዋል፡፡

ወጣቶቹ የጀመሩት የትጥቅ ትግል ዳር ለማድረስ ባደረጉት ሁለንተናዊ ጥረት የአቶ መለስ አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር የትግል አጋሮቻቸው ይናገራሉ። በ1971 ዓ.ም ወደ አመራርነት የወጡት አቶ መለስ ባሳዩት ትእግስትና ብስለት የተሞላ የአመራር ክህሎትና ብቃት ደረጃ በደረጃ ወደ ከፍተኛ የአመራር እርከን መምጣት መቻላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ተዝቆ የማይልቅ እውቀትና ጥበብ እንዳላችው የረጅም ጊዜ የትግል አጋሮቻቸው ይመሰክራሉ። የትግራይ ህዝብ የትግል እንቅስቃሴ በድል እንዲጠናቀቅ የተለያዩ እቅዶችን በመንደፍና በመተግበር የነበራቸው ሚናም ከፍተኛ ነበር።

በአገሪቱ የሚገኙ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ነጻ አውጪዎች ወደ ጥምረት በማምጣትና የጋራ የትግል መድረክ በመፍጠር ረገድ ያላሳለሰ ጥረት አድርገዋል። ከእያንዳንዷ የህወሓትም ሆነ የኢህአዴግ ስኬት ጀርባ አቶ መለስ ዜናዊ እንደነበሩ በቅርብ የሚያውቋቸው የትግል አጋሮቻቸው ይመሰክራሉ።

በአገራችን በአፍሪካ ተወዳዳሪ ያልነበረው ዘመናዊ ትጥቅ የተላበሰ ግዙፍ ሰራዊት የተገነባበት ወቅት ነበር፤ የደርግ ዘመን። ከዚያም በላይ ሁሉንም በማጥፋትና በመደምሰስ፣ የተቃወመን ሁሉ በመግደልና በማሰቃየት የሚያምን የደርግ አመራር የነበረበት ወቅት ነበር። ዘመናዊ መሳሪያ እስካፍንጫ ታጥቆ የነበረውን የደርግ ስርዓት ለመደምሰስ የተነደፉ እቅዶችም በአብዛኛው የአቶ መለስ ዜናዊ እንደሆኑ ይነገራል። አቶ መለስ በህወሓትም ሆነ በኢህአዴግ የላቀ የመሪነት ሚና ነበራቸው።

ደርግን ለመገርሰስ፣ በኢትዮጵያ ሰላም፣ ዴሞክራሲና ልማትን ለማስፈን እና የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች እኩልነትና ነጻነትን ለማረጋገጥ በተለያየ ፈርጅና በተለያየ አካባቢ ይደረግ የነበረውን የትግል እንቅስቃሴ ኢህአዴግን መስርቶ የጋራ ትግል ሲጀምርም አቶ መለስ ዜናዊ የኢህአዴግ ሊቀመንበር ሆነው ለመመረጥ ያገዳቸው አንዳች ነገር አልነበረም። በዚህ ሂደትም በርካታ ስኬትን ያስገኙ ሃሳቦችን ያፈለቁ ታላቅ ሰው ናቸው - አቶ መለስ ዜናዊ፡፡

አስከፊው የደርግ ስርዓት በተገረሰሰበት ወቅት በሚሊዮን የሚቆጠር የደርግ ሰራዊት በመላ አገሪቱ እስከነ ሙሉ ትጥቁ ተበተነ። የደርግ ስርዓት አቀንቃኞችና ተጠቃሚዎች የነበሩ በርካታ ሰዎችም በስርዓቱ መደፍረስ አኮረፉ። በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ጥያቄ ውስጥ ይገባል የሚል አስተያየት መስተጋባት ጀመረ።

በተጨማሪም ኢህአዴግ ደርግን ደምስሶ አገሪቱን ማስተዳደር ሲጀምር ያገኘው ምንም አይነት ገንዘብ አልነበረም። ያገኘው ነገር ቢኖር ባዶ ካዝና ነበር። ከዚህ አንጻርም የአገሪቱን ኢኮኖሚ ማንቀሳቀስ የማይቻልበት ደረጃ ላይ ስለነበር ስጋቱን የበለጠ አስጨናቂ አድርጎት ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ እነዚህ የደርግ ስርዓት ርዝራዦች በእምነት ስፍራዎች በመሰግሰግ በሃይማኖት ሽፋን እንቅስቃሴ የጀመሩበትም ወቅት ነበር፡፡ ይህ አጠቃላይ የአገሪቱን ሰላምና መረጋጋት አደጋ ላይ ያስገባል ተብሎ የታመነበት እንደነበር ይታወሳል፡፡

የስርዓቱ አካሄድና አመጣጥን የተረዱ የከሰሩ ፖለቲከኞች የሃይማኖት ነጻነት በሚል ስም የክርስትና ሃይማኖት እምነትን ለማጥፋት የተነሳ ስርዓት ነው በሚል ስብከት ምእመኑን ማደናገር የተያያዙበት ሁኔታም ተፈጥሮ ነበር፡፡

አገሪቱ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚና በማህበራዊ መስኮች አሃዱ ብላ የመጀመሯን ያህል ከፍተኛ የትርምስ ቀጠና ትሆናለች የሚል ትንታኔ የሰጡ ምሁራንና የመገናኛ ብዙሃን ተቋማትም የትየለሌ ነበሩ፡፡

ኢትዮጵያ ግን አልፈራረሰችም፤ የብጥብጥና የሁከት ቀጠናም አልሆነችም፤ በወቅቱ ከዚህ ለመታደግ ለተደረገው ጥረት የአቶ መለስ ዜናዊ ብልህ አመራር ተጠቃሽ ይሆናል፡፡ የተበታተነ ህዝብ፤ የተለያዩ የታጠቁ የፖለቲካ ድርጅቶች በአገሪቱ በሞሉበት ወቅት፣ አገሪቱ ምንም ዓይነት መንቀሳቀሻ ፋይናንስ ባልነበራት ወቅት፤ አገሪቱን ወደ ትርምስ የሚያስገቡ በርካታ መሰረቶች በነበሩበት ሁኔታ መረጋጋትንና ሰላምን ማረጋገጥ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አንድነት በማረጋገጥ የተዋጣለት ስራ መስራታቸው ለማንም የተደበቀ አይደለም፡፡

መለስን የሚያውቁ አንዳንድ ሰዎች እንደሚገልጹት መለስ ለሁሉም አካባቢ ተወላጆች ያላቸው አመለካከት አንድና አንድ ነው፡፡ ሁሉንም በእኩል የማየት፤ ሁሉንም የማድመጥ፤ የሁሉንም መብት የማክበር ትእግስታቸውንና አቋማቸውን ሁሉም ይመሰክራል፡፡ አገሪቱ የመፈራረስና የመገነጣጠል አደጋ ተደቅኖባት በነበረበት ወቅትም የሽግግር መንግስቱ ፕሬዚዳንት ሆነው አገሪቱን ወደ ተረጋጋ ህይወት ለመመለስ ያሳዩት የአመራር ብስለትና ብቃት የሚያኮራ ነው፡፡

ብዙዎቹን የታጠቁ ሃይሎቻቸውን እያስፈቱ ወደሰላማዊ የትግል መድረክ እንዲመጡ ካስቻላቸው አንዱ ምክንያትም የአቶ መለስ ዜናዊ ትክክለኛ የህዳሴ ራዕይን የሰነቀ አመራር እንደሆነ በርካቶች ይስማሙበታል፡፡

የኢህአዴግን ዓላማ እየደገፉ ከሽግግር መንግስቱ ጎን ለመሰለፍ የቻሉ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በእውነት ኢህአዴግ ለህዝብ መሞቱን መቁሰሉንና በመጨረሻም ለድል በቅቶ እዚህ ደረጃ በመድረሱ እኩልነታቸው መረጋገጡ በመረዳት፤ ለዚህ ስኬት እውን መሆን ደግሞ የበሰለ የፖለቲካ አመራር መኖር እንደሆነ ሁሉም ይስማማል፡፡

ከ1983-1987 ዓ/ም የነበረው የሽግግር ወቅት በአግባቡ እንዲጠናቀቅና ሁሉም የፖለቲካ ሃይሎችና ብሄር ብሄረሰቦች በአገሪቱ ፓርላማ እንዲወከሉ፣ የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የማድረጉን ተግባር የኢህአዴግ ስርዓት የፈጠረው ቢሆንም በዚያ ውስጥ የአቶ መለስ ተራ ቀላል አልነበረም፡፡ ሁሉንም ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን አቀራርቦና አዲስቱን የኢትዮጵያ ጉዞ እውን ለማድረግ የተከተሉት የአመራር ስልትም በሳል ነበር፡፡ ስኬቱም ያን ያህል ጣፋጭ ሆኖላቸዋል፡፡ ይህ ማንም የሚያውቀው ነው፡፡ በዚሁ ብቃታቸውም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፓብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በ1987 ዓ/ም ለመመረጥ ችለዋል፡፡

የበሰለ የኢህአዴግ የፖለቲካ አመራርን ካነሳን አቶ መለስ በቀደምትነት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እንግዲህ ህወሓትን በመምራት በኋላም ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ጥምረትን በመፍጠርና ኢህአዴግን በመምራት ደርግን ለመደምሰስ የሚያስችል እቅድ ነድፎ አጋሮቻቸውን አስተባብረው በመተግበር ለውጤት የበቁት አቶ መለስ ዜናዊ ከደርግ ውድቀት ማግስትም የሽግግር መንግስት ፕሬዚዳንት ሆነው የሽግግሩን ወቅት በተገቢው ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አድርገዋል፡፡ ለዚህ ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለዋል፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ይሁንታ አግኝተው አገሪቱን ለመምራት በህዝብ የተመረጠ የመጀመሪያው ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ችለዋል፡፡

ይሁን እንጂ አሁን ካጋጠማቸው የጤና መታወክ ጋር ተያይዞ የተለያዩ የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅት አመራሮች የሰጧቸው አስተያየቶች በእውነትም “የማይሰማ ጉድ የለም” ያሰኛል፡፡ ይህንን ያህል ከፍተኛ አገራዊ አደራን ተሸክመው በተገቢው መንገድ ለመወጣት ቀን ተሌት ሲሰሩ የኖሩት መለስ ዜና በስራ ጫና ምክንያት ቢታመሙ ከፖሊሲ ጋር ምን ያገናኘዋል? ሲመለሱ ፖሊሲ ይቀይሩስ እንዴት ያስብላል? ዳሩ እነ ዶክተር የእለቱን እንጂ የወደፊቱን የሚያይ ልቦና እንዳልፈጠራላችሁ የእናንተው አባላት ሳይቀሩ መገንዘብ ችለዋል፡፡ የማይሰማ ጉድ የለም፡፡

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 245 guests