የፖለቲካዊ ግብን ያለመው የወሃቢያ ቡድን ዘመቻ
ኢብሳ ነመራ (ሐምሌ 19/2004)
ላለፉት ስምንት ወራት በአወሊያ ተቋም ዙሪያ “የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ” በሚል የተሰባሰቡት ጥቂት ግለሰቦች፣ ህዝበ ሙስሊሙንና የተቀረውንም ኢትዮጵያዊ ግራ ሲያጋቡ ከርመዋል።
አዲስ አበባ የሚገኘውን አወሊያ መስጊድን ማዕከላቸው ያደረጉት “የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ” ተብዬዎቹ 17 ግለሰቦች ፊት ለፊት ይዘወት ያቀረቡት ጥያቄ በአብዛኛው ሙስሊሙን ኅብረተሰብ ብቻ ይመለከት የነበረ ቢሆንም፣ “መንግሥት ጣልቃ ይግባበት” በሚል ለመንግሥት እንዲቀርብ የውጥር ይዘው እንደነበረም እናስታውሳለን፡፡ በዚሁ መነሻነት በመንግሥት በኩል ከፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስትርና ከሥራ ኃላፊዎቹ ጋር የውይይት መድረክ ተዘጋጅቶላቸው ነበር።
በዚህ የውይይት መድረክ ላይ ኮሚቴው ባነሳቸው ጥያቄዎች ዙሪያ መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበርም እናስታውሳለን፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በተደጋጋሚ ሲነሱ የቆዩ በመሆናቸው እጅ እጅ ቢሉንም፣ አሁንም ኮሚቴው እነሱኑ በተዛባ አኳኋን ማብጠልጠልን ሙጥኝ ብሎ ስለያዘ ከልሶ ማየቱን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ።
ቀደም ሲል ቀርበው የነበሩት የቡደኑ ዋና ዋና ጥያቄዎች፣ “የእሥልምና ጉዳዮች፣ ጠቅላይ ምክር ቤት (መጅሊስ) ምርጫ ተካሂዶ በአዲስ ይተካ፣ አህበሽ የተሰኘው የእሥልምና ኃይማኖት አስተምህሮ በግዳጅ መሰጠቱ ይቁም” የሚሉ ነበሩ፡፡
ሁላችንም እንደምናስታውሰው፣ በሥራ ላይ ያለውን መጅሊስ በምርጫ መተካትን በተመለከተ፣ ከኮሚቴው ጋር የተወያዩት የመንግሥት ባለስልጣናት ይህ ጉዳይ የመንግሥት ጉዳይ አለመሆኑን፣ ሆኖም ጥያቄው ተገቢ መሆኑን ገልፀው፣ የመጅሊሱ ምርጫ እንዲካሄድ በሚል ነበር መግባባት ላይ የተደረሰው፡፡
ይህንኑ ጉዳይ ለማስፈፀም በሥራ ላይ ካለው መጅሊስም፣ 17 አባላትን ካካተተው መፍትሄ አፈላላጊ ከሚቴም ገለልተኛ የሆነው የኡላማዎች (የሃይማኖት ሊቃውንት) ምክር ቤት ገለልተኛ አስመራጭ አስመርጦ የመጅሊሱን ምርጫ እንዲያካሂድ ይወሰናል፡፡ የኡላማዎች ምክር ቤቱም ሰዎች ተስማምተው ካዘጋጁት ደንብና መመሪያ ይልቅ ኃይማኖታዊ መርሆች ላይ ተመስርቶ ምርጫው ከመስጊድ ውጭ በሆነ ቦታ ሙስሊሙ ሕዝብ በሚኖርበት የቀበሌ አሰፋፈር መሠረት እንዲካሄድ ወስኖ የምርጫውን ፕሮግራም አሳውቋል፡፡
ይሁን እንጂ እንዴትና በማን እንደተወከለ በግልፅ የማይታወቀው አወሊያ መስጊድ ውስጥ የመሸገው |መፍትሄ አፈላላጊ´ የተሰኘው ኮሚቴ፣ በሥራ ላይ ያለውን መጅሊስ ማብጠልጠሉን፣ ምርጫ አይደረግም የተባለ ይመስል፣ “የመጅሊሱ ምርጫ ይደረግ፣ አሁን ሥራ ላይ ያለው መጅሊስ ይውረድ … ” የሚለውን ጩኸቱን ማቋረጥ አልመረጠም ነበር።
የኡላማዎቹ ምክር ቤት ምርጫው እንደሚካሄድ አስታውቆ የምርጫ ፕሮግራሙን ይፋ ካደረገ በኋላ ደግሞ፣ አንዳችም ተጨባጭና አሳማኝ ምክንያት ሳያቀርብ ምርጫው ሕዝበ ሙስሊሙ በሚኖርበት ቀበሌ መደረጉን እንደማይቀበል አሳወቀ፡፡ የግንቦት 7ቱ ልሣን ኢሳት “ቀበሌ የካድሬ መፈልፈያ እንጂ …” በሚል የመጅሊሱ ምርጫ በቀበሌ አስተዳደር ይደረግ የተባለ አስመስሎ ካቀረበው ውጭ ኮሚቴው አንድም አቋሙን የሚያስረዳለት ተቃውሞ አላቀረበም፡፡
“መፍትሄ አፈላላጊ” ተብዬው ኮሚቴ ይህን ያደረገው “የተቋቋመበትን ዋና ተልዕኮ አጠናቋል” በሚል በአወሊያ መስጊድ ያሰባሰባቸው ደጋፊዎቹ ከትኩረታቸው ውጭ እንዳያደርጉት በመስጋት ነው። “ዋነኛውን ተልዕኮዬ” ብሎ የያዘው ጉዳይ እልባት ወደማግኘት ከተሸጋገረ በኋላም፣ ኮሚቴው ቀደም ሲል ባነሳው አጀንዳ የያዛቸውን ደጋፊዎቹ እንዲርቁት ያልፈለገው ከመጅሊሱ ምርጫ የዘለለ አጀንዳ ስለነበረው ነው።
በተለይ አብዛኛው ሙስሊም ወደ መስጊድ በሚሄድበት የዓርብ /የጁመዓ የፀሎት ሥነ ሥርዓት/ በየሣምንቱ ለየት ያለ የተቃውሞ ገፅታ ወዳለው ስብስብ በመቀየር፣ “የአወሊያው ተቃውሞ እንደቀጠለ ነው።” የሚል ወሬ በተወሰኑ የአገር ውስጥና የውጭ አገር የመገናኛ ብዙኃን እያስጮኸ፣ ሙስሊሙንና ሙስሊም ያልሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ማደናገሩን ቀጠለበት።
ይህ ሁኔታ አወሊያን፣ የጁመዓ የፀሎት ሥነ ሥርዓትንና የተቃውሞ ስብሰባን የማይነጣጣሉ አድርጓቸው ቆይቷል። በዚህ ሀኔታ አወሊያ ላለፉት ስምንት ወራት በየሣምንቱ ዓርብ ዜና ሆኖ ቆይታል። በመጅሊሱ ምርጫ ዙሪያ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር መግባባት ላይ ከተደረሰበት በኋላና በፊት የአወሊያ የዓርብ ውሎ አንዳችም ለውጥ አልታየበትም።
በዚህ አኳኋን የአወሊያን ትኩሳት ተንከባክቦ ከማቆየት ጎን ለጎን በሚዲያና በተለያዩ አጋጣሚዎች በሥራ ላይ ያለውን መጅሊስ “የአህበሽ አስተምህሮ በግዴታ እየሰጠ ነው፣ እነእከሌ አህበሻ ናቸው፣ … ወዘተ” በሚል ወሬ በአንድ የእሥልምና ኃይማኖት አስተምህሮ ላይ የጥላቻ ጦርነቱን አጧጧፉት። ኮሚቴው ከመንግሥት ተወካዮች ጋር ባካሄደው ውይይት ላይ ምንም ዓይነት የእምነት አስተምህሮ በግዳጅ እንዳልተሰጠ፣ ለወደፊትም እንደማይሰጥ ተገልፆ መግባባት ላይ ተደርሶ እንደነበር ግን ይታወሳል፡፡
በውይይቱ ላይ ዜጎች በራሳቸው ፍቃድ የመረጡትን ኃይማኖትና የኃይማኖት አስተምህሮ የመከተል፣ በሠላማዊ መንገድ የአምልኮ ሥርዓታቸውን የመከወን ሕገ መንግሥታዊ መብት ያላቸው መሆኑ አፅንዖት ተሰጥቶት እንደነበርም እናስታውሳለን፡፡ ሙስሊሙ “አህበሽ” የተሰኘውን አስተምህሮ “ከእሥልምና ጋር ይፃረራል” በሚል አስትምህሮውንና ተከታዮችን በጥላቻ እንዲመለከት፣ እሥልምና መንግሥታዊ ኃይማኖት በሆነባቸው አገራት በዚህ “ባዕድ ነው” ባሉት የእሥልምና አስተምህሮ ላይ የማጥላላት ዘመቻ አውጀው ያቀረቧቸውን ምንም ተጨባጭነት የሌላቸው ወሬዎች እየጠቀሱ የጥላቻ መርዝ መንዛታቸውን ተያያዙት፡፡
በዚህ ዘመቻ ላይ ቀደም ሲል በተለያዩ ጎራ ተሰልፈው ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሲገዘግዙ የቆዩና ያልተሳካላቸው፣ እንዲሁም ከገዢው ፓርቲ ጋር አብረው ተጉዘው በተለያየ ምክንያት ከፓርቲው የተሰናበቱ አኩራፊዎች፣ በፖለቲካ መለዮዋቸው ላይ ኢማማ ጠምጥመው የአወሊያ ትኩሳት የወለዳቸው የማጥላላት ዘመቻው ፊታውራሪዎች ሆኑ።
በዚህ በኃይማኖት አስተምህሮ ዙሪያ ለተነሱ ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሠላማዊ መንገድ የፈቀደውን ኃይማኖትና የኃይማኖት አስተምህሮ የመከተል ህገ መንግሥታዊ መብት ያለው መሆኑን መነሻ በማድረግ፣ ሰለፊያና ሱፊ የሚባሉትን አስተምህሮዎችን ጠቅሰው ማብራሪያ ከሰጡ በኋላ ደግሞ የአወሊያው ቡድንና የአጋፋሪዎቹ የቅስቀሳ አቅጣጫ ተቀየረ። ይህ አዲስ የቅስቀሳ አቅጣጫ “መንግሥት አንድ የነበረውን እሥልምና እየከፋፈለ ነው” የሚል ሆነ፡፡
እዚህ ላይ የአወሊያ ቡድንና በኋላ የተቀላቀሉት አጋፋሪዎቹ፣ አህበሽ የተሰኘው የእሥልምና አስተምህሮ ላይ ተገቢ ያልሆኑና ህገ ወጥ ነገሮችን በመግለፅ ጭምር የማጥላላት ዘመቻ መክፈታቸውን፣ በርቀትም በቅርበትም ከዚህ አስተምህሮ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ሱፊዎች በመነጠል እሥልምናን እየከፋፈሉ እንደነበር ለምንከታተል ኢትዮጵያውያን በአዲሱ ወሬ በጣሙን ተገረምን፡፡ ያለ ምክንያት አልነበረም - የኢትዮጵያን ሙስሊሞች ለመከፋፈል የተቀናጀ ዘመቻ የከፈቱት እነርሱ ራሳቸው መሆናቸውን ስለምናውቅ ነው፡፡
ሰሞኑን የምንሰማቸው፣ ምናልባት ነገር ላለማካረር ሊሆን ይችላል ተደብቀው የቆዩ ነገሮች ይፋ መደረግ ሲጀምሩ ደግሞ በአወሊያ መስጊድ ዙሪያ የተሰበሰቡ ዋሃቢያ/ ሰለፊያ የተሰኘው አስተምህሮ ቡደን አራማጆች የኢትዮጵያን ሙስሊም በሁለት የተካረሩ ጎራዎች ከመክፈል ባሻገር፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የኖረውን የሱፊ እሥልምና አስተምህሮ በኃይል ለማጥፋት ዘመቻ መክፈታቸውን ተገንዝበናል። ከአማራ፣ ትግራይና ኦሮሚያ ክልል የመጡ ኡላማዎች ሰሞኑን የነገሩን ነገር ይህን ያረጋግጣል፡፡
ይህን ጉዳይ ከመንፈሳዊ አንፃር እንመልከተው፡፡ ኡላማዎቹ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች መፈፀማቸውን ተጨባጭ ማስረጃ እየጠቀሱ የገለፁት ነገር፣ እንኳን ፍጹም ጥሩና ምሉዕ በኩለሄ በሆነ ፈጣሪ አምላክ በሚያምን ሙስሊም ቀርቶ፣
በወሮበላ ወንበዴም የማይፈፀም ነው፡፡
ምሉዕ በኩለሄ የሆነው አምላክ ፍጡሩን ሁሉ ይወዳል፡፡ በዚህ በሚወደው ፍጡር ላይ የሚፈፀም ማንኛውም ክፉ ድርጊት ያሳዝነዋል፡፡ ከመንፈሣዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ፣ ሰዎች “በአምላክ አናምንም፣ ለመለኮታዊ ትዕዛዛት ተገዢ አንሆንም …” ቢሉ እንኳን፣ “ኃጢያተኛ ነህ” ብሎ የመበየን ሥልጣን የፈጣሪ አምላክ ብቻ ነው፡፡
ታዲያ እነዚህ ለራሳቸው የዋሃቢያ አስተምህሮ የበላይነት በፈጣሪ አምላክ የማይወደደውን፣ በህግም የሚያስጠይቀውን ድርጊት የፈፀሙ ሰዎች ለፈጣሪ ትዕዛዛት ራሳቸውን ያስገዙ፣ ለፈጣሪ ያደሩ - ሙስሊም ሊባሉ ይችሉ ይሆን? መልሱን ለንጹህ ሙስሊሞችና ለሌሎች ኃይማኖት ተከታዮች እንዲሁም ትክክለኛ የህሊና ፍርድ ላላቸው እተወዋለሁ፡፡
እነዚህ ሁኔታዎች በአወሊያ መስጊድ ዙሪያ የተሰበሰበው የዋሃቢያ ቡድን ጥቂት ማስመሰያ አጀንዳዎች ላይ ተንጠልጥሎ ያራመዳቸውን የማጥላላት ዘመቻና በዚህ አስተምህሮ ስር አሰባስቦ በጥላቻ ስሜት ቃኝቶ በመላው አገሪቱ ያሰማራቸው እብሪተኞች ዋነኛ አጀንዳቸው ምሉዕ በኩለሄ ፈጣሪ አምላክን መሠረት ያደረገ ኃይማኖታዊ ጉዳይ ያለመሆኑን ያመለክታሉ፡፡
አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ በዋሃቢያ አስተምህሮ ስር የተሰባሰቡ ግለሰቦች የፈጠሩት ቡድን፣ ቀደም ሲል ሙስሊሞችን በአምላክ ስም ድሆችን ለመመገብና አምላክን ለመዘከር በሚል የሚያዘጋጇቸውን የሰደቃ ፕሮግራሞች በመቃወም፤ “ሰደቃ አዘጋጃችሁ፣ ሰደቃ በላችሁ …” እያለ በየገጠሩ ሙስሊሙን በማዋከብ፣ በመዝለፍ፣ በመድበደብ፣ በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደል፣ ሰደቃ የተዘጋጀባቸውን መስጊዶች በማቃጠል፣ መስጊድ ውስጥ በመፀዳዳት … ወንጀል እንዲሁም ፀያፍና ነውረኛ ድርጊት ሲፈፅም መቆየቱን የድርጊቶቹ ሰለባ የሆኑ ዜጎችና ኡላማዎች ሲናገሩ አድምጠናል፡፡
በዚህ አኳኋን በመቻቻልና በመከባበር ተደጋግፈው መዝለቅ በሚችሉ መሠረታዊ ልዩነት በሌላቸው የእሥልምና አስተምህሮዎች መካከል የጥላቻ ድንበር ያኖሩት ወሃቢያዎች በመጨረሻ ራሳቸው አዲስ አበባ ላይ ሰደቃ እናውጣ ብለው ተነሱ፡፡ ሰደቃ ያዘጋጁት በአወሊያ መስጊድ ነበር፡፡
መፍትሄ አፈላላጊ ተብዬ የአክራሪ ዋሃቢያ ቡድን ማዘዣ ጣቢያ በሆነው አወሊያ መስጊድ የተዘጋጀው ሰደቃ ከመላው አገሪቱ ሰዎች የተጋበዙበት እንደሆነ ተነገረ፡፡ “የአንድነት፣ ሙስሊሙ ይቅር የሚባባልበት ሰደቃ” በሚል ሽፋን በአወሊያ መስጊድ የተዘጋጀ ሰደቃ ሕዝባዊ ስብሰባ (ትዕይንተ ሕዝብ) ነበር፡፡
በተለይ የመጅሊሱ ምርጫ በሠላም የሚካሄድበት ሁኔታ ስለተመቻቸና በዚህም ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ስለተረጋጋ፣ ይህን የተረጋጋ ሁኔታ በማተራመስ ለተከታዮቻቸው መመሪያ ሰጥተው የጀመሩትን ሁከት የሚያስቀጥሉበት ስብሰባ ነበር፡፡ እንደማንኛውም ኝዝባዊ ስብሰባ ወይም ትዕይንተ ሕዝብ ብንወስደው እንኳን ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ፍቃድ ያስፈልገው ነበር፡፡
ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ፍቃድ ማግኘት የሚያስፈልገው፣ ሕዝባዊ ስብሰባው ወይም ትዕይንተ ሕዝቡ ሊያስነሳ ለሚችላቸው ሕገ ወጥ ድርጊቶች ኃላፊነቱን የሚወስድ አካል ስለሚያስፈልገው ነው፡፡ ሌሎች አካላት ለህገ ወጥ ድርጊት መጠቀሚያነት እንዳያውሉት፣ በታዳሚዎቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ የፖሊስ ጥበቃ ሊደረግለትም ስለሚገባ ነው፡፡ ሕዝባዊ ትዕይንቱ በሠላማዊ ሁኔታ ተጀምሮ ማብቃት ስላለበት ይህን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ለትዕይንቱ አመቺ የሆነ ጊዜና ቦታ ሊወስን እንደሚችልም ሕግ ያዛል፡፡ የአወሊያው ማንአለብኝ ቡድን ግን ይህን ማድረግ አልወደደም፡፡
መንግሥት እጅግ ከፍተኛ ሕዝብ የሚታደምበት ትዕይንተ ሕዝብ መጥራታቸውን አስቀድሞ ስለደረሰበት፣ ትዕይንተ ሕዝቡ ሕገ ወጥ መሆኑን፣ በተለይ የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ስብሰባ በሚካሄድበት እለት የተጠራ በመሆኑ ለፀጥታ አመቺ አለመሆኑን ነግሮ የትዕይንቱ ፕሮግራም እንዲሰረዝ በመገናኛ ብዙኃን ማሳሰቢያ ሰጠ፡፡ ቀደም ሲልም በአገሪቱ ሕግና ሥርዓት የሌለ ያህል ቆጥረው በመላው አገሪቱ የሰዎችን የኃይማኖትና የአምልኮ ነፃነት ሲጥሱ የቆዩት የአወሊያ ጀግኖች ግን በዚህ የመንግሥት ማሳሰቢያ መሠረት ለሕግ ለመገዛት ፍቃደኛ አልሆኑም፡፡
ይህ ሕገወጥ ሕዝባዊ ስብሰባ ቀደም ሲል የታሰበበትን ቀውስ ለመቀስቀስ መነሻ ምክንያት ይሆን ዘንድ የተዘጋጀ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ፖሊስ ላስተላለፈው ማሳሰቢያ ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ፍቃደኛ ባለመሆናቸው ሕዝባዊ ስብሰባው በዚያን ዕለት እንዳይካሄድ ማድረግ ነበረበት፡፡ ይህን ለማድረግ ሲንቀሳቀስ ቀደም ሲል በወጠኑት መሠረት ከምሽቱ ሶስት ሰዓት በኋላ ደጋፊዎቻቸውን አደራጅተው ባሰማሯቸው አካባቢዎች ለረብሻ እንዲወጡ መልዕክት አስተላለፉ፡፡
የረብሻው ዋና አቀነባባሪዎችና አዛዦች በሚገኙበት አወሊያ መስጊድ፣ ከኃይማኖቱ ሥርዓት ውጪ የሕዝብ ጥሪ ሃዛን ተለፈፈ፡፡ በሌሎች ጥቂት የአዲስ አበባ መስጊዶችም የአወሊያው ቡድን ያደራጃቸው ግለሰቦች ሳይፈቀድላቸው መስጊዶችን በርግደው ገብተው በተመሣሣይ ሁኔታ ሃዛን ለፍፈዋል፡፡
በዚህ የሃዘን ጥሪ መሠረት ቀድሞውኑ ካዘጋጇቸው ሰዎች ውጭ የተቀረው ሙስሊም ኅብረተሰብ ለአመፅ ሊወጣ ፍቃደኛ አልነበረም፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች በየመንደሩ እየተሽሎከለኩ ሙስሊም የሆኑ ሰዎችን ቤት በር እየደበደቡ |ጅሃድ ነው ውጡ”´ የሚል ቅስቀሳ ያካሄዱበት ሁኔታም ነበር።
ይህ አዲስ አበባ የአፍሪካ አገራት መሪዎችን ተቀብላ በማስተናገድ ላይ በነበረችበትና ከሌላው ጊዜ የተለየ ሠላምና ፀጥታ በሚያስፈልግበት እለት በመላው ከተማዋ ሊካሄድ የተወጠነ ረብሻ ግን በጥቂት የፀጥታ ኃይሎችና የአመፅ ተሰላፊዎች ላይ ከደረሰ የመፈንከት ጉዳት ሳያልፍ በመንደር ጫጫታነት ተወስኖ አክትሟል።
የአወሊያው የዋሃቢያ ቡድን ግን በዚህ መታረም አልፈቀደም። እንዲያውም ማዕከሉን ከፍተኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በሚካሄድበት ግዙፍ የመርካቶ ገበያ አቅራቢያ ወደሚገኘው ታላቁ አንዋር መስጊድ አዘዋወረ፡፡ የረመዳን ፆም በገባበትና የታላቁ የረመዳን ፆም የመጀመሪያ የዓርብ/ ጁመዓ ፀሎት በሚካሄድበት ሥነ ሥርዓት ላይ በአኑዋር መስጊድ ፍቃድ የሌለው ህገ ወጥ የስብሰባ ጥሪ አስተላለፈ።
በዚህ እለት በጥቂት ሺህዎች የሚደርሱ የቡድኑ ደጋፊዎች በአኑዋር መስጊድ ዙሪያ ቢሰባሰቡም፣ ምንም ዓይነት ነውጥ ሳይቀሰቀስ ተበትነዋል። ይህን የጁመዓን የፀሎት ሥርዓት ሽፋን በማድረግ በታላቁ አንዋር መስጊድ ሊካሄድ የነበረውን ሕገ ወጥ የተቃውሞ ትዕይንት አስመልክቶ የአወሊያው ቡድን ለውጭ የመገናኛ ብዙኃን በሰጠው መግለጫ 500 ሺህ ሰው ተገኝቷል ብሏል ።
ህዝቡ የተሰበሰበበትን ከአንዋር መስጊድ ፊት ለፊት ያለ ከ200 ሜትር የማይበልጥ ርዝማኔ ያለውን የመኪና መንገድ ሥፍራ የሚያወቅ ሰው ይህ በአወሊያው ቡድን የተገለፀ የሰው ቁጥር ምን ያህል የተጋነነና ሀሰተኛ እንደሆነ መገመት ይቻላል። የኃይማኖት መሪ ካልሆንኩ ከሚል ሙስሊሙ የማይጠበቅ ውሸት በመናገራቸውም ታዝበናቸዋል።
ያም ሆነ ይህ አጠቃላይ የቡድኑና ቡድኑ የሚያራምደው የአወሊያ መስጊድ የዋሃቢያ ቡድን እንቅስቃሴ ስናስተውል፣ ሁኔታው ኃይማኖታዊ ያልሆነ፣ በውጭ ኃይሎች ድጋፍ በኃይማኖት ሽፋን የሚካሄድ ፖለቲካዊ ግብ ያለው መሆኑን እንረዳለን፡፡
| < Prev | Next > |
|---|


