ኢትዮጵያ መሪ ምርቶቿን መለየትና የዓለምን ፍላጎት ባማከለ መልኩ ማቅረብ እንደሚገባት ተገለፀ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 25/2004 (ዋኢማ) - ኢትዮጵያ በአለም አቀፍ የገበያ ብቁ ተወዳዳሪ እንድትሆን መሪ ምርቶቿን መለየትና የዓለምን ፍላጎት ባማከለ መልኩ ማቅረብ እንደሚገባት የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለፀ፡፡
በሀገሪቱ መሪ ምርቶች ላይ የሚመክር አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ፣ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤትና በጃፓን አለም አቀፍ የልማት ትብብር /ጃይካ/ አማካኝነት የተዘጋጀው አውደ ጥናት ኢትዮጵያ መሪ ምርቶቿን በምታሳድግበትና በአለም ገበያ በምታስተዋውቅበት መንገድ ላይ መክሯል፡፡
የመሪ ምርቶቹ መለየትም የሀገሪቱን ገፅታ በመገንባት፣ የወጪና ንግድ መጠኑን በማሳደግና በአለም አቀፍ ገበያዎች ውስጥ ተወዳዳሪ ለማድረግ አይነተኛ መሳሪያ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዲኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ የመሪ ምርቶች ወጪ ንግድ የሀገር ውስጥ ምርትና ባለሃብቶችን በመበረታታት በኩል ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ገልጸዋል፡፡ የሀገሪቱ የወጪ ንግድም ከግዜ ወደ ግዜ እያደገ መምጣቱን በመጠቆም፡፡
ኢትዮጵያ በተለይ በጨርቃጨርቅ ፣ በምግብ እህሎችና በቅጠላቅጠል ያላት ልዩ የተፈጥሮ ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ አለም አቀፉን ገበያ በቀላሉ እንደሚቀላቀል በጃፓን አለም አቀፍ የልማት ትብብር የአለም አቀፍ ንግድና ኢንቨስትመንት ተቋም ዋና ዳይሬክተር ሳቡሮ ዩዛዋ ገልጸዋል፡፡
ተቋማቸውም ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ መሪ ምርቶች ላይ ጥናት በማካሄድና እሴት በመጨመር ወደ ጃፓን ገበያ በመላክ ሂደት ውስጥ ድርሻ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ በአለም ላይ የማይገኘ እንደ ጌሾ፣ ጠጅ፣ ጤፍ እና ጠላ የመሳሰሉ ልዩ ምርቶቿን በተለያዩ አለም አቀፍ መገናኛ ብዙሃን እንዲሁም በአውደ ርዕዮች ላይ ማስተዋወቅና ከምርቶቿ ተገቢውን ጥቅም ማግኘት እንደሚገባትም ሚስተር ሳቡሮ ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ የወጪ እና ገቢ ንግድ መካከል ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንደ ጃፓን ያሉ ሀገራትን ልምድ በመውሰድ መሪ ምርቶችን ማሳደግ እንደሚገባም ነው በውይይቱ የተገለጸው፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


