የሶማሊያ መሪዎች አዲስ ሕገ መንግሥት አፀደቁ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2004 (ዋኢማ) - ሞቃዲሾ ውስጥ አንድ ሳምንት በስብሰባ ላይ የቆዩት የሶማሊያ ጎሳ መሪዎችና የማኅበረሰብ ተወካዮች አዲስ ሕገ መንግሥት ማፅደቃቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ያስተላለፈው ዜና አረጋገጠ። 645 የጎሳ መሪዎችና የማኅበረሰብ ተወካዮች ተካፍለውበት ለአንድ ሳምንት በውይይት ላይ የቆየው ጉባኤ ያፀደቀው አዲስ ሕገ መንግሥት የግለሰብ መብቶችን እንደሚያረጋግጥና የሕዝብ ውክልና ያለው ጠንካራ መንግሥት እንዲመሠረት ለማድረግ እንደሚያስችል ተነግሮለታል።

አዲሱ ሕገ መንግሥት የፀደቀው ከተሰብሳቢ 645 የጎሳ መሪዎችና ተወካዮች መካከል የ621 ድጋፍ በማግኘት እንደሆነ በአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ ተመልክቷል፡፡ አዲሱን ሕገ መንግሥት 13 የጎሳ መሪዎችና ተወካዮች ሲቃወሙት 11 ደግሞ በድምፀ-ተአቅቦ አልፈውታል።

የጎሳ መሪዎችና የማኅበረሰብ ተወካዮች አዲሱን ሕገ መንግሥት ያፀደቁት ከጊዜያዊ መንግሥቱ ፕሬዚዳንት ሼክ ሸሪፍ ሼክ አህመድና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዲዎሊ ሞሐመድ አሊ ጋስ ጋር ከተወያዩ በኋላ እንደሆነ ተገልጿል።

ለአለፉት ስምንት ዓመታት ሲዘጋጅ እንደቆየ የተነገረለትና ባለፈው ረቡዕ በጎሳ መሪዎችና ተወካዮች ጉባኤ የፀደቀው አዲስ ሕገመንግሥት የሶማሊያ ሕጋዊ መሠረት ኢስላማዊ ሕግ እንደሆነ፣ ማናቸውም ሕጎች ከሸሪያ ሕግ ጋር የሚጋጩ መሆን እንደሌለ ባቸው ያመለክታል። አዲሱ ሕገ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ከኢስላም በስተቀር ሌላ ሃይማኖት መሰበክ እንደማይኖርበትም እንደሚያመለክት ተገልጿል።

በአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ መሠረት አዲሱ የሶማሊያ ሕገ መንግሥት የእናትን ሕይወት ለማዳን ሲባል ውርጃን የሚፈቅድ ሲሆን፤ የሴት ልጅ ግርዛትን ከልክሏል። በሶማሊያ የሴት ልጅ ግርዛት የተለመደ ሆኖ እንደቆየ ይታወቃል።

አብሽር አብዲ የተባሉ አንድ የዚሁ ጉባኤ ተካፋይ አዲሱን ሕገ መንግሥት በሚመለከት በሰጡት አስተያየት ሶማሊያ አሁን ዴሞ ክራሲያዊና ሰላማዊ አቅጣጫ መያዟን አመልክተው፤ አዲሱ ሕገ መንግሥት ሕዝቡ ያለፈው ችግር ከፈጠረበት ጭንቀት እንዲፈወስ አመቺ ሁኔታ እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የጊዜያዊ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዲዌሊ ሞሐመድ አሊ ደግሞ የአዲሱ ሕገ መንግሥት በጎሳ መሪዎች ጉባኤ መፅደቅ የሽግግሩ ሂደት ማብቃቱን እንደሚያመለክት ገልጸዋል። የሶማሊያ ሽግግር መንግሥት የመቆያ ጊዜ የሚያበቃው እ.ኤ.አ ነሐሴ 20/2012 እንደሆነ ታውቋል። የጎሳ መሪዎች ጉባኤ 275 አባሎች የሚኖሩት ፓርላማ የመመረጥ ኃላፊነት እንደተሰጠውም ተገ ልጿል።

የአዲስ ሕገ መንግሥት መፅደቅ በአገሪቱ ታሪክ ውስጥ አዲስ ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ መከፈቱን አመላካች እንደሆነ በሶማሊያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ልዩ ተወካይ ኦገስቲን ማሂጋ አመልክተዋል። በአገሪቱ ውስጥ በአዲሱ ሕገ መንግሥት ላይ የተመሠረተ ጠቅላላ ምርጫ ለማካሔድ ጊዜ እንደሚወስድ ቢገመትም የሕገ መንግሥቱ መፅደቅ በራሱ አንድ ከፍተኛ እርምጃ እንደሆነ ተደርጎ ተወስዷል።

ባለፈው ረቡዕ 645 የሶማሊያ የጎሳ መሪዎችና የማኅበረሰብ ተወካዮች በአዲሱ ሕገ መንግሥት ላይ ድምፅ የሰጡት ሁለት አጥፍቶ ጠፊዎች ከስብሰባ አዳራሹ አቅራቢያ የፈንጂ አደጋ ለመፈፀም ከሞከሩ ከሁለት ሰዓት በኋላ እንደሆነ በአሶሺየትድ ፕሬስ ዘገባ ተመልክቷል። በስብሰባ አዳራሹ ላይ የፈንጂ አደጋ ለመፈፀም የሞከሩት አጥፍቶ ጠፊዎች አደጋውን ከማድረሳቸው በፊት መገደላቸውን አንድ የፖሊስ መኮንን በሰጠው መግለጫ አረጋግጧል። ቀደም ሲል ከሞቃዲሾ ከዚያ በኋላም ከተለያዩ ከተሞችና አካባቢዎቻቸው የተባረረውና በመባረር ላይ የሚገኘው የሶማሊያ አሸባሪ ቡድን አልሸባብ አልፎ አልፎ አደጋ የሚፈጽሙ አንዳንድ ሰርጎቦችን ወደ ሞቃዲሾ ከማስገባት እንዳልተቆጠበ ተገልጿል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 140 guests