ጋዜጣዊ መግለጫ እና የማጣሪያ ጨወታ!

  • PDF

ዮናስ

የከሰሩ ፖለቲከኞችን በአወልያና በመጅሊሱ ገበያ ትርፋማ እናደርጋለን፤

ያሸለቡ ትምክህተኞችን በዋልድባ መናንያን ፀሎት እናነቃለን፤

ለተኙ ሽብርተኞች መቀስቀሻ የፈንጂ አማራጮች ከታላቅ ቅናሽ ጋር አቅርበናል፤

በሞት አፋፍ ላይ ለሚገኙ ያረጁ ፖለቲከኞቻችን ደግሞ ነፍስ የሚዘሩ መምህራኖቻችን ከጭማሬያቸው ጋር ዝግጁዎች ናቸው፤

ሁሉንም ለማግኘት ወይም ሁሉንም ለማጣት ለደፈረ ማንኛውም ጡረተኛ የቀመምነው ግን ይለያል፣ ጉራፈርዳ፣ የዜሮ ድምር ፖለቲከኞች የዘመኑ ምርጫ ፤

እነዚህን ማስታወቂያዎች ካለፉት ሁለት ወራት ጀምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች እየሰማን እና እያነበብን ነው፡፡ የአሜሪካ ድምጽና ፣ኢሣት ከውጭ የተመረጡ ፕሮሞተሮች ሲሆኑ፤ የሀገር ውስጡን የማስታወቂያ ገበያ የተቆጣጠሩት ደግሞ ፍትህ፣ ፍኖተ ነፃነት፣ ነጋድራስ ና አዲስ አድማስ ናቸው፡፡ ደረጃቸውም እንደቅደም ተከተላቸው መሆኑን የኩባንያዎቹ የገበያ ጥናት አማካሪ የሆኑት ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕና ሂውማን ራይትስ ዎች የተባሉት ተቋማት አረጋግጠዋል፡፡ አክስዮኑን በበላይነት የያዘው መኢአድ የተባለው ኩባንያ ሲሆን የጥምር አክስዮን ድርሻ ያላቸውና መድረክ በሚል የንግድ መዝገብ የተመዘገቡት ኩባንያዎች ደግሞ ተከታዩን ቦታ ስለመያዛቸው አማካሪ ተቋማቱ ከሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የአማካሪ ድርጅቱ በሰጠው መግለጫ አፅንኦት የሰጠበት ዋና ጉዳይ የቀረቡት አማራጮች ለሁሉም ኩባንያዎች እንደየፍላጎታቸው እንዲያገለግሉ ሆነው የተሰናዱ መሆናቸውን ነው፡፡ ለክልል እና ብሄራዊ ሊግ መሳተፍ የሚሹ የዋልድባ ገዳምን መጠቀም ብቻ ተወዳዳሪ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ ለአዲስ አበባው ፕሪሚየር ሊግ መወዳዳር ለሚሻ ኩባንያ ደግሞ አወልያንና መጅሊሱን ጠዋትና ማታ መውሰድ ግድ ይለዋል፡፡ ለሻምፒየንስ ሊጉ የቀመምነው ግን አሉ አማካሪዎቹ፦ ከተከለከሉ የምግብ አይነቶችና ከማናቸውም መጠጥ መቆጠብን ይጠይቃል፡፡ ይኸው ጉራፈርዳ በመባል የሚታወቀውን መድሃኒት በቀን ሶስቴ ከተጣለው ገደብና ማስጠንቀቂያ ጋር አዋህዶ የሚጠቀም ኩባንያ ሌላም ማሟላት የሚገባው ተጨማሪ ነገር አለ፡፡ ይኸውም ከደብረማርቆስ እስከ ቤንች ማጂ የግር ጉዞ ማድረግና በቀን አንዴ “ፕሪማች” መግለጫ መስጠት ይገባዋል፡፡

በእያንዳንዱ መግለጫ ላይ የስታራቴጂው ዋና አጋር የሆኑት ፍትህ፣ ፍኖተ ነፃነት፣ ቪኦኤና ኢሳት መገኘታቸውን በቅድሚያ ማረጋገጥ አስፈላጊ ሲሆን የኢቲቪና የአዲስ ዘመን ሰዎችና መቅረጫዎች የሚለቁት ጨረር መድሃኒቱን እንዳይሰራ ስለሚየደርገው ብርቱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት ሲሉም አማካሪዎቹ ከበድ ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል፡፡ ከእኛ ትዕዛዝ ውጪ የሚወሰዱ ማናቸውም መድሃኒቶች በኩባንያዎቹ ላይ የማያንሰራራ ክስረት ከማስከተላቸውም በላይ ቃልቲ ሆስፒታል እስከ እለተ ሞት ሊያሰተኙ የሚችሉ ከባድ መድሂኒቶች ናቸው፡፡

በተረፈ ግን እኛ ባዘዝነው መሰረት ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግና በልኩ መድሃኒቱን መውሰድ ኩባንያዎቹን ለሚንሊክ ቤተመንገስት የሚያበቃ ሲሆን ላረጁት ልጅነትን ለተኙትም ደግሞ ትንሳዔ እንደሚሆን ያለጥርጥር መናገር እንችላለን ብለው መግለጫቸውን ሲያጠናቅቁ በእለቱ ከየኩባንያው ከተገኙ የስራ ሃላፊዎችና ከተመረጡ ሚዲያዎች የመጡ ዋና አዘጋጆች ለአማካሪ ተቋማቱ ጥያቄና አስተያተቶችን አቅርበዋል፡፡

የምንወስዳቸው ምግቦችና መጠጦች እንዲሁም የተከለከሉት ሁሉ በዝርዝር በዚሁ መድረክ ላይ ቢቀርቡልን የሚለው ጥያቄ የመድረኩ ኩባንያ ባለድርሻ ከሆነ አንድ አባል የቀረበ ሲሆን የጋምቤላን እርሻ ልማትና የሊዝ አዋጁን አልፍ አልፎ መውሰድ ለክልልና ብሄራዊ ሊግ ለሚወዳደሩት ኩባንያዎች አይጠቅምም ወይ? የሚል ጥያቄ ያነሱት ደግሞ “ሩዝ የተቅማጥ መድሃኒት” መሆኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በምርምር የደረሱበት ፕሮፌሰር ናቸው፡፡

ከፕሮፌሰሩ ጋር እኩል የአክስዮን ድርሻ ያላቸው አንድ የፖለቲካል ሳይንስ ዶክተር ደግሞ ውድድሩን ሊያደምቁ የሚችሉ ቲፎዞዎችን ከየትምህርት ተቋማቱ ለማስመጣት እንዲቻል ልምዳቸውን ያጋሯቸው ዘንድ የጠየቁ ሲሆን የፓርላማው ብቸኛ ተጠሪም ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል ፦ ከአወልያ እና ዋልድባም በላይ ምህዳሩንና የኑሮ ውድነቱን በቀን ቢያንስ አንዴ እንኳ መጠቀም ለፕሪሚየር ሊጉ ወሳኝነት ይኖረዋል የሚል ሃሳብ ስላለኝ አማካሪው አስተያየት ቢሰጥበት ያሉ ሲሆን ለሻንፒየንስ ሊጉ የተቀመመውን ግን ያለጨረታም ቢሆን ለብቻችን እንዲሰጠን ሲሉ ተማጽኖ ያቀረቡት ደግሞ ጡረታ በመውጣትና ባለመውጣት መሃል ላይ የሚገኙት የመኢአድ ኩባንያ ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡

መድረኩን የሚመሩት የኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕና ሂውማን ራይትስ ዎች አመራሮች በነሱ በኩል የሚመለሱትን እንዲለዩና የተወሰኑት ግን በቀጣዩ ጋዜጣዊ መግለጫ የሚመለከታቸው አልሸባብና አልቃይዳ ተገኝተው ማብራሪያ እንደሚሰጡ ቃል በመግባት ወደምላሹ ከማለፋችን በፊት ግን አጋር ሚዲያዎቻችን አስተያየትና ጥያቄ ካላቸው ማቅረብ ይችላሉ ሲሉ መድረኩን ለቤቱ ሰጥተዋል፡፡

እድሉን ቀድሞ የወሰደው የፍትህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች አዋጅ ጀምሮ፣ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ፣ የሊዝ አዋጁና የንግድ ምዝገባና የግብር ሥርዓቱ፣ የታክሲ ስምሪት መመሪያውን ጨምሮ በርካታ ቅመሞችን ፍቱን ናቸው ስትሉ ማቅረባችሁንና ኩባንያዎቹም የእነዚህን መድሃኒቶች ፍቱንነት በኛ በኩል በተደጋጋሚ ሲያስነግሩ ቢቆዩም ፍቱንነታቸው ቀርቶ ማስታገሻ መሆን እንዳልቻሉ የኩባንያዎቹ ደንበኞች ወደ እኛ ጥያቄ እያቀረቡ ነው፡፡ ስለሆነም አሁን የቀረቡት አዲስ አማራጮች ኩባንያዎቹን ለተጨማሪ ኪሳራ ከመዳረጋቸው በፊትና እኛንም ከተጠያቂነት ለማዳን ይረዳ ዘንድ የቀደሙት አማራጮች ያልተሳኩበት ምክንያት ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ አለብን የሚል አስተያየት ሰጥቶ መድሃኒቱ ካልሰራ ተፎካካሪ ኩባንያዎች ስለሚወስዱት እርምጃና ቅድመ ጥንቃቄ፣ እንዲሁም ስለ ውድድሩ መሪዎች ዳኞችና መሰል ጉዳዮችም አንድ የጋራ አቋም ይዘን ብንለያይ የተሻለ ይሆናል ሲል ተጫማሪ አስተያየት ሰጥቷል፡፡

በቅድመ ዝግጅታችን ላይ ሚስጥር መሆን ስለሚገባቸው ጉዳዮችም ዛሬ መነጋገርና መጨረስ ግድ ይለናል ያለው የፍትህ ዋና አዘጋጅ ለአራት ጊዜ የሻምፒየንስ ሊጉ ባለቤት ከሆነው ምክር ቤት ሬድዋንና በረከት ወጥመድ የምናመልጥበት የማሪያም መንገድም ከወዲሁ ማዘጋጀት ያለብን ሲሆን የህገ መንግስቱን አንቀጽ የምንጠቀምበት አግባብ ምን መሆን እንዳለበት ከወዲሁ መለየት አለብን ሲል አስተያየቱንን አጠናቋል፡፡

ከፍኖተ ነፃነት ቪኦኤና ኢሣት የተገኙት ጋዜጠኞች በፍትህ ዋና አዘጋጅ ከቀረበው አስተያየትና ጥያቄ የተለየ ሃሳብ ስለሌለንና ተጫማሪ ነገር ካለም ተደዋውለን መጨረስ የሚቻል በመሆኑ በኩባንያዎቹና በዋና አዘጋጁ ለቀረቡት ጥያቄዎችና አስተያየቶች ከመድረኩ ምላሽ ይሰጠን ብለዋል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን ተከትሎ ለወጣቶች ንግግር ያደርጋሉ የተባሉ አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህር አሁን በታዳሚው መሃል ተገኝተዋል፡፡

አማካሪዎቹም ከኩባንያዎቹና ከአጋር ሚዲያዎች ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ለመስጠት በዝግጅት ላይ ናቸው፡፡ የሂውማን ራይትስ ዎቹ

ተወካይ ማብራሪያውን ጀመሩ፡፡ መጀመሪያ ከአጋር ሚዲያው በኩል የተነሱት ጥያቄዎች መመለስ እንዳለባቸው በአጽንኦት ተናገሩ፡፡ ምክንያቱም አሉ የአማካሪ ተወካዩ የፊተኞቹ ቅመሞች የፎረሹበትን ምክንያት ግልጽ ማድረግና የጋራ መግባባት ላይ መድረስ ለቀጣዩ ጉዞ መሰረትና ውጤታማነት አስፈላጊ ስለሆነ፡፡

ስለሆነም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የፀረ ሽብርተኝነት፣ የሊዝ፣ የግብር ሥርዓቱና በወቅቱ የነበሩት ሌሎች አዋጆችን በተመለከተ ስህተቱ የሁላችንም እንደሆነ መጀመሪያ መስማማት አለብን። በርግጥ የስህተቱን ትልቅ ድርሻ የምንወስደው እኛና ኩባንያዎቹ ብንሆንም አጋር ሚዲዎችም ብትሆኑ ድርሻ እንደነበራችሁ ልትዘነጉት አይገባም።

ጉዳዩን ዘርዘር አድርገን ስንመለከተው ተፎካካሪያችን ሶስት ጊዜ የፕሬሚየር ሊጉን፣ አራት ጊዜ የክልሉንና የሻምፒየንስ ሊጉን ዋንጫ እንደማንሳቱ ሰፊ የማጥቃት ልምድ ሊኖረው እንደሚችል መጀመሪያውኑ መገመት ነበረብን፡፡ ይህን ባለማድረጋችንና አሰላለፋችንን ከ97ቱ እና 2002 ቱ ባለመቀየራችን የደረሰ ክሽፈት እንጂ አሁንም ቅመሞቹ ስራ ላይ አይውሉም ማለት አይደለም፡፡

ሁለተኛው ስህተት አጫዋቹን ህገ መንግስት ወደጎን ትተን ዋናው ትኩረ ታችን ቲፎዞው ላይ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው፡፡ ያም ሆኖ ቲፎዞዎቻችንን እንኳ በቅጡ ያለየንበት ሁኔታም እንደነበር በኋላ ካደረግነው ግምገማ ተገንዝበናል፡፡

ይኸውም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን የተመለከተውን አዋጅ በመጠቀም ከጎናችን ተሰልፈው የነበሩት ቲፎዞዎች የሊዝ አዋጁ ላይ አብረውን አልነበሩም፡፡ የሊዝ አዋጁ ላይ አብረውን ለነበሩት ቲፎዞዎች የግብር ሥርዓቱ ምናቸውም አልነበረም፤ የአረቡ አለም አብዮትን ስናነሳ የተፎካካሪያችን ጥቃቅንና አነስተኛም ከጎናችን ይሆናል የሚል የየዋህ አካሄድም ተከትለን ነበር፤ እነዚህ ሁሉ ተደማምረው የቱ ጋር እንዳለን እንኳ እስክንዘነጋ ድረስ ሽንፈት አድርሰውብናል፡፡ እዚህ ላይ ግን አጋር መዲያዎቻችን የተበታተነው ቲፎዞን በማስታሳሰርና ወደ አንድ በማምጣት በኩል ሚናችሁ ከአዲስ ዘመንና ከኢቲቪ በጣም ዝቅ ያለ መሆኑን ልትገነዘቡት ይገባል፡፡ ለዚህም ነው ስህተቱ የናንተም ነው ያልነው፡፡

ሌላው በቀይ የወጡትን እነ ሰለሞን ክፍሌ፣ ብርሃኑ ነጋ ፣አንዷለም አራጌና እስክንድር ነጋ ለማሰለፍ ያደረግነው ጥረት በአጫዋቹ ህገመንግስት በኩል ዋጋ አስከፍሎናል፡፡ በአቤቱታ ሰሚ ኮሚሽኖች በኩል ያቀረብነው ኡኡታ ተሰሚነት የተነፈገውም ለዚህ ነው፡፡ ሌላውና ትልቁ ስህተት ደግሞ የኩባንያዎቹ ነው፡፡ በተለይም የመድረኩ የአክስዮን መስራችና አመራር የሆኑት ፕሮፌሰር የጋምቤላን ቅመም መጠቀም እንዳንችል “የተቅማጥ መድሃኒት” የሚል ቫይረስ ይዘውብን መምጣታቸው ሌላው ዋጋ ያስከፈለን ጉዳይ ነው፡፡ ይህንኑም ኩባንያዎቹ ባደረግነው ስብሰባ ያረጋገጡና የተማመኑበት መሆኑን የተከበራችሁቱ አጋር ሚዲያዎቻችን ትረዱልን ዘነድ እንጠይቃለን፡፡

በኛ ባማካሪዎቹ በኩል የአንዳንድ ባለሀብቶችን ሃሳብ ብቻ መሰረት አድርገን የሁሉም ባለሀብቶች ሃሳብ እንደሆነ በመውሰድ ለኩባንያዎቹ የሰጠነው ምክር ተገቢ እንዳልነበር በመገንዘብ የካሳ ክፍያ ፈጽመናል፡፡

ሌላውና የመጨረሻው ስህተት ዴያስፖራው አካባቢ ያሰባሰብነው ቲፎዞ 200 ሆኖ ሳለ በነቪኦኤ በኩል 10 ሺህ እየተባለ ሲነገረን የምናገኘውን የገንዘብ ድጋፍ ስናባዛ የነበረው በ10 ሺህ ደጋፊዎች ነበር። ሂሳቡ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘበትና ጨዋታው በተጋጋለበት ሰዓት ግን ኪሳችን ባዶ በመሆኑ በተለያየ ትጥቅ ለመጫወተና ኳሷንም ለተፎካከካሪው ቡድን በተደጋጋሚ ለማቀበል በመገዳዳችን ተሸንፈናል።

አሁን ደግሞ የኢንተርናሽናል ኪራይስስ ግሩፕን የወከሉት አማካሪ ማይኩን ወደ አንደበታቸው አስጠጉና መናገር ጀመሩ።

ከኩባንያዎቹ ከቀረቡት አስተያየቶች እና ጥያቄዎች ፓርላማ የወከልነው ባልደረባ ያነሳው ጥያቄ ከዚሁ ከእነ ተመስገን ጋር ተያያዥነት ያለው በመሆኑ እሱን በማብራራት ጀምራለሁ።

የፓርላማው ተጠሪና የአንድነት ባለአክሲዮኑ እንደተናገሩት የኑሮ ውድነቱንና ምህዳሩን ከአሰላለፉ ያወጣናቸው ሁለት ቢጫ ያለባቸው በመሆኑና አጫዋቹን ህገ መንግስት መሸወድ ስለማይቻለን ነው። የሊዝ አዋጁን የግብር እና የታክሲ ስምሪቱን ግን በተቀያሪ ወንበር ላይ አስቀምጠን እንደ አስፈላጊነቱ እንጠቀምባቸዋለን የሚል መግባባት ላይ በመድረሳቸን ነው።

ምክንያቱም ታስታውሱ እንደሆን የሊዝ አዋጁን በግራ መስመር እንዲያጠቃ ስናደርገው ተፎካካሪው ግራ ተከላካይ ያደረገው የወጣቶችን ሊግ ነበር።

የመሃል አጥቂው የግብር ስርዓቱ አንዲሆን ስንስማማ በርካታ ጎሎችን ጠብቀን ነበር በወቅቱ ግን ተፎካካሪያችን የህዳሴው ግድብ የተባለ ተከላካይ በ80 ቢሊዮን ብር ከጣልያን አስፈርሞ ስለነበር ማለፍ ሳይቻለው ከመቅረቱም በላይ በሰራው ፋውል የግብር ስርዓቱ በሁለት ቢጫ ካርድ አንዲወጣ ተደርጓል። የኑሮ ውድነቱም በቀኝ በኩል ሰፊ ጥቃት እንደሚሰነዘር ቢጠበቅም የዋጋ ማረጋጋቱ የነበረው ወቅታዊ አቋም ጥሩ ስለነበረ ሊሰበር አልቻለም።

ስለሆነም ከዚህ ብዙ ስለተማርን አዳዲስ አጥቂዎችንና ተከላካዮችን ከኒዮሊበራሉ ሃይል በዝውውር አምጥተናል። አሰላለፋችንም ተፎካካሪውን መሰረት ያደረገ ነው። ለጊዜው ኢህአዴግ አካባቢ ካስቀመጥናቸው ጆሮዎቻችን እንደተረዳነው ቡድኑ የሚከተለው አሰላለፍ 4 4 2 የተባለውን ፎርሜሽን ሲሆን ጎል ጠባቂው ደግሞ የደቡቡ ህገ መንግስት ነው።

በተከላካይ መስመር የፀረሽብርተኝነት አዋጁ፣ማሳለጫው፣የባቡርሃዲድ እና ኮንዶሚኒየም ሲሆኑ የአማካዩን ስፍራ የሚይዙት ደግሞ፣ የተወካዮች ምክር ቤት፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ፣ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር እና ኢህአዴግ ጽ/ቤት ናቸው። አጥቂዎቹም ያው የጠበቅናቸው የህዳሴው ግድብና ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ሆነዋል።

ስለሆነም በኛ በኩል የሚኖረው አሰላለፉ ይህንኑ የተቃራኒውን ቡደን አሰላለፍ ታሳቢ ያደረገ እንዲሆን ታስቧል።

በዚሁ መሰረት 4 5 1 ፎርሜሽን በመከተል የአጥቂነቱን ስፍራ ለመኢአድ ሰጥተናል። በአማካይ ስፍራ አወልያን፣ መጅሊሱን፣ ዋልድባን፣ መምህራኑን እና አልቃይዳን የምንጠቀም ሲሆን አልሸባብ፣ ጉራፈርዳ ፣ አንድነትና መድረክ የመከላከሉን ስራ ይወስዳሉ።

ጎል ጠባቂው ደግሞ ግንቦት 7 ነው። ቦንድ መኢአድን እንደአስፈላጊነቱ ተክቶ እንዲገባ ዝግጅቱን አጠናቋል።

ሌላው ተፎካካሪያችን በተቀያሪነት ያስቀመጠው ሌላ ሁለተኛ ቡድን ሆነው መውጣት የሚያስችል አቅም ያላቸውን ተጫዋቾች መሆኑንም ከጆሮዎቻችን ሰምተናል። ከእነዚህም ውስጥ ስኳር ኮርፖሬሽን፣ የባቡር ሃዲድ ፣ኮንደሚኒየም እና የመሳሰሉት የተፎካካሪው ተቀያሪ ተጫዋቾች ናቸው።

ከጆሮዎቻችን እንደሰማነው ሌላና ትኩረት ማድረግ የሚያስፈልገንን አብይ ጉዳይም አለ። ይኸወም የተፎካካሪው የልምምድ ስታይል አንድ ለአምስት በሚል ስትራቴጂ የበሰለ ሲሆን በዚህ ስልቱም ከተፋሰስ ልማት ጋር ባደረገው የወዳጅነት ጫወታ 11.1 ጎሎችን በማግባት አሸንፎ ወጥቶበታል። የኳስ አያያዙም(boll possetion) 96.1% በሆነ የበላይነት በልጦበታል።

በካታንጋ በኩል ሙሉ ቲፎዞዎች ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲና ከሌሎች ቦታዎችም እንዲሰባሰቡ ለባለአክሲዮኑ ዶክተር አስተማሪ የቤት ስራ የተሰጠ ሲሆን ሴት መምህራኖች ደግሞ ምስማር ተራን ቀውጢእንደሚያደርጉት ቃል ገብተውልናል። የሆቴል የመስተንግዶና የትጥቅ ጉዳይ በሻዕቢያና በአውሮፓ ህብረት በኩል የሚሸፈን ሲሆን ከእኛ የሚጠበቀው በተሰጠን ቦታ ሁሉ በትኩረት መስራት ነው።

ሌላው መሰረታዊ ነጥብ ደግሞ አጋር ሚዲያዎቻችንን የተመለከተው ጉዳይ ነው። ፍትህ አርብ መታተሟን በመቀጠል ከቅዳሜው ጨዋታ በፊት በሚገባ ተፎካካሪውን ማደናበርና ቲፎዞውን የወጣት ሊግና የሴቶች ሊግ ማስበርገግ አለባት። ቀጥላም ተከታዩን አርብ ሳትጠብቅ እሁድ በድጋሚ ካሸነፍን ደስታውን ከተሸነፍን ደግሞ የተጭበርብሯል ዜናዎችን ይዛ መውጣት የግዷ ነው።

ቪኦኤና ፍኖተ ነፃነት በተለመደው እለትና ሰዓት ፍትህን መነሻ እያደረጋችሁ መደበላለቅ አለባችሁ።

ተጨማሪ ካለ በጫወታው ስፍራ ስንገናኝ እንነጋገርበታለን ።መልካም ውጤት እንዲገጥመንም እንመኛለን ሲሉ ከታዳሚው በተቸራቸው ጭብጨባ አማካሪዎቹ ጋዜጣዊ መግለጫውን አጠናቀቁ።

ቅዳሜ ደረሰ፣ ጥላፎቅን ጨምሮ ከማን አንሼና ሌሎችም ቦታዎች በኢህአዴግ ደጋፊዎች ተሞልተዋል። ካታንጋን ይሞሉታል በተባሉት የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ፈንታ ጥቂት ስራፈቶች ተገኝተዋል። በሴት መምህራኑ ምትክ የተገኙት ደግሞ ውስን የመኢአድ አባላቶች ናቸው።

ዳኛው ህገ መንግስት ፍርድ ቤቱንና ፍትህ ሚንስቴሩን በአራጋቢነት ይዘው ቦታቸው ላይ ተገኝተዋል። በግብርናና ጥቃቅን አነስተኛ የሚመራው የኢህአዴግ ቡድን አረንጓዴ ማልያ አርማ ያለው ቢጫ ቁምጣና ቀይ ገምባሌ ለብሷል። የተቃውሞው አክሲዮን ማህበር በመኢአዱ ባለቤትና ስራ አስኪያጅ መሪነት ሙሉ ጥቁር ማልያና ምስማር የተጠቀጠቀ ታኬታ ተጫምቷል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የሁለቱም ቡድኖች እርስ በርስ ሰላምታ የመለዋወጥ ስነ ስርዓት በክብር እንገዳው ምርጫ ቦርድ በኩል አደረጉ።

መጀመሪያ “የዜግነት ክብር” የሚለው የባለአረንጓዴ ቢጫ ቀይ ማሊያ ለባሹ ቡድን መዝሙር ተዘመረ፤ ቀጠለናም |ኧረ ጥራኝ ዱሩ ኧረ ጥራኝ ጫካው´ የአክስዮኑ ቡድን መዝሙር ተዘምሮ ጨዋታው ተጀመረ።

በተጀመረ በ7ኛው ደቂቃ አወልያ ጎል አገባ፤ ብዙም ሳይቆይ ግብ ጠባቂው ግንቦት ሰባት አማካዩ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ በሰራው ከባድ ጥፋት በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጣ፤ የአክሲዮኑ ተሰላፊ መምህር ሳይመዘገብ የገባ የሻቢያ አንድ ክለብ ተጫዋች መሆኑ ተረጋገጠና እሱም የቀይ ካርድ ሰለባ ሆነ።

ጨዋታው እንዲህ እንዲህ እያለ ሲቀጥል የህዳሴው ግድብ 2 የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅዱ ደግሞ 3 በማግባት የመጀመሪያው ግማሽ ተጠናቀቀ።

የባለአክስዮኑ ቡድን አሰላለፉን በመቀየር ከአማካይ ስፍራ መጅሊሱን አንስቶ ከመኢአድ ጋር ቦንድ እንዲያጠቃ ተደረገ። ሁለቱም አጥቂዎች በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ 10 ደቂቃዎች ተደጋጋሚ ሙከራዎች ቢያደርጉም ከግንባሩ ግብ ጠባቂ የደቡብ ህገ መንግስት ያመለጠች ኳስ ግን አልነበረችም።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ 20 ደቂቃዎች ሲቀሩት በተደጋጋሚ ጥቃት ያደረገው ግንባር በህዳሴው ግድብ በኩል ተጨማሪ ሶስት ጎሎች እና በኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት በኩል ሶስት ጎሎች በማከል 10 ለ 1 ሲመራ ባለቀ ሰዓት ላይ ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ በ“ፎርቢች” ያገባትና ሃትሪክ የሰራባት ጎል ግን ከሁሉም የተለየችና ተመልካቹን ያስደመመች ሆነች።

በዚህ ጫወታ ላይ ከባለአክስዮኑ በኩል መድረክ አንድነት አወልያና መምህሩ ከከባድ ማስጠንቀቂያ ጋር የቢጫ ካርድ ያዩ ሲሆን በቀጣዩ ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት ከ11 በላይ ጎል ይጠበቅባቸዋል።

የባለአክሲዮኑ አሰልጣኝ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከጫወታው በኋላ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ዳኛው አጭበርብሮናል፣ ግብ ጠባቂ ለሆነው ደቡብ ክልል ያደላ ሲሆን፣ ከቲፎዞዎቹ ብሄር ብሄረሰቦች የደረሰብንን ውግዘት እንኳን ለመመልከት አልፈቀደም ።ዞሮዞሮ ተከታዩ ጨዋታችን በራሳችን ሜዳ ጉራ ፈርዳ የሚካሄድ በመሆኑ እጥፍ ጎሎችን በማስቆጠር እንደምናሸንፍ አንጠራጠርም ብለዋል።

የግንባሩ ቡድን መሪ ጥቃቅን እና አነስተኛም በተመሳሳይ በሰጡት መግለጫ ተጋጣሚዎቻችን ለጫወታው ህግ ካለመገዛታቸውም ባሻገር አወልያ ዋልድባ ምናምን የሚሉ መርዘኛ የመድሀኒት ስሞችን በቅጽል ስምንት በመጠቀም ወደሜዳ መግባታቸው በራሱ ህገ ወጥነት መሆኑን ለኮምሽኑ ምርጫ ቦርድ እናመለክታለን ያሉ ሲሆን በተከታዩ ግጥሚያም ልምምዳችንን ባለመድነው አንድ ለአምስት አጠናክረን በመቀጠል የ40 በመቶ ተጨማሪ የጫወታ ብልጫ አሳይተን በአሸናፊነት እንደምንወጣ አንጠራጠርም ብለዋል። የጫወታው ኮከብ(man of the game) ደግሞ የህዳሴው ግድብና የትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሆነዋል።

ጨዋታው ከባድ እንደነበር ለኢቲቪ አስተያየታቸውን የሰጡት የዕለቱ ዳኛ ህገ መንግስት ፌዴሬሽኑ የምረጫ ቦርድ ስርነቀል የሆነ ለወጥ እንዲያደርግ ለባለአክሲዮኑ ቡድን ማሳሰቢያ ካልሰጠ በስተቀር በጫወታው ላይ ተሰልፈው የነበሩት የባለአክሲዮኑ ተጫዋቾች እንደስማቸው መርዛማ መድሃኒቶች አንጂ ኳስ ተጫዋች አልነበሩም። ችግሩም በቦርዱ በኩል ካልተፈታ የቀጣዩ ጫወታ አጫዋች ጫወታው ሳይጀመር የሚያቋርጥበት አልያም ሁሉም የባለአክሲዮን ተጫዋቾች ከሜዳ በቀይ የሚወጡበት አጋጣሚ ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ። ስማቸውን በመርዛማ መድሀኒቶች ቀይረው ስለመምጣታቸውም በኔ በኩል ለሚመለከተው አካል ሪፖረት አድርጌያለሁ።

የባለአክሲዮኑ ቡድን አማካሪ ሂውማን ራይትስዎች ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበለት ጥያቄ፦ የጫወታ ፍልስፍናችንን በፈላስፋው ቡድን መሪ አማካይነት ወጣቶች ላይ አድርገን በመስራት ለቀጣዩ ጫወታ ዝግጅታችንን ከወዲሁ እናደርጋለን ሲሉ አጥቂው መኢአድ ሙሉ ትንፋሽ የሌለው በመሆኑ በቀጣዩ ጨዋታ እንማይሰለፍ ውስጠ አዋቂ ምንጮችን በመጥቀስ አዲስ ዘመን ዘግቧል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 190 guests