የሰውን ተፈጥሮአዊ ክስተት በማራገብ ፖሊሲን የመተቸት ዘመቻ

  • PDF

ዘአማን በላይ
This e-mail address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it

ከመሰንበቻው የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊን ¬ጤንነት አስመልክቶ ያልተባለ፤ ያልተነገረ፤ በስሚ ስሚ ከዳር እስከ ዳር ያልተቀባበለ ተጨባጭ የሆነና ያልሆነ የወሬ ዓይነት አልነበረም ብል ማጋነን የሚሆንብኝ አይመስለኝም፡፡ አብዛኛው ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጤንነት ሁኔታ ከራሱ የደህንነት ዋስትና እንዲሁም ስለ እርሳቸው ጤንነት ከማሰብ ብሎም የሀገሩን መፃዒ የእድገት ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ተጨንቋል፤ ተጠብቧል፡፡

“ፎርቹን’’ የተሰኘው ሀገር በቀል የእንግሊዝኛ ጋዜጣ ሰሞኑን እንደገለፀው፤ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጤንነት አስመልክቶ በርካታ ግለሰቦች ባደረጉት የጎግል ፍለጋ 5 ሺህ በመቶ ሊሆን ችሏል፡፡ ይህ ዕውነታ የሚያመላክተው ሁለት ነገሮችን ነው፡፡ አንደኛው ¬ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር ወዳድ በሆነው ህዝብ ልብ ውስጥ ምን ያህል ቦታ ያላቸው መሆኑን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ መንግስት እጅግ የተፋጠነ መረጃ አለመስጠቱን ነው፡፡

ምንም እንኳን ሁኔታውን አስመልክቶ በመንግስት በኩል የተሰጠው መግለጫ ፈጣን ባይሆንም፤ እጅግ የዘገየ ነው የሚባል ግን አይደለም። ምክንያቱም አቶ መለስ ከህመማቸው ማገገማቸውና በሃኪም ትዕዛዝ እረፍት ላይ መሆናቸው ከተገለፀ በኋላ፤ አብዛኛው ህዝብ ውስጥ መረጋጋት በመፈጠሩ ነው፤፤ ይህን ተከትሎም ቀና አስተሳሰብ ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህመማቸው ያገግሙና ይፈወሱ ዘንድ ፆም ፀሎት ላይ መሆናቸው ከማናችንም የተሰወረ አይደለም— ከጥቂት “የፖለቲካ ነጋዴዎች” በስተቀር ሁላችንም ተግባሩን እየከወንነው ነውና።
እርግጥ በሀገራችን ባህል የታመመን ሰው “እግዚሐብሔር ይማርህ” ማለት የተለመደ ብቻ ሳይሆን፤ ህዝባችን ለዘመናት ሲከተለው የኖረው እሴቱም ጭምር ነው። ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመታመማቸው ምክንያት፤ የእርሳቸውን ቅን ሀገራዊ አሳቢነት፣በበሳል አመራራቸው በሀገራችን እንዲመዘገብ ያደረጉትን ከፍተኛ ምጣኔ ሐብታዊ ዕድገት እንዲሁም ዘወትር ግጭት በማይለየው የምስራቅ አፍሪካ ከባቢ ሀገራችን ሰላማዊና የተረጋጋች እንድትሆን ማስቻላቸውን በመጥቀስ አብዛኛው ዜጋ ከሐዘኔታ ጋር “ጠንካራ መሪያችን ናቸው” ሲል ይደመጣል። በአንፃሩ ደግሞ የአቶ መለስን መታመም ተከትሎ ሁኔታውን የከሰረ ፖለቲካቸው ማገገሚያ ለማድረግ የሚሹ፣ የኢትዩጵያዊ ጨዋነትና ባህል የጎደላቸው የተቃውሞው ጎራ ጥርቅም ውስጥ ያደፈጡት የኪሳራ አወራራጅ ፖለቲከኞች እና የጡት አባታቸው “ሂዩማን ራይትስ ዎች’’ ያገጠጠና ያፈጠጠ አሳፋሪ መግለጫ ሲሰጡ ተመልክተናል።
ለወትሮው ሂዩማን ራይትስ ዎች በኢትዩጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገባ ሲያስነጥሰው እንትፍታውን ለማበስ በምስክርነት ጭምር መሃረብ ይዘው የሚሯሯጡት የመድርክ አመራሮች፤ ከኢትዩጵያዊ ስነ-ምግባር ባፈነገጠ መልኩ ከጡት አባታቸው ቀድመው የሻገተ ፖለቲካቸውን ለማቀንቀን ጊዜ አልወሰደባቸውም። እንቶ ፈንቶ ብጭቅጫቂ ወረቀቶችን በቦርሳቸው አጭቀው ከሀገር ሀገር ይዞራሉ የሚባሉትና ሰሞኑን የመድረክ ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ የፖለቲካ እምነታቸው አምሳያ ለሆነው “እሳት” ቴሌቪዠን (ይቅርታ “ኢሳት” ለማለት ነው) እንደተናገሩት፤አቶ መለስ ስለታመሙ ገዥው ፓርቲ የፖሊሲ ማስተካከያ ማድረግ አለበት ብለዋል።
ውድ አንባቢዎቼ እንግዲህ የኛ ሀገር የተቃውሞ ፖለቲካ ይኸው መሆኑ ነው—አንድ ሰው በተፈጥሮአዊ ክስተት ሳቢያ ሲታመም ድርጅቱ ፖሊሲውን እንዲቀይር መጠየቅ።…መቼም “ወደው አይስቁ” እንጂ ከቶ ምን ይባላል?!... እርግጥ በኢህአዴግ ውስጥ ያሉ ግለሰቦች “ሰዎች” መልዓክት አለመሆናቸውን ለዶክተሩ ማስረዳት ተገቢ ነው ብዬ ባምንም፤ የእርሳቨው ነገር ግን “ድንጋይ ሰባ ዓመት ውሃ ውስጥ ቢቀመጥ ዋና አይማርም” እንዲሉት ስለሆነብኝ ሃቁን መግለፅ ግድ ይለኛል።
በኢህአዴግም ይሁን በመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉት ሰዎች እንደ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ይደሰታሉ፣ይከፋሉ፣ይታመማሉ፣ይድናሉ። አቶ መለስም ሰው ናቸውና እነዚህን የሰብዓዊ ፍጡር ነባራዊ ክስተቶችን ይጋራሉ። ይሁን እንጂ እርሳቸው እንደማንኛውም ሰው ሲታመሙ የሚመሩት ድርጅት ፖሊሲውን እንዲቀይር የሚጠየቅበት ሁኔታ በየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ ፍለስፍና (political philosophy) መስማቴንም ሆነ ማንበቤን አላስታውስም። ከመድረክ አመራሮች አቋም የለሽ “አቋም” የፖለቲካ መቆመሪያ ዲስኩር በስተቀር።
እርግጥ ሀገራዊ ጥቅሞቻችንን ከማረጋገጥ አኳያ ያላቸውን ዕውቀት፣ክህሎትና ችሎታ በመጠቀም ግንባር ቀደም የመሪነት ሚና መጫወታቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። በውጭ ግንኙነታችን በኩልም ሀገራቸውንና አፍሪካን በመወከል በቡድን ሰባት፣ ስምንትና ሃያ ጉባዔዎች ባደረጉት እንቅስቃሴ እንዲሁም በአየር ንብረት ለውጥ ላይ አፍሪካዊ ተሟጋች ሆነው መስራታቸው የጠቅላይ ሚኒስትራችንን እምቅ አቅም የሚያረጋግጥ ነው።
ይሁን እንጂ የእርሳቸው ተግባራቶች የድርጅታቸው ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች መገለጫዎች መሆናቸው መዘንጋት አይኖርበትም። ኢህአዴግ ከትጥቅ ትግሉ ወቅት ጀምሮ በዓላመ እንጂ በግለሰቦች ላይ የተመረኮዘ ህልውና የለውም፤ ኖሮትም አያውቀም። ድርጅቱ በራሱ ፖሊሲ የሚመራ ነው። እናም በድርጅቱ ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም አባል የኢህአዴግን ፖሊሲ በፅናት ያስፈፅማል እንጂ፣ የእኔ የሚለው ግለሰባዊ የፖለቲካ አውድ ሊኖረው አይችልም።
ገዥው ፓርቲ በኢትዩጵያ ህዝቦች ፈቃድ እንደ መንግስት የመሰረተው ስርዓት (system) በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባ ነው። ግለሰቦች ቢኖሩም፣ ባይኖሩም የተገነባው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ይቀጥላል። ከኢህአዴግ የ38 ዓመት የትግል ታሪክ የምንገነዘበው ግለሰቦች በዴሞክራሲያዊና በፀረ-ዴሞክራሲያዊ እሳቤዎቻቸው ድርጅቱን ሲለቁና ሲሰናበቱ የቆዩ ቢሆንም፤ ድርጅቱ ግን ከታገለላቸው ዓላማዎቹ ጋር ዛሬም ድረስ ዘልቋል። ወደፊትም እንዲሁ። እናም ግለሰቦች ቢሄዱና ቢመጡ የተገነባው ስርዓት መቀጠሉ አይቀሬ ነው።
ከዚህ በመነሳት “የነጋሶ መንገድ” በሚለው መፅሐፋቸው ላይ ከኦነግ እስከ ሚጢጢዬው የአመፃ እና ቧልተኞች ቡድን (አንድነት ፓርቲ) ድረስ በመዝለቅ ዛሬም ማንነታቸውን ባለመቀየራቸው የማውቃቸው ዶክተር ነጋሶ ያነሱትና ሰው ሲታመም “ፖሊሲያችሁን ቀይሩልን” የሚል የአላዋቂ ሳሚ ጥያቄ ረብ የለሽ መሆኑን ለመረዳት አይከብድም። መሪው ሲታመም ፖሊሲውን የሚቀይር፣ ሲሻለው ደግሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ የሚመለስ ድርጅት ታይቶም ሆነ ተሰምቶ አይታወቅምና።…እናንተዬ ነገሩ እንዴት ነው?...እኔ የምለው ዶክተር ነጋሶ እግራቸውን ሲታመሙ፤ አንድነት ፓርቲ በሌሎች ወገኖች አጀንዳ እየተንጠላጠለ የሚጎስመውን “ሞቴን ከሁከት ጋር ያድርገው” የአመፃ ጥሪ ፖሊሲውን ቀይሮት ይሆን እንዴ?!...እኔ ግን እርሳቸውን አይደለሁምና በሚዲያዎች ላይ እንደተገለፀው እርግጥም ዶክተሩ እግራቸውን አሟቸው ከሆነ፤ “ምህረቱን ይስጣቸው” ብያለሁ — ዘመን በማይሽረው ኢትዩጵያዊ ጨዋነት።
የማይተማመኑ ባልንጀሮች ስብስብ የሆነውና “መድረክ” የተሰኘውና በቅርቡ ራሱን “ግንባር ስለሆንኩ እወቁልኝ” በማለት ያወጀው ድርጅት (ምንም እንኳን የጉልቻ መለዋወጥ ወጥ ባያጣፍጥም) ተጣማሪ አባል የሆነው የአንድነት ፓርቲ አመራሮች የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጤንነት ሁኔታ ተመርኩዘው ከዶክተር ነጋሶ ያልተናነሰ መግለጫ ሰጥተዋል—“የዘሬን ብተው ያንዘርዝረኝ” እንዲል የሀገራእን አርሶ አደር። ታዲያ ጉዳዩ ለውድ አንባቢዎቼ ግልፅ ይሆን ዘንድ ከሰሞኑ ለአዲስ አድማስ ጋዜጣ የሰጡትን አስተያየት የሚመስል የፖለቲካ ጨዋታቸውን እንካችሁ ልበል።
የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ እና የሰው በላው የደርግ ስርዓት የሸንጎ አባል የነበሩት ዶክተር ኃይሉ አርአያ የአቶ መለስን ህመም አስመልክተው “አንድ ሰው ሁሉንም መሆን አይችልም” ሲሉ፤ ዋና ፀሐፊውና ፓርላማ ውስጥ ከፓርቲያቸው የተሰጣቸውን ፅሑፍ እንደ መፅሐፍ ቅዱስ ቃል ሳይጨምሩና ሳይቀንሱ አጎንብሰው የሚያንበለብሉት የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ ደግሞ “እስካሁን አለመታመማቸው ትንግርት ነው” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን ‘ቀደም ሲል ሊያማቸው ይገባ ነበር’ የሚል አንድምታ ያለውና ከባህላችን ያፈነገጠ አባባል ጭካኔ በተሞላበት መንገድ ተመኝተውላቸዋል። የመድረክ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲም በበኩላቸው “ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ህመም ዋነኛ ችግር ሁሉንም ነገር ጠቅልለው በመያዝ በራሳቸው ላይ ጫና በማሳደር ራሳቸውን ለመታመም ማዘጋጀታቸው ነው” ብለዋል።
መቼም ማንም ነፁህ ህሊና ያለው ኢትዩጵያዊ የመድረክ አመራሮች መግለጫ ሊያሳዝነውና ሊያስቆጨው እንደሚችል አልጠራጠርም። ምክንያቱም መግለጫቸው እንደ ዜጋ ከኢትዩጵያዊ ጨዋነት ባፈነገጠ መልኩ ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ብቻ በሚያሳፍር ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩን “አስቀድመው መታመም ይገባቸው ነበር” እስከሚል መብሰልሰልና የታፈነ ቁጭት ድረስ የሚዘልቅ በመሆኑ ነው።
ምንም እንኳን የእነዚህ ወገኖች አስተያየት ምህረት የለሽና ለፖለቲካ ጨዋታ ቁማራቸው ሲሉ ምኞታቸው እስከ የት ድረስ እንደሚዘልቅ ቢያመላክትም፤ አባባላቸውን ኢትዩጵያዊ ፈሩን ባልሳተ መልኩ እንዲህ ጠቅለል አድርገን መመልከት እንችላለን። ይህም አንድም የመዘዙት የተሳሳተ ካርድ የማንነታቸው መገለጫ መሆኑን፣ ሁለትም የጤና ፖለቲካ ቁማር የትም የማያደርስ መሆኑን በግልፅ ያስረዳናል።
እስቲ በቅድሚያ ኢንጂነር ዘለቀ ረዲንና የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉን አስተያየቶች እነርሱው እንደሚሉት “በአንድ ግንባር” አጣምረን እንመልከት። የግለሰቦቹ አስተያየቶች በግርድፉ ሲታዩ የሚያመላክቱት ጉዳይ ቢኖር እንደተለመደው ያለ ህዝብ ይሁንታ በአቋራጭ ስልጣን አካፍሉን ጥያቄ ነው። “አንድ ሰው የሚታመመው ብዙ ስልጣን ስላለው ነው። ስለዚህ ግለሰቡ እንዳይታመም ስልጣን መከፋፈል አለበት” የሚል ምክንያታዊ ያልሆነ አመክንዩን ያነገበው የአመራሮቹ “በልጅ አመካኝቶ ይበሏል አንጉቶ” ፍላጎት ግን ውሃ የሚቋጥር አይደለም።
በአንድ ወቅት በሚዲያ ላይ ስማቸው በነጋዴነት የተወሳው የተከበሩ አቶ ግርማ ሰይፉ፤እንደ መርካቶና አካባቢው ንግድ ፖለቲካን ለመሸቀጥ ፈልገው ከሆነ፣ የሁለቱ አብሮነት “ማሞ ሌላ፣ መታወቂያው ሌላ” እንዲሉት ዓይነት መሆኑን መገንዘብ ያለባቸው ይመስለኛል። ለምን ቢሉ፤ የንግድ ስራ በአንድ በማይታወቅ ግለሰብ ዋጋ ላይ ተንተርሶ የጨረታ ዋጋ ማቅረብን የሚያጠቃልል ሲሆን፣ ፖለቲካ ግን የታወቀ ፖሊሲንና ስትራቴጂን ተመርኩዞ ዜጎችን በማሳመን በህዝብ ዘንድ ተመራጭ መሆንን የሚጠይቅ ተግባር ነው።
ዳሩ ግን አቶ ግርማ “የእንቁጣጣሽ ቀን ያበደ፣ ዘፈኑ ሁሉ አበባ ይሆሽ ነው” እንዲሉ፤ ራሳቸውም ሆኑ ፓርቲያቸው አጀንዳ ሳይኖራቸው ‘የሚባል ነገር አገኘን’ በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩን “አስቀድመው መታመም ነበረባቸው” በሚል ቃና በሰው ልጅ የተፈጥሮ ክስተት ያልተገባ ወግ መጠረቃቸው ከማስተዛዘብ ውጭ የሚያስገኝለቸው ነገር ያለ አይመስለኝም። እናም ጥያቄያቸው በተዘዋዋሪ መንገድ ‘ስልጣን ስጡን’ የሚል ከሆነ፣ በተገኘ አጀንዳ ላይ ሁሉ እየተንጠላጠሉ ማንነትን የሚያሳብቅና ኢትዩጵያዊ ወዝ የሌለው ዲስኩርነ ከማነብነብ፤ የራስን አጀንዳ ቀርፆ ህዝቡን በማሳመን ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ መዘጋጀት በጄ ነው — ምናልባትም ፓርቲያቸው አመፅን ከመጎንጎን ውጭ የሚጨበጥና የሚዳሰስ ፖሊሲ ካለው ማለቴ ነው።
የዚህን ፅሑፍ አቅራቢ እጅግ ያስገረመው ሌላው ጉዳይ፤ የአንድነት ፓርቲ ህዝብ ግንኙነት ሃላፊ ዶክተር ኃይሉ አርአያ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የጤና መታወክ አስመልክተው “አንድ ሰው ሁሉንም መሆን አይችልም” የሚለውና ከማንነታቸው ጋር የሚጣረስ አባባል ነው። ዶክተሩ ከዛሬ 21 ዓመት በፊት በደርግ ሸንጎ ውስጥ ከነ ሰማያዊ ካኪያቸው በአባልነት ተሰድረው በነበረበት ወቅት ግራ እጃቸውን ወደ ላይ በማንሳት “አንድ ሰውና አንድ ጥይት እስኪቀር ድረስ እንዋጋለን” የሚል መፈክር ሲያሰሙ የነበሩ የኢሠፓ ባለሟል ናቸው።
እርሳቸው ለአንድ አምባገነን መሪያቸው ህልውና መቀጠል ዋስ ጠበቃ እንዳልሆኑ (የማታ ማታ ማጣፊያው ሲያጥርባቸው የተቀየሩ ቢመስሉም)፣ የመንግስቱ ኃይለማርያም የጡት ልጅ እንዳልነበሩ፣ ዛሬ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ተደራጅተው “እሰየው” ማለት ሲገባቸው በሌለ ዕውነታ የዴሞክራሲያዊ አሰራሩን ለማጠልሸት መቋመጣቸው በእኔ እምነት ራስን ያለማወቅ አባዜ ነው። ለነገሩ እኚህ ግለሰብ ስለ አንድ ሰው አሰራር የመናገር የሞራል ብቃት የላቸውም—ለአንድ ሰው ስልጣን ሲሉ ዕድሜያቸውን ገፍተው ዛሬ ላይ የደረሱ የኢ-ዴሞራሲያዊነት አራማጅ ናቸውና።
እርግጥ እነ ዶክተር አርአያ ሲያጨበጭቡለት የነበረው ሰው በላው ስርዓት በኢትዩጵያ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ግፍ ያንገሸገኸው ክንድ ተገርስሶ ዕውን የሆነው የኢፌዴሪ ህገ-መንግስት፤ ለፌዴራልና ለክልል መንግስታት በሰጠው የስልጣን ወሰን መሰረት ማንኛውም የመንግስት ባለስልጣን ኃላፊነቱን ሲወጣ ቆይቷል፤ በመወጣት ላይም ይገኛል። ጠቅላይ ሚኒስትሩም እንደ አንድ የመንግስት ተቀጣሪ ባለስልጣን በተሰጣቸው ሃላፊነት እርሳቸውን የሚመለከተውን ብቻ ህገ-መንግስቱ አኳያ ያለ አንዳች እረፍት የአፍሪካን እና የታላላቅ ሀገራት መሪዎችን በሚያስደምም ብቃት የተወጡ ብርቅዬ የኢትዩጵያ ልጅ ናቸው።
ይሁን እንጂ የደርጉ ቧለሟልና ግብረ-አበሮቻቸው “አንድ ሰው ሁሉንም ሊሆን አይችልም፣…ጫና በማሳደር ራሳቸውን ለማሳመም መዘጋጀታቸው ነው” የሚለው አባባላቸው፤ ‘አቶ መለስ በሀገር ውስጥ፣ በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለምን ተሰሚነት አገኙ?’ የሚል የተለመደው ሁሉንም ነገር በቅናት የመቃወም አባዜ ከሆነ፤ እነዚህ ወገኖች ከዕውነታው ጋር መታረቅ ያለባቸው ይመስለኛል።
ይኸውም ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሀገራችን የአፍሪካን ጥቅሞች ለማስከበር መንቀሳቀሳቸውና በዚህም ሳቢያ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት የማግኘት ምስጢር፤በሀገር ውስጥ አቶ መለስና መንግስታቸው የኢትዩጵያን ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገት በማረጋገጣቸው እንዲሁም ጦርነት ቋያ በማያጣው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ሀገራችንን ሰላማዊ፣ የተረጋጋችና ዴሞክራሲያዊ እንድትሆን ከፍተኛ ጥረት አድርገው ስለተሳካላችው ነው። ከዚህ ባሻገርም ከሀገራት ጋር በሰላም፣ በእኩል ተጠቃሚነትና በመከባበር ላይ የተመሰረተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ቀርፀው ገቢራዊ ማድረጋቸው ለተደማጭነታችን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱ ተግባራት ናቸው። እንግዲህ ሃቁ ይኸው ነው— የሰውን ተፈጥሮአዊ ክስተት በማራገብ ፖሊሲን ለመተቸት በዘመቻ መልክ የተሰማሩት የመድረክና ግልገል ፓርቲዎቹ አመራሮች ያሻቸውን ቢደሰኩሩም።
መቼም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ የኢትዩጵያን መንግስት ውጤታማ ፖሊሲዎችን በሰበብ አስባቡ የሚተቹ ድርጅቶችን ሲሰማ፤ አንድ የተለመደ ድምፅ ወደ አዕምሮ ጓዳው ማቃጨሉ አይቀርም—ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚል። እርግጥ ይህ በሰብዓዊ መብት ስም ለይስሙላ የሚንቀሳቀሰው ድርጅትና የመድረክ አመራሮች የኢትዩጵያን ህዝብና መንግስት የውስጥና የውጭ ጠላቶች ሆነው በዘመቻ መልክ መንቀሳቀስ የጀመሩት ዛሬ አይደለም። ቢያንስ የሰባትና ስምንተ ዓመታት ቁርኝትን ያስቆጠሩ ናቸውና።
የአቶ መለስ ተፈጥሮአዊ ህመም የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ነኝ ከሚል ድርጅት ጋር ሊኖረው የሚችለው ቀጥተኛ ቁርኝት ለእኔ ግልፅ ባይሆንልኝም፤ ተቋሙ የሀገር ውስጥ “ክንፉ” ሲንጫጫ ሰጨአጋር መሆኑን ለመግለፅ በአፍሪካ ጉዳዩች ከፍተኛ ተመራማሪው ቤን ራውለንሰ አማካኝነት ከኢትዩጵያ ህዝብና መንግስት ጋር ያለውን ፖለቲካዊ ልዩነት ባልተለመደ ሁኔታ በይፋ ግልፅ አድርጓል። በግለሰቡ ስም የወጣው ፅሑፍ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የቻይና መንግስትን እንደ ሞዴል በመመልከት የኢኮኖሚ ዕድገትን በማስቀደም ሰብዓዊ መብትን ወደ ጎን ብለዋል ባይ ነው።
ማንም የዚህ ፅሑፍ አንባቢ እንደሚገነዘበው ይህ የሂዩማን ራይትስ ዎች መሰረተ-ቢስ ክስ የተሰለቸና የቸከ ነው። ዓላማውም ፖለቲካዊ እንጂ ከሰብዓዊ መብት ጋር የሚገናኝ አይደለም። በዊኪሊክስ መረጃ ጭምር እንቅስቃሴው ፖለቲካዊ ግብ ያለው እንጂ ከሰብዓዊ መብት ጋር የተገናኘ እንዳልሆነ በአደባባይ የተጋለጠው ይህ ተቋም፤ በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት የሶቭየት ህብረትን ካምፕን ለማዳከም “ሄልሲንኪ ዎች” በሚል ስያሜ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ “የእኛን የፖለቲካ- ኢኮኖሚ ዘይቤን ተከተሉ” የሚል አክራሪ ድርጅት መሆኑ ይታወቃል።
ዛሬም ልክ እንደ ሀገር ውስጥ ደቀ-መዝሙሮቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩን መታመም አስታክኮ የኢትዩጵያን መንግስት ፖሊሲ በመተቸት ተግባር ላይ መሰማራቱም የዚህ ማንነቱ ሁነኛ ማሳያ ነው። በመሰረቱ አንድ የውጭ አክራሪ ኒዩ-ሊበራል ተቋም ኢትዩጵያ የትኛውን ዓይነት ፖሊሲና የትኛውን ሀገር በሞዴልነት መከተል እንዳለባት ሊወስን አይችልም — ምርጫው ሉዓላዊ የስልጣን ባለቤት የሆነው የሀገራችን ህዝብ እና እርሱን ወክሎ እንዲሰራ የመረጠው መንግስት ነውና። ከዚህ ውጭ በሌለ ነባራዊ ሁኔታ “እኛን እንደ ሞዴልነት ተጠቀሙ፣ አሊያ ግን ሰብዓዊ መብት የሚባል ሰነድ እየመዘዝኩ የሪፖርት ናዳን እንደ በረዶ አዘንብባችኋለሁ” ማለት በየትኛውም መስፈርት ተቀባይነት የሌለው ተግባር ነው።
ለነገሩ አክራሪው ተቋም “እኛን ብቻ ተከተሉ” የነዩ-ሊበራሊዝም ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ እሳቤ የተከታዩቹን ሀገራት ምጣኔ ሃብት ለቀውስ በመዳረግ አብዛኛውን ዜጎቻቸውን ስራ አጥ ያደረገ፣ 99 በመቶ በሚሆን ህዝባቸው በደባባይ የተወገዘ ስርዓት ነው። እናም እኔ እስከሚገባኝ ድረስ፤ ኢትዩጵያ ራሱን በራሱ የጣለን ስርዓት በመከተል የውድቀት ማወራረጃ ሆና እንደ ጧፍ መንደድ የለባትም። የምትከተለው ልማታዊ ዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ፤ በየዓመቱ የሀገሪቱን ምጣኔ ሃብት በሁለት አሃዝ ያሳደገና የህዝቦቿን ተጠቃሚነት በየደረጃው ከፍ ያደረገ ነው። እሳቤው ከውጭ እንደ ቁሳቁስ ተገዝቶ የገባ ፖለቲካዊ-ኢኮኖሚ ሳይሆን፣ ከተጨባጭ ሁኔታዋ ጋር አብሮ የሚሄድና ሁለንተናዊ የዕድገት አቅጣጫዎችን የሚከተል ትክክለኛ ሞዴል ነው።
እናም ሀገራችን ትናንት የምትታወቅበትን የድህነት አረንቋን ታሪክ እየቀነሰላት ያለውንና በቀጣይም መካከለኛ ገቢ ወዳላቸው ሀገራት ውስጥ እንድትቀላቀል ግብ የሰነቀውን ውጤታማ ፖሊሲ ለእነ ሂማን ራይትስ ዎች የቁራ ጩኸት ስትል የምትተውበት አንዳችም ምክንያት የለም። ሂማን ራይትስ ዎች ዋነኛ ግቡ ሰብዓዊ መብትን ማስከበር ሳይሆን፤ በራሱ ፖለቲካዊ ርዕዩተ-ዓለም (ideology) ጠፍጥፎ የሰራው አሻንጉሊት መንግስት መመስረት ነው። መድረክ ደግሞ “የበሬ ምንትስ ይወድቃል ብላ ስትከተል ዋለች” እንደተባለችው እንስሳ በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በአቋራጭ ዙፋን ላይ ለመውጣት የሚያልም የድርጅቱ ተስፈኛ ነው።
ዳሩ ግን ምንም እንኳን መድረክና የውጭ ተጣማሪው ሂዩማን ራይትስ ዎች የአቶ መለስን የህመም ተፈጥሮአዊ ክስተት በማራገብ አሁንም ፖለቲካ ፍላጎታቸውን በእግረ መንገዱ ለማሳካት የመንግስትን ፖሊሲ የመተቸት ስራ በዘመቻ መልክ ለማከናወን ቢንቀሳቀሱም፤ አህአዴግ ሰው በታመመበት ቁጥር ማንነቱን የሚቀይር አለመሆኑን መረዳት ያለባቸው ይመስለኛል። ኢትዩጵያ ውስጥ ህገ-መንግስታዊ ዋስትና የተሰጠውን ብሎም በተግባር ተፈፃሚ በመሆን ላይ የሚገኘውን የሰብዓዊ መብት ጥበቃን እንደ አጀንዳ በመያዝ ያልተፃፈ ድርሳንን ማነብነብ አዲስ አበቤዎች እንደሚሉት ሁሉም ያወቀውና “የተበላ ዕቁብ” ነው። እናም አንድ ሰው ሲታመም “ጭር ሰል አልወድም” በሚል ስሌት ‘ፖሊሲችሁን ቀይሩ’ እያሉ ማላዘን ‘አሉ’ ለመባል ካልሆነ በስተቀር የሚያተርፈው ነገር ቢኖር ትዝብትን ብቻ ነው።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 395 guests