ሳይፍ አልኢስላም ጉዳዩ በኔዘርላንድስ እንዲታይለት ይፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2004 (ዋኢማ) - የቀድሞው የሊቢያ መሪ ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አልኢስላም ተጠያቂ የሆነበት ጉዳይ ከአገር ውስጥ ይልቅ መቀመጫው ዘሄግ በተባለችው የኔዘርላንድስ ከተማ በሆነው ዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲታይ የሚፈልግ መሆኑን ጠበቆቹ አስታወቁ። ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (ኢንተርናሽናል ከሪሚናል ኮርት-አይሲሲ) ሳይፍ አልኢስላምን በሰው ልጅ ላይ ከባድ ወንጀል በመፈፀም ወንጀል ተጠያቂ ማድረጉ ይታወቃል።
ኤኤፍፒ ጠበቆቹን ጠቅሶ እንዳመለከተው ሳይፍ አልኢስላም በሊቢያ ውስጥ ለፍርድ ቀርቦ የሞት ቅጣት ቢወሰንበት ድርጊቱ ከተራ የነፍስ ግድያ ተለይቶ እንደማይታይ መግለጹን ለዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት የቀረቡ ሰነዶች አመልክተዋል። ራሱን ለውጦ ለማምለጥ ሲሞከር እንደተያዘ የተነገረለት የ40ዓመቱ ሳይፍ አልኢስላም በአሁኑ ጊዜ ዚንታን በተባለችው ከተማ በሚገኘው ሚሊሺያ ኃይል ቁጥጥር ሥር እንደሚገኝ ተገልጿል።
የሊቢያ ጊዜያዊ መንግሥት እስካሁን ድረስ በሰው ልጅ ላይ ከባድ ወንጀል በመፈፀም ወንጀል (ከራይም አጌይንስት ሂውማኒቲ) ተጠያቂ የሆነው ሳይፍ አልኢስላም ተላልፎ እንዲሰጠው አይሲሲ ያቀረበውን ጥያቄ እንዳልተቀበለው ታውቋል። የሊቢያ ጊዜያዊ መንግሥት ሳይፍ አልኢስላም ፍርዱን በአገር ውስጥ ማግኘት አለበት የሚል አቋም ይዟል።
ሳይፍ አልኢስላም ራሱን ለውጦ ከአገር ለመውጣት ሲሞክር የተያዘው ሊቢያን ለ42 ዓመታት የመሩት አባቱ ኮሎኔል ሙአማር ጋዳፊ ባለፈው ዓመት ጥቅምት የትውልድ አካባቢያ ቸው ከተማ በሆነችው ሲርት ውስጥ ከተገደሉ በኋላ እንደሆነ ይታወሳል። ኤኤፍፒ ጠበቆቹን ጠቅሶ እንዳመለከተው ግለሰቡ ሞትን እንደማ ይፈራ አመልክቶ ፍርዱ በአገሩ ተካሂዶ በሞት እንዲቀጣ ከተወሰነ ውሳኔው ከተራ የነፍስ ግድያ ተለይቶ እንደማይታይ ገልጿል።
እ.ኤ.አ ባለፈው ሰኔ 2012 አንድ የአይሲሲ የጠበቆች ቡድን ዚንታን ውስጥ ሳይፍ አልኢስላምን ከአነጋገረ በኋላ በቁጥጥር ሥር ውሎ ለሦስት ሳምንታት ያህል እንደቆየ መገለጹ ይታወሳል። ቡድኑ ከሦስት ሳምንታት በኋላ ተለቅቋል።
ሜሊንዳ ቴይለር የተባለችው አውስትራሊያዊት የአይሲሲ ጠበቃና ሊባኖሳዊት አስተርጓሚዋን ሄለን አሳፍ፣ አሌክሳንደር ከደኮቭ የተባለውን ሩሲያዊ ጠበቃ፣እንዲሁም ኢስትባን ፐርላልታ ሎሲላ የተባለውን የስፔን ጠበቃ ያካተተው የአይሲሲ ጠበቆች ቡድን እ.ኤ.አ ሰኔ 7/2012 ዚንታን ከተማ ውስጥ በቁጥጥር ሥር የዋለው በተለይ ሜሊንዳ ቴይለር ለሳይፍ አልኢስላም በሕገ-ወጥ መንገድ ኢንፎርሜሽን ለማቀበል በመሞከሯ ምክንያት እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል። ሜሊንዳ ቴይለር ብዕር የሚመስል ካሜራና ከቀድሞ የሊቢያ ባልሥለጣን ለሳይፍ አልኢስላም በኮድ የተጻፈ ደብዳቤ ለማቀበል መሞከሯ ታውቋል።
የተጠቀሰው የአይሲሲ ጠበቆች ቡድን በፈቃድ ሊቢያ የገባው ሳይፍ አልኢስላም ተጠያቂ ለሆነበት ጉዳይ መከላከያ ዝግጅት ድጋፍ ለመስጠት እንደነበር ተገልጿል፡፡ የአይሲሲ ጠበቆች ልዑካን ቡድን ድርጊት የሊቢያን ብሔራዊ ደህንነት የተዳፈረ መሆኑን አንዳንድ የአገሪቱ ባለሥልጣኖች በወቅቱ ማመልከታቸው ተገልጿል።ይሁን እንጂ በሊቢያ መንግሥትና በአይሲሲ ባለሥልጣኖች መካከል በተካሄደ ውይይት የቡድኑ አባላት ሊለቀቁ ችለዋል።
አንዳንድ የሊቢያ ባልሥልጣኖች ያልተያዙት የቀድሞው መሪ ሙአማር ጋዳፊ ባለሟሎች ዜንታን ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውሎ የሚገኘውን ሳይፍ አልኢስላምን የማስለቀቅ ሙከራ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ግምት እንዳላቸው ተገልጿል።
| < Prev | Next > |
|---|


