የመንግሥታቱ ድርጅት የሶማሊያና ኤርትራ ተቆጣጣሪ ቡድን ኃላፊነት ተራዘመ

  • PDF

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 21/2004 (ዋኢማ) - የፀጥታው ምክር ቤት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በሶማሊያና ኤርትራ ላይ የጣለውን የጦር መሣሪያና ወታደራዊ መሣሪያዎች እገዳን ለማስፈፀም የቁጥጥር ሥራ ለሚያካሂደው የባለሙያዎች ቡድን የሰጠውን ኃላፊነት በአንድ ዓመት እንዲራዘም ውሳኔ አሳለፈ።

ምክር ቤቱ ከትናንት በስቲያ ይፋ እንዳደረገው የተቆጣጣሪ ቡድኑን ኃላፊነት እስከ ነሐሴ 2005 ዓ.ም ድረስ እንዲራዘም በሙሉ ድምፅ ተወስኗል።

ውሳኔው የእነዚህ ሀገሮች የሀብት ምንጭ በመሆን ሊያገለግሉና በእገዳው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ሊያሳርፉ በሚችሉ የፋይናንስና የባህር ዘርፎች ላይ ቡድኑ ምርመራውን እንዲቀጥል ያስችላል።

ቡድኑ የትኛውንም የትራንስፖርት መስመር፣ ወደብ፣ አየር ማረፊያ እና ለጦር መሣሪያ ዝውውር የሚረዱ አገልግሎቶችን በሙሉ እንዲመረምር ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ውሳኔው ቡድኑ በሶማሊያ የተመድ የፖለቲካ ቢሮ አማካኝነት የሚደረግ የጦርና ሌሎች ወታደራዊ መሣሪያዎች ዝውውርንና ዕርዳታን የማይመለክት መሆኑን አስገንዝቧል።

በኤርትራ ላይ የተጣለው ማዕቀብ በተመድ፣ በመገናኛ ብዙኃን ተወካዮች፣ በሰብአዊና የልማት ተቋማት ሠራተኞችና በሌሎች በሚመለከታቸው አካላት ለግል መጠቀሚያ በሚል ወደ ኤርትራ የሚላኩ ለመከላከል አገልግሎት የሚውሉ አልባሳትን እንዲሁም ለሰብአዊ አገልግሎት ብቻ እንዲውሉ የተደረጉና ጉዳት ሊያስከትሉ የማይችሉ ወታደራዊ ቁሳቁስን እንደማይመለከትም አብራርቷል።

ምክር ቤቱ ተቆጣጣሪ ቡድኑ የሶማሊያ የሽግግር መንግሥት ተቋማት የፋይናንስ አስተዳደር፣ ተጠያቂነትንና ግልጽነትን ለማሻሻል የሚያስችል የጋራ የፋይናንስ አስተዳደር ቦርድ ለማቋቋም ያቀረበውን ሀሳብ አድንቆ፣ የአገሪቱ ሀብት ላልተገባ ዓላማ የሚውልበት ሁኔታ እንዲቆምም አቅርቧል።

  • Facebook Page: 204028600784
  • FeedBurner: waltainfo/LdbW
  • Flickr: waltainformationcenter
  • Twitter: walta_info
  • YouTube: waltainformation
 242 guests