ማዕከሉ የሀገሪቱን የዓሣ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋል እየሰራ ነው

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2004 (ዋኢማ) - የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የሀገሪቱን የዓሣ ሀብት ጥቅም ላይ ለማዋልና ሀብቱን ለመጠበቅ የሚያስችሉ የልማት ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

የኢንስቲትዩቱ የብሔራዊ ዓሣና የውሃ ውስጥ ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶክተር አዳምነህ ዳኜ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የምርምር ማዕከሉ በመናመን ላይ ያለውን የዓሣ ሀብት ለመጠበቅና በዘርፉ የሚገኘውን የገቢ ምንጭ ለማሳደግ የሚያስችሉ መርሐ ግብሮችን ቀርፆ እየተንቀሳቀሰ ነው።

እንደ እርሳቸው ገለፃ፤ በሀገሪቱ ያለው ባህላዊ የአጠማመድ ሥርዓትና ኋላቀር አያያዝ እንዲሁም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣው የዓሣ ፍላጐት ለዓሣ ሀብቱ መናመን ምክንያት ሆኗል።

በተለይም ዓሣው ከተጠመደ በኋላ ያለው የድህረ ምርት ብክነትና ለገበያ እስከሚቀርብበት ጊዜ ያለው ደካማ አያያዝ ሀገሪቱ በዓሣ ሀብቷ በሚገባ ተጠቃሚ እንዳትሆን ያደረጓት መሆኑን ገልጸዋል።

በዚህ ረገድ ማዕከሉ በተፈጥሮ ወንዞችና ሀይቆች ከሚገኘው የዓሣ ምርት በተጨማሪ በሰው ሠራሽ ኩሬዎች ተጠቅመው ከሌላው የግብርና ሥራ ጐን ለጐን እንዲያመርቱ ጥረት እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

በሀገሪቱ ካሉት 180 የዓሣ ዝርያዎች ውስጥ ከ120 የሚበልጡት በጋምቤላ ክልል ውስጥ በሚገኙ ወንዞች ውስጥ ያገኛሉ ያሉት ዶክተር አዳምነህ፤ ይሁን እንጂ በክልሉ ያለው ኋላቀር የዓሣ ማስገር ሥርዓት ሳቢያ የሚፈለገውን ያህል ተጠቃሚ መሆን አለመቻሉን አስረድተዋል።

በመሆኑም ማዕከሉ በበጀት ዓመቱ የዓሣ ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅ በነደፋቸው መርሐ ግብሮች አማካኝነት ለክልሉ በሁሉም ወረዳዎች ለአርሶ አደሮች ዘመናዊ የዓሣ አጠማመድና አያያዝ ሥርዓት ሥልጠና መስጠቱን አመል ክተዋል። በድህረ ምርት ወቅት የሚደርሰውን ውድመት ለመታደግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩልም ማዕከሉ በሰጠው ሥልጠናና ድጋፍ አማካይነት ከአራት ዓመታት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና በደቡብ ምዕራብ ሸዋ አካባቢ ለሚገኙ አርሶ አደሮች በሰው ሠራሽ ኩሬ ዓሣን በማርባት ተጠቃሚ እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል።
በበጀት ዓመቱ በወሊሶ፣ ቱሉ ቡሎና ኢጃጂ አካባቢ ለሚገኙ 75 አርሶ አደሮች ዘመናዊ የዓሣ አረባብ ዘዴ የተግባር ሥልጠና መስጠቱንና ሥልጠናውን ከወሰዱት ውስጥ 50 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸውን ተናግረዋል። በምርት ሂደት ውስጥም የማዕከሉ ድጋፍ እንደማ ይለያቸው አስንዝበዋል።

በተጨማሪም ማዕከሉ ለኃይል ማመንጫነት በሚሰሩ ግድቦች ውስጥ ዓሣን ማርባት እንዲቻልና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ ከሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ጋር አብሮ ለመሥራት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አስታውቀዋል።
በሀገሪቱ የሚገኙ ባለሀብቶችም ለዘርፉ ልማትና ለውሃ ብዝሀ ሕይወት ጥበቃው የራሳቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉ ዳይሬክተሩ ጠይቀዋል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 187 guests