ደም የመሰብሰብና የማሠራጨት ሥራ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተዛውሯል
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ደም የማሰሳሰቡን ሥራ ከቀይ መስቀል ማህበር ተረክቦ በአዲስ አበባና በክልል ጤና ቢሮዎች አማካይነት ለተጠቃሚዎች ለማሠራጨት መዘጋጀቱን አስታወቀ።
የዓለም ደም ለጋሾች ቀን « እያንዳንዱ ደም ለጋሽ ጀግና ነው» በሚል መርህ ለዘጠነኛ ጊዜ ትናንት ሲከበር በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የሜዲካል አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር አብርሃም እንዳሻው እንደገለጹት፤ የህሙማንን ሞትና ህመም ለመቀነስ የደም አገልግሎት ወሳኝ ነው።
ሆኖም በቀይ መስቀል የሚቀርበው ደም ከፈላጊዎች አንጻር በጣም አነስተኛ ነው። በመላ ሀገሪቱ ከፈቃደኛ ደም ለጋሾች ደም ለመሰብሰብና ለማሠራጨት ውስንነት ስላለ አገልግሎቱ ወደ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ተዛውሯል። የቀይ መስቀል ማህበር ለረጅም ዘመን የካበተውን ልምድ በማካፈል በትብብር ለመሥራት መግባባት ላይ ተደርሷል።
በቀጣይ ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን በቂ ደም ለማቅረብ በየመቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የደም ባንኮች ይቋቋማሉ። አስፈላጊውን መሣሪያና የሰው ኃይል በማሟላት፣ የሚታየውንም የደም ችግር ሙሉ በሙሉ ለመቅረፍ መታሰቡን ዶክተር አብርሃም ተናግረዋል።
በጐ ፈቃደኞችን ለማበራከት በክፍለ ከተማና በትምህርት ቤቶች የቀይ መስቀል ክበባትና የበጐ ፍቃድ አገልግሎት ግብረ ኃይላትን እንዲሁም የክለብ 2025 እና ሌሎች ማህበራት ይቋቋማሉ ብለዋል።
የሰውን ልጅ ህይወት ለማዳን ምንም ዓይነት ክፍያ ሳያስፈልጋቸው በፈቃደኝነት ደማቸውን ለለገሱ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ለዚህ ሰብዓዊ ተግባር ሌሎች ጓደኞቻቸውንና ዘመዶቻቸውን ይዘው በመምጣት ሰብዓዊ ሥራቸው እንዲቀጥል ጥሪያቸውን አስተላል ፈዋል።
የብሔራዊ ደም ባንክ ዳይሬክተር ዶክተር ግርማ ተስፋዬ የዘንድሮው የዓለም የበጐ ፈቃድ ደም ለጋሾች ቀን ዓላማዎች የበጐ ፈቃድ ደም ለጋሾች ለማመስገን፣ ደም መለገስ እየቻሉ እስከ አሁን ያልለገሱትን በበጐ ፈቃድ እንዲለግሱ ለማበረታታት ፣ የበጐ ፈቃድ ደም ለጋሾች እውቅና እንዲሰጣቸውና የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ሌሎች መስሪያ ቤቶች መቶ በመቶ ከበጐ ፈቃድ ደም ለጋሾች ብቻ ደም የመሰብሰብን ዓላማ እንዲያራምዱ ለማሳሰብ ነው።
በአገራችን ዘመናዊ ህክምና እያደገ መንግሥት የእናቶችንና የሕፃናትን ሞት ለመቀነስ እየተገበረው ባለው የጤና ስልት የደምና ደም ተዋጽኦ አቅርቦት አንዱ ነው። እስከ አሁን የተሰበሰበው ደም አነስተኛ በመሆኑ ደም ከፍላጐት ጋር የሚጣጣም እንዲሆን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ዶክተር ፖል ማንዮካ በበኩላቸው በታዳጊ አገሮች የደም አቅርቦትና ፍላጎት ባለመመጣጠናቸው በደም ችግር ምክንያት ብዙ ሰዎች ይሞታሉ ብለዋል።
በኢትዮጵያ ያለው ሁኔታም ከስድሳ ሦስት በመቶ በላይ የሚሆነው ደም የሚሰበሰበው ከአዲስ አበባ ሲሆን፤ ሰማኒያ አራት በመቶ የሚሆነው ደም የሚሰበሰበው ከቤተሰብና ከዘመድ መሆኑን ጠቁመዋል። ይህም በሀገሪቱ ያለውን የደም አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ብዙ መሥራት እንደሚገባ ያመለክታል።
ደም የሚለግሱ ሰዎችም መለገሳቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ማበረታቻና ምስጋና ማቅረብ አስፈላጊ ነው ያሉት ዶክተር ማንዮካ የዓለም ጤና ድርጅት በኢትዮጵያ የደም አቅርቦት እንዲሻሻል ድጋፍ እንደሚያደረግ ተናግረዋል።
| < Prev | Next > |
|---|


