በአሌፖ ከተማ ውጊያ እንዲቆም ተጠየቀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2004 (ዋኢማ) - የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አስተባባሪ የሆኑት የድርጅቱ ረዳት ዋና ፀሐፊ ቫለሪ አሞስ የሶሪያ ተፋላሚ ኃይሎች አሌፖ የተባለችውን ከተማ ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞችና አካባቢዎች በሚያካሂዱት ጦርነት የሰላማዊ ሰዎችን ሕይወት ከማጥፋትና ከመጉዳት እንዲቆጠቡ የሚጠይቅ ጥሪ አስተላለፉ። ቫላሪ አሞስ ይህን ጥሪ ያስተላለፉት የሶሪያ መንግሥት ጦር ኃይሎች የአሌፖን ከተማ ከታጣቂ ተቃዋሚ ቡድኖች ለማፅዳት ከፍተኛ ዘመቻ በከፈተበት፣ ታጣቂዎችም ዘመቻውን ለመመከት የሚያካሂዱት ፈልሚያ እልቂት በማስከተል ደረጃ ላይ እንደሆነ በሚነገርበት ወቅት እንደሆነ የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።
የተመድ ሰብአዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አስተባባሪያዋ የሶሪያ ተፋላሚ ኃይሎች በተለይ በአሌፖ ከተማ የሚያካሂዱትን ከፍተኛ ውጊያ እንዲያቆሙና ለተጐጂው ሰላማዊ ሕዝብ ሰብአዊ ዕርዳታ እንዲደርስ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል። ቫለሪ አሞስ በዚሁ ማሳሰቢያቸው የመንግሥቱ ጦር ኃይሎች በአሌፖና በደማስቆ ከተሞች በታንኮች፣ በጦር ሄሊክፕተሮችና በሌሎች ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎች የሚያካሂዱት ድብደባ በሰላማዊው ሕዝብ ላይ የሚያደርሰው የሕይወት ጥፋትና ጉዳት በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ገልጸዋል። በመሆኑም ተፋላሚ ኃይሎች ውጊያቸው ሰላማዊን ሕዝብ ኢላማ እንዳያደርግ፣እንዲሁም በውጊያው አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ሕዝብ ነፍስ አድን ዕርዳታ እንዲያገኝ አመቺ ሁኔታ እንዲፈጥሩ ጠይቀዋል።
ከአሌፖ ከተማ የሚወጡ ዘገባዎች እንደሚያመለክቱት ከአገሪቱ ከተሞች ከፍተኛዋ እንደሆነች በሚነገርላት በዚች ከተማ ውስጥ ከፍተኛ ጦርነት በመካሄድ ላይ ነው። የተመድ የሰብአዊ ጉዳዮችና የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ አስተባባሪ ቫለሪ አሞስ በሰጡት መግለጫ በአሌፖ ከተማና ዙሪያዋ በመንግሥቱ ጦር ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ጦርነት እየከፋ በመምጣቱ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ 200,000 ያህል ሕዝብ ወደጐረቤት አገሮች የተሰደደ መሆኑን ገልጸዋል።
የተመድ ረዳት ዋና ፀሐፊ ቫለሪ አሞስ እስካሁን ድረስ በአሌፖ ከተማ ውስጥ በመንግሥቱ ጦር ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል በሚካሄደው ውጊያ በአጣብቂኝ ውስጥ የገባውን ሕዝብ ቁጥር በትክክል ለማወቅ ባይቻልም ብዙ ሕዝብ የትምህርት ቤቶችና ተቋሞች ውስጥ ተጠልሎ እንደሚገኝና አስቸኳይ ነፍስ አድን ዕርዳታ እንደሚፈልግ ገልጸዋል። በአሁኑ ጊዜ ወደ አሌፖ፣ ሐማና ሌሎች በርካታ ከተሞች ሰብአዊ ዕርዳታ ለማድረስ ሁኔታው አስቸጋሪ እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
ቫለሪ አሞስ ይህን መግለጫ ከመስጠታቸው ቀደም ሲልም የተመድና የዓረብ ሊግ የሶሪያ ጉዳይ ልዩ መልዕክተኛ ኮፊ አናን የፕሬዚዳንት ባሻር አልአሳድ መንግሥት በአሌፖ ከተማ ዙሪያ የጦር ኃይልና ከባድ መሣሪያ የማከማቸቱ ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን መግለፃቸው ታውቋል። ሁኔታው በከተማዋ ውስጥ እልቂት ለመፈፀም የሚደረግ ዝግጅት እንደሆነም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማስታወቃቸው ተገልጿል።
በሌላ በኩል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን የኦሊምፒክ ውድድር ለዓለም ሰላም መጠበቅ የሚያበረክተውን ገንቢ ድርሻ መነሻ በማድረግ አገሮች ጦርነቶችን እንዲያቆሙ ጠይቀዋል። ዋና ፀሐፊ ባን-ኪ-ሙን ይህን ጥያቄ ያቀረቡት ለማኅበራዊ ለውጥ የኦሊምፒክ ስምምነትና ስፖርት (ኦሊምፒክ ትሩስ ኤንድ ስፖርት ፎር ሶሻል ቼንጅ) በሚል ርዕስ ለንደን ውስጥ ሰሞኑን በተካሄደ ፕሮግራም ላይ በተካፈሉበት ወቅት ነው። ይህ ፕሮግራም እ.አ.አ ከ1993 ጀምሮ እንደሚ ካሄድ ታውቋል። ዋና ፀሐፊው ጠንካራ ተዋጊዎችና ደጋፊዎቻቸው ዓላማቸውን ለማሳካት የሚያካሂ ዱትን ውጊያ ለማቆም አይችሉም ብሎ ማሰብ ትክክል እንዳልሆነ አመልክተው የዚህን የሰላማዊ ዓላማ መከተል አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆነ አመልክተ ዋል።
በማያያዝም በአሌፖ ከተማ እየተባባሰ የመጣው ሁከት አሳሳቢ እንደሆነ አመልክተው የሶሪያ መንግሥት ከተማዋን ከአሸባሪዎች ለማፅዳት በሚል ሽፋን የጀመረውን ዘመቻ እንዲያቆም ጠይቀዋል።
ዋና ፀሐፊ ባን ኪ-ሙን በለንደን አሊምፒክ መጀመር ዋዜማ በችቦ ቅብብሎሽ ፕሮግራም መሳተፋቸውም ተገልጿል።
| < Prev | Next > |
|---|


