ፕሬዚዳንት ትራውሬ የአንድነት መንግሥት ምሥረታ ዝግጅታቸውን አጠናቀቁ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2004 (ዋኢማ) - የማሊ ጊዜያዊ ሲቪል መንግሥት ፕሬዚዳንት ዳዮኩንዳ ትራውሬ አዲስ የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት የሚያደርጉትን ዝግጅት ማጠናቀ ቃቸውን እንዳስታወቁ ኤኤፍፒ ከባማኮ ያስተላለፈው ዜና አመለከተ። ፕሬዚዳንት ትራውሬ ይህን ያስታወቁት አዲስ የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ሁኔታ እንዲያመቻቹ በምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) የተሰጣቸው የጊዜ ገደብ በተጠናቀቀበት ዕለት እንደሆነም ተገልጿል። ኢኮዋስ ፕሬዚዳንቱ አዲስ የአንድነት መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለው ዝግጅት እንዲጠናቀቅ የሰጠው የጊዜ ገደብ ሐምሌ 31/2012 ነበር።

በማሊ አዲስ የአንድነት መንግሥት መመሥረት በአማፅያን ቁጥጥር ለዋለው ሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል ችግር መፍትሔ ለመፈለግ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ተገምቷል። የጊዜያዊ ሲቪል መንግሥት ፕሬዚዳንት በቅርቡ የወታደራዊ ቡድኑ ደጋፊዎች በቤተመንግሥቱ አካባቢ ባካሄዱት የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሂደት የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ወደፓሪስ በመሄድ ለሁለት ወራት የሕክምና ዕርዳታ ካገኙ በኋላ ሰሞኑን እንደተመለሱ የአንድነት መንግሥት የመመሥረቱን ዝግጅት በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ለማጠናቀቅ ተንቀሳቅሰዋል። የአንድነት መንግሥት ምሥረታ ዝግጅቱም እንደተጠቀሰው ከትናንት በስቲያ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።

ፕሬዚዳንት ዳዮንኩንዳ ትራውሬ ከትናንት በስቲያ ባደረጉትና በአገሪቱ ቴሌቪዥን የተላለፈው ንግግራቸው የተመሠረተውን ከፍተኛ የመንግሥት ምክር ቤት (ሃይ ካውንስል ኦፍ ስቴት) ራሳቸው በሊቀመንበርነት እንደሚመሩት አመልክተው ሰሜናዊን የአገሪቱ ክፍል ከተቆጣጠሩት አክራሪ ቡድኖች ጋር ድርድር የሚያካሂድ ኮሚቴ እንደሚመሠርቱ አስታውቀዋል። ይህ እርምጃ የጊዜያዊ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ቺክ ሞዲቦ ዲያራ ከሥልጣን መገለላቸውን አመላካች እንደሆነ ተገልጿል። በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠቅላይ ሚኒስትር ቺክ ሞዲቦ ዲያራን በችሎታ ማነስ ሲነቅፉ መቆየታቸው ታውቋል።

ኤኤፍፒ ማማዱ ዲያራ የተባሉትን ሶሺዮሎጂስት ጠቅሶ እንዳመለከተው አሁን በፕሬዚዳንት ዳዮንኩንዳ ትራውሬ የተወሰደው እርምጃ አገሪቱን ከቀውስ ለማላቀቅ በሚደረገው ጥረት ውስጥ አንድ ከፍተኛ እርምጃ እንደሆነ ተደርጐ ተወስዷል።
በፕሬዚዳንት ዳዮንኩንዳ ሊቀመንበርነት የሚመራው ከፍተኛ የመንግሥት ምክር ቤት ጊዜያዊውን ፕሬዚዳንት፣ ሁለቱን ምክትል ፕሬዚዳንቶችና እንዲሁም ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያልወገኑ ኃይሎችና አካላት ተወካዮችን እንደሚያካትት ተገልጿል። ከሁለቱም ምክትል ፕሬዚዳንቶች መካከል አንዱ የመከላከያና የደህንነት ክፍሎችን በኃላፊነት ከመምራት ጐን ለጐን አራት ወራትን ያስቆጠረውን የሰሜናዊ ማሊ ክፍል ጉዳይ እንደሚከታተል ተገልጿል።

ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት በሚቀጥለው የፕሬዚዳንት ምርጫ የአሁኑ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳ ንቶችና ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሁም ሚኒስትሮች ተፎካካሪ ሆነው ለመቅረብ እንደማይችሉም በዚሁ ንግግራቸው ማመልከታቸው ተገልጿል።

የቀድሞው ፕሬዚዳንት አማዱ ቱማኒ ቱሬ መንግሥት በሰሜናዊ የአገሪቱ ክፍል የሚንቀ ሳቀሱትን የአማፅያን ቡድኖች ለመቋቋም የአመራር ድክመት አሳይቷል በሚል ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ቢካሄድም ሁኔታውን የሚለውጥ እርምጃ እስካሁን አልተወሰደም። የተወሰደው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት እርምጃ በፈጠረው የደህንነት ክፍተት ተጠቅመው እስላማዊ ቡድኖች በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰሜናዊውን ክፍል ለመቆጣጠር ችለዋል።

ሰሜናዊ ማሊን የተቆጣጠሩት ፅንፈኛ ቡድኖች ቲምቡክቱ የተባለችውን ታሪካዊ ከተማ ጨምሮ በበርካታ የአካባቢው ከተሞች ታሪካዊ ቅርሶችን፣ ሐውልቶችን፣ መካነ-መቃብሮችንና ጥንታዊ መስጊዶች ከማውደም በተጨማሪ በአካባቢው ሰላም ላይም ስጋት መፍጠራቸው ታውቋል። ከዚህ በመነሳትም ማሊ በአባልነት የምትገኝበት የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ (ኢኮዋስ) ወደ ማሊ 3,000 አባሎች የሚገኙበት ወታደራዊ ኃይል የመላክ ፍላጐት አሳይቷል። ለዚህም ከማሊ ጊዜያዊ መንግሥት ጥያቄ፣ከተባበሩት መንግሥ ታት ድርጅት ፀጥታ ምክር ቤት ደግሞ ፈቃድ በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል።

የጊዜያዊ ፕሬዚዳንትነቱን ሥልጣን ከወታደራዊ ቡድኑ መሪ ሻምበል አማዱ ሳኖጐ ባለፈው ሚያዚያ የተረከቡት የ70 ዓመቱ ዳዮንኩንዳ ትራውሬ ማሊ በሰሜናዊ ክፍል በተፈጠረው ሁኔታ ልትፈርስ እንደማትችል በተጠቀሰው ንግግራቸው ማመል ከታቸው ተገልጿል።

የእርሳቸውን ሹመት የተቃወሙ ወገኖች እ.ኤ.አ ግንቦት 21/2012 ሁከት በፈጠሩበት ወቅት የአካል ጉዳት ደርሶባቸው ለሕክምና ዕርዳታ ወደፓሪስ ሲሄዱ የአመራር ኃላፊነቱን የወሰዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ቺክ ሞዲቦ ዲያራ ፅንፈኞች በሰሜናዊ ማሊ ይዞታቸውን ሲያስፋፋ ይህንኑ የሚገታ እርምጃ ለመውሰድ ባለመቻላቸው ተነቅፈዋል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 592 guests